የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ተጽእኖ በጀርመን
ማክሰኞ፣ መጋቢት 27 2014
የዩክሬን ጦርነት በአውሮጳ ሀገራት ላይ የተለያዩ ተጽእኖዎችን ማሳደሩ ቀጥሏል። በጦርነቱ ምክንያት ምዕራባውያን ጠንካራ ማዕቀቦችን የጣሉባት ሩስያ የምትወስዳቸው ከዚህ ቀደም ያልተጠበቁ የሚመስሉ የአጸፋ እርምጃዎች በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ላይ ተጽእኖ እያስከተሉ ነው። ከመካከላቸው አንዱ ሩስያ ወዳጅ ያልሆኑ ያለቻቸው የጋዝ ደንበኞች በውጭ ምንዛሪ ሳይሆን በሀገርዋ መገበያያ ሩብል እንዲከፍሉ አለበለዚያ የጋዝ ግዥ ውላቸው እንዲሰረዝ ባለፈው ሳምንት ባወጣችው አዋጅ ያወጣችው ማስጠንቀቂያ ነው። አዋጁ ከሚመለከታቸው ሀገራት አንዷ ጀርመን ናት።ጀርመን የሩስያን አዲስ ድንጋጌ አልተቀበለችም።ሆኖም የኤኮኖሚ ምሁርና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ፈቃዱ በቀለ ከበርሊን በዚህ ጉዳይ ላይ ለዶቼቬለ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ጀርመን በተለይ ከሩስያ ጋር ጥብቅ የኤኮኖሚ ግንኙነት ያላት ሀገር መሆንዋ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከነዳጅ ፍጆታዋ አብዛኛው ከሩስያ መግባቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከቷታል።ሌሎች የሩስያ ጋዝ ነዳጅ ዘይት ደንበኛ የሆኑ የአውሮጳ ሀገራትም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል።
በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት በሩስያ የኃይል አቅርቦት ላይ የአውሮጳ ኅብረት ማዕቀብ እንዲጥል ግፊት እየተደረገበት ነው። ኅብረቱ የሩስያ ወታደሮች ቡቻ በተባለው የዩክሬን ከተማ ፈጽመዋል ለተባለው ግድያ በአጸፋው ከሩስያ ነዳጅ ዘይት ወይም ጋዝ መግዛት ማቆምን እያሰበ ቢሆንም አባል ሀገራት ግን አንድ አቋም መያዝ አልቻሉም። እስካሁን ከአባል ሀገራት የተወሰኑት ከሩስያ ጋዝ መግዛት እንዲቆም ይፈልጋሉ ። ጀርመን ኦስትሪያና ኢጣልያን የመሳሰሉት ሀገራት ደግሞ ኅብረቱ የሚጥለው ተጨማሪ ማዕቀብ ጋዝና ነዳጅ ዘይትን ወደ መሳሰሉት እንዳይስፋፋ እየተከላከሉ ነው። የኔቶም የአውሮጳ ኅብረትም አባል የሆኑት ፖላንድ ኤስቶንያ ፣ላቲቪያ እና ሊትዌንያ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ ፣ሩስያ ለጦርነት ማካሄጃ ትጠቀምበታለች ያሉት የጋዝና የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ላይ የኅብረቱ አባል ሀገራት ማዕቀብ እንዲጣሉ እየወተወቱ ነው። ጀርመን በማዕቀቡ እንድትስማማ ከተለያየ አቅጣጫ ግፊቱ ቢበረታም ዶክተር ፈቃደ እንደሚሉት መንግስትና በሩስያ የሚወርቱ የጀርመን ባለሀብቶች አልተቀበሉትም። በዩክሬኑ ጦርነት የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ፣ ንብረት መውደሙ፣ ዜጎችም መሰደዳቸው ቀጥሏል።ምዕራባውያንም ለዩክሬን መሳሪያ ማቀበላቸው አልቆመም። ዶክተር ፈቃዱ በጦርነቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚሳተፉት ወገኖች ከሚገኙበት ቀውስ እንዲወጡ ጦርነቱን ከማቆም ውጭ ሌላ አማራጭ የለም ይላሉ ።ሆኖም ዋናው ጥያቄ ጦርነቱ እንዴት ሊቆም ይችላል? ነው።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ