1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ 47ኛ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 27 2017

የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩው ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸነፉ። ትራምፕ በዊዝኮዚን ግዛት በማሸነፋቸው ወደ ዋይት ሐውስ ለመመለስ የሚያስፈልጋቸውን 270 ኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጾች አግኝተዋል። ትራምፕ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክት እየጎረፈላቸው ይገኛል።

የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩው ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸነፉ
የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩው ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸነፉ። ምስል Brendan McDermid/REUTERS

ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ 47ኛ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ። ትራምፕ በዊዝኮዚን ግዛት በማሸነፋቸው ወደ ዋይት ሐውስ ለመመለስ የሚያስፈልጋቸውን 270 ኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጾች አግኝተዋል።

ትራምፕ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት መሪዎች የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክት እየጎረፈላቸው ይገኛል።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ለዶናልድ ትራምፕ "የእንኳን ደስ አለዎ" መልዕክት አስተላልፈው ሀገራቸው ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ባሻገር ለሚገኙት ለሁለቱም ነጻነት እና ብልጽግና ለመፍጠር ከአሜሪካ ጋር መሥራቷን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።

የጀርመን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በበኩላቸው "ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈዋል። በዚህም እንኳን ደስ አለዎ እንላቸዋለን" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ቤርቦክ በአሜሪካ ምርጫ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት ወደ ዩክሬን ካደረጉት ጉዞ ሲመለሱ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ፎን ዴር ላየን ትራምፕ በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አለዎ መልካም ምኞታቸውን በኤክስ በኩል ገልጸዋል።

"የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ ከአጋር በላይ ናቸው። 800 ሚሊዮን ዜጎቻችንን አንድ በሚያደርግ እውነተኛ የሕዝቦች አጋርነት የተሳሰርን ነን" ብለዋል።

አውሮፓ እና አሜሪካ "ዘላቂ ኅብረት እና ታሪካዊ ትሥሥር እንዳላቸው የገለጹት የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ቻርለስ ሚሼል ተመሳሳይ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።

ትራምፕን "እንኳን ደስ አለዎ" ያሉት የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ የሩሲያ ጦርነት በዩክሬን ያበቃል የሚል ተስፋቸውን አያይዘው ገልጸዋል።

ባለፈው መስከረም ከትራምፕ ተገናኝተው ዩክሬን ጦርነቱን በምታሸንፍበት የድል ዕቅድ ላይ መምከራቸውን የገለጹት ዜሌንስኪ "ፕሬዝደንት ትራምፕ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች 'ሰላም በጥንካሬ' የሚል ቁርጠኝነታቸውን አደንቃለሁ" የሚል መልዕክት አስፍረዋል።  

የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝደንት እና በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ የጸጥታ ምክር ቤት አባል ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ግን ለዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጥሩ ቀን እንዳልሆነ በገደምዳሜ ጠቆም አድርገዋል።  

በቴሌግራም ገጻቸው "ሐሌሉያ" ሲሉ የጻፉት የሩሲያ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማሪያ ዛክሐሮቫ ምርጫውን ያሸነፉት የገዛ ሀገራቸውን የሚወዱት ዕጩ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮርጂያ ሜሎኒ፣ የሐንጋሪው ቪክቶር ኦርባን ትራምፕን "እንኳን ደስ አለዎ" ካሉ መሪዎች መካከል ይገኙበታል።

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW