1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት 30ኛ ዓመት እና አዲሱ ትውልድ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 4 2016

ሩዋንዳ ውስጥ የተፈፀመው የዘር ማጥፋት ዘመቻ 30ኛ ዓመት ባለፈው ሳምንት እሑድ ታስቧል። ይህ አሳዛኝ ድርጊት በወቅቱ ባልተወለደው ወይም የዛሬው የሩዋንዳ ወጣት ላይ አሁንም ድረስ ተዕፅኖ እንዳለው የዶይቸ ቬለ ባልደረባ አይዛክ ሙጋቤ የጻፈው ዘገባ ይጠቁማል።

ሁለት ወጣቶች የሩዋንዳ ዋና ከተማ ቆመው
ዛሬ ላይ ያለው የሩዋንዳ ወጣት በሀገሩ ስለተፈፀመው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ምን ያውቃል? ምንስ ይላል? ምስል PHIL MOORE/AFP/Getty Images

የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት 30ኛ ዓመት እና አዲሱ ትውልድ

This browser does not support the audio element.

እ.ጎ.አ. ሚያዝያ 7 ቀን 1994 ዓ ም በጀመረው እና ለሦስት ወራት በዘለቀው ግድያ ጽንፈኛ ሁቱዎች ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የቱትሲ አባላትን እና ቱትሲ ጎረቤቶቻቸውን ለማትረፍ የሞከሩ ሁቱዎችን ገድለዋል።  ዛሬ ላይ ያለው የሩዋንዳ ወጣት ስለዚህ ከሀገሩ አልፎ ዓለምን በወቅቱ ስላስደነገጠው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ምን ያውቃል? ምንስ ይላል? 


በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ሲፈፀም ሳሙኤል ኢሺምዌ የሁለት ዓመት ልጅ እንደነበር ይናገራል።  ወላጆቹን እና አብዛኛው የቤተሰቡን አባላት አጥቷል። እሱንና የተረፈው ታናሽ ወንድሙን አንዲት ሴት ናት ያሳደገቻቸው። የወላጆቹ አስክሬን አጎቱ የሚኖርበት ቤት አቅራቢያ ከሞቱ ከስምንት ዓመት በኋላ ተገኝቷል። «ከሩዋንዳ ላልሆነ ሰው ማስረዳት በጣም ከባድ ነው። ምክንያቱም በጣም የተለመደ ነገር ነበር። የተለየ ነገር አልነበረም። ሰዎች ማልቀስ እንኳን ተስኗቸው ነበር። ይህ የልጅነት ጊዜዬ አካል ነው። ጠባሳውን ጥሎ የሚያልፍ የማይረሳ  ትውስታ አለው።»

የሳሙኤል ወላጆችምስል Samuel Ishimwe/DW

በዝምታ የሚከናወን ጓደኛ መምረጥ 

ዛሬ ላይ ያለው አብዛኛው የሩዋንዳ ማኅበረሰብ ወጣት ነው። እንደ ሳሙኤል በሀገሪቱ ከ 30 ዓመት በፊት የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ድርጊት ጨርሶ አላየም። ስለሆነም አብዛኛው ወጣት ታሪኩን  የሰማው ከቤተሰቡ ወይም ትምህርት ቤት ከተማረው ነው።  ይሁንና በርካታ ወጣቶች እንደሚሉት ያኔ የሆነው ነገር ዛሬ ድረስ ይረብሻቸዋል።
የሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ነዋሪ የሆነው የ19 ዓመቱ ፍራንሲስ ሙጊሻ ለዶቼ ቬለ /DW/ እንደተናገረው «በቱትሲዎች ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት መታሠቢያ ማክበር የእሱም ግዴታ እና ኃላፊነት ነው።  « ይህ የመጀመሪያ ነው። ሲቀጥል ደግሞ እንደ አንድ ሩዋንዳዊ በአገሬ ውስጥ ስለሚሆነው ነገር ሁሉ ያሳስበኛል ። ስለዚህ ሀላፊነት ብቻ ሳይሆን የሚሰማኝ፤ ውስጤም የሚቀር እና ተላምጄ መኖር ያለብኝ ነገር ነው ። »

በዘር ማጥፋቱ የተገደሉምስል SIMON MAINA/AFP

ግን ሰዎች እንዴት ነው ራሳቸውን ከቀድሞ ታሪካቸው ጋር ራሳቸውን አላምደው መኖር የሚችሉት?

ኢማኑኤል ኢሺምዌ 30 ዓመቱ ነው።  በቀድሞው ታሪክ የተነሳ አሁን ድረስ አዲስ ሰዎችን መተዋወቅ እና ጓደኞችን ማፍራት ከባድ እንደሆነ ነው ለዶይቸ ቬለ የገለፀው።  «አንዳንዶች ጓደኞቻቸውን የሚመርጡት በጎሳ ላይ ተመርኩዘው ነው። ነገር ግን ይህንን በግልጽ አያሳዩም ወይም አይናገሩም ።እኔ በግሌ ጎሰኝነት ሚና ይጫወታል ብዬ አላስብምም። ምክንያቱም አሁን ሁላችንም ሩዋንዳውያን መሆናችንን ተረድተናል።»
 ነገር ግን ሁሉም ሰው የእሱ ዓይነት አመለካከት አለው ማለት እንዳልሆነውም ኢማኑኤል ይናገራል። ከአስከፊው የዘር ማጥፋትም በኋላ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በተደጋጋሚ ይህንን የሚያመላክቱ ዘገባዎች ይፋ ሆነዋል። ምንም እንኳን የሀገሪቱ መንግሥት አንድነትን ለማጎልበት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስለዘር ማጥፋት ጥናቶች በግዴታ እንዲሰጡ ቢያበረታታም  በአዲሱ ትውልድ መካከል አሁንም ድረስ የጎሳ ክፍፍል ይስተዋላል። ባለፈው ዓመት ለምሳሌ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ ጥቁር ሰሌዳዎች እና መታጠቢያ ቤቶች የጥላቻ ንግግር መልእክቶች ተገኝተዋል።  
ፍሬዲ ሙታንጉዋ ከዘር ጭፍጨፋው የተረፈ ወጣት ነው። አንዳንድ ሰዎች ለምን አሁንም ድረስ ከፋፋይ እንደሚሆኑ ግራ ይገባዋል። እሱ እንደሚለው ስለ ሩዋንዳ ታሪክ በትምህርት ቤት ደረጃ ያለው አስተምህሮ ሰዎችን ለማቀራረብ እንጂ ለማራራቅ አይደለም።  ፍሬዲ ቱትሲዎችን እና ሁቱዎችን አንድ ላይ በመሰብሰብ መፍትሔ በሚያመጣ መልኩ እንዲወያዩ መድረክ መፍጠር ያሻል። ይሁንና እሱ እንደሚለው አብዛኛው ችግር ገና ከቤት እና ከቤተሰብ ይጀምራል።

የሩዋንዳ ተፈናቃዮች በታንዛኒያ እጎአ 1994ምስል Gerard Julien/AFP/Getty Images

ስለ ዘር ጭፍጨፋው በቂ ትምህርት ተሰጥቷል?

« አንዳንድ ወላጆች ስለ ተከሰተውን ነገር ለልጆቻቸው ማስረዳት አይፈልጉም። ይህ ማለት ብዙ ልጆች ስለ ዘር ጭፍጨፋው የሚሰሙት በመታሠቢያው ወቅት ነው። ነገር ግን የዘር ጭፍጨፋው መንሥኤ ምን ነበር ? ማን ፈጸመው የሚለውን አያውቁም። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ነገር ዳግም እንዳይፈፀም ወላጆች ደፍረው ስለሆነው ነገር ማስረዳት አለባቸው። »  ፍሬዲ እንደሚለው በተለይ በሁቱ ጎሳ አባላት ዘንድ ዝምታው የባሰ ነው። በዚህም የተነሳ ወጣቱ ሙሉ መረጃ የለውም።  « የወንጀል ፈፃሚዎቹ ልጆች፤ የዘር ማጥፋቱን የፈፀሙት ሰዎች እውነታዎን ከልጆቻቸው ይደብቃሉ። ምክንያቱም ምን እንደፈፀሙ እንዲያውቁ አይፈልጉም። አሁንም በሀፍረት ላይ ናቸው። ስለሆነም ለልጆቻቸው  ስለተፈጸመው ነገር አይነግሯቸውም። ለዚህ ነው አንዳንድ ወጣቶች በቱትሲዎች ላይ ስለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ሙሉ በሙሉ የማያውቁት።»

እንደ የ 27 ዓመቱ ክርስቲያን ሺሚኒማና ያሉ ሌሎች ወጣቶች ደግሞ ስለ ተፈፀመው ነገር የተማርነው ወይም የተረዳነው ዘግይቶ ነው ይላሉ።  ክርስቲያን በሀገሩ ስለተፈፀመው የዘር ማጥፋት በደንብ የገባው 16 ዓመት ሲሆነው ነው። «ከወላጆቼ እንደሰማሁት እና በታሪክ ክፍለ ጊዜ ትምህርት ቤት ውስጥ እንደተማርኩት ፣ ከጓደኞቼም ጋር እንደተወያየሁበት ከሆነ አሁንም ቢሆን ስለ የዘር ማጥፋቱን ፅንሰ ሀሳብ ፣ መንስኤ እና አደገኝነት ብዙ መማር የሚገባን ነገር አለ። በተለይ ደግሞ ከ 20 በታች ያሉ ወጣቶች። »
ክርስቲያን እንደሚለው በሩዋንዳ ቱትሲዎች ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንዲፈፀም የዳረገው ፅንሰ ሀሳብ የአንድ ሚሊዮን ሕዝብን ሕይወት ከቀጠፈ በኋላም ተዳፈነ እንጂ አልጠፋም። ሰዎች በጉዳዩ ላይ ለመወያየት አለመድፈራቸው በራሱ  እንደ አዲስ የጎሳ ግጭት እንዳይነሳ ስጋት ነው ባይ ነው።  

የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት 30ኛ ዓመት ዕለት የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና ባለቤታቸውምስል LUIS TATO/AFP

አዲሲቷ ሩዋንዳ

በሌላ በኩል ደግሞ አብዛኞቹ የሩዋንዳ ወጣቶች የሀገራቸውን ጥቁር ታሪክ ወደ ኋላ ትተው ሁሉም ጎሳዎች በጋራ የሚኖሩባትን አዲስ ሀገር መገንባት እንደሚፈልጉ ክርስትያን ይናገራል። 
« ጓደኞቼን ስመርጥም ይሁን በጠቅላላ ሕይወቴ ጎሰኝነት ምንም አይነት ቦታ የለውም። አብዛኞች የጎሳ መከፋፈል ስለሚፈጥረው አደጋ ተረድተዋል። ስለሆነም በአንድነት እና በአዲሱ ሕገ መንግሥት ያምናሉ። ምክንያቱም የጎሳ ልዩነት ሩዋንዳ ላይ ወደተፈፀመው ዓይነት የዘር ማጥፋት ሊያመራ እንደሚችል ያውቃሉ።»
ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜም ሩዋንዳ በውጪው ዓለም እንድትታይ የሚፈልጉት በዚህ መልኩ ነው፡ ሁቱዎች እና ቱትሲዎች በሰላም አብረው የሚኖሩባት፣ የበለፀገ ኢኮኖሚ የሰፈነባት፣ እና ጎዳናዎቿ ሁል ጊዜ ንጹህ የሆኑባት። 
 

አይዛክ ሙጋቤ

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW