የራያ ቆቦ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው መመለስ ጀመሩ
ማክሰኞ፣ መስከረም 24 2015
የራያ ቆቦ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ!
ከነሐሴ 18/2014 ዓ ም ጀምሮ በሰሜን ወሎ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት ተፈናቅለው የነበሩ የራያና የራያ ቆቦ ወረዳዎች ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ተፈናቃዮችና ባለስልጣናት ተናገሩ። አንዳንዶቹ ወደ ቀያቸው ቢመለሱም ንብረታቸው ተዘርፎና ወድሞ ማግኘታቸውን አመልክተዋል፣ ዛሬ ጨርጨርና ዋጃ በተባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ዉጊያ መኖሩ ተመልክቷል፡፡
የህወሓት ታጣቂዎች ይዘዋቸው ከነበሯቸው የሰሜን ወሎ አንዳንድ አካባቢዎች ትናንት መውጣታቸውን ተከትሎ ተፈናቅለው የነበሩ የራያና የራያ ቆቦ አካባቢ ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆናቸውን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ አንድ ተፈናቅለው ወልዲያ ከተማ ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃይ ዛሬ በጠዋት ወደ አካባቢቸው ለመመለስ የትራንስፖርት ወረፋ እየጠበቁ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
“ እየወጣሁ ነው ከወልዲያ እየወታሁ ነው አዎ፣ የሄደ አለ ማታ … ቤተሰብ የያዘም እንዲሁም ብቸኛ የሆነ ማታ ወጥቶ ከሌሊት ጀምሮ በተለያየ ተሸከርካሪ እየሄደ ነው እንግዲህ የእኛም ተራ እየደረሰ ነው ጓደኛሞች ተሸክፈን አንድ ላይ የኛ ቀበሌ የሆንነው ለመሄድ ፈልገን ነው እየወጣን ነው እየሄድን ነው ከመርሳ የኛ ቀበሌ (ተፈናቃዮች) እየመጡ ነው ወልዲያም የደረሱ አሉ፣ መንገድ ላይም የደወሉልን አሉ በአንድ ላይ እንውጣ እያሉ የደረሱም አሉ”
ከራያ ቆቦ 022 ቀበሌ እንደተፈናቀሉ የሚናገሩት ሌላው አስተያየት ሰጪ አካባቢያቸው ነፃ መውጣቱን ተከትሎ ወደ ቀያቸው ቢመለሱም ያገኙት ምንም ንብረት እንደሌለ ረዘም ያለ መንገድ በመጓዝና የስልክ መስመር ካገኙበት ቦታ ደውለው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ ሰጥተዋል፣ ተጨማሪ አስተያየቶችን ከቆቦና አካባቢው ለማግኘት ከፍተኛ የስልክ መቆራረጥ በመኖሩ አልተሳካልኝም፡፡
ሌላዋ በመርሳ መጠለያ ጣቢያ የምትገኝ ተፈናቃይ ቀድመው የሄዱ ተፈናቃዮች ቤት ንብረታቸው መዘረፉንና ምንም የቀረ ሀብት ባለመኖሩ ወደ ቦታው መመለስ እንደማይፈልጉ አስረድተዋል፡፡
“ እየሄዱ ነው፣ አሁንም ዛሬም ሄደዋል፣ እቃችን ተቃጥሏል፣ ብለው ደወሉልን ሀብትም የለ፣ አዱኛም የለም ብለው ደወሉ 022 ይባላል ከዚያ ሄደን እርዳታም የለም (ውሀ) የምንጠጣበትም ‘ጎማ’ የለ ሄደንም የምንገባበት ቤት የለንም፡፡”
አንድ አስተያየት ሰጪ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ በወልዲያ ከተማ የነበሩ በርካታ ተፈናቃዮች በሙሉ ወደ ራያ ቆቦ ዛሬና ትናንት በእግርና በተሸከርካሪ ወደ ቀደመ ቀያቸው እየተመለሱ እንደሆ ተናግረዋል፡፡
እስከ 40 ሺህ የሚደርሱ የራያና የራያ ቆቦ ወረዳ ተፈናዮች በመርሳ ከተማ ይኖሩ በመጠለያና ከህብረተሰቡ ጋር ተጠግተው ይኖሩ እንደነበር የገለፁልን በሰሜን ወሎ ዞን የመርሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መልካሙ ዓለሙ ናቸው፡፡ ትናንት አካባቢያቸው ነፃ መውጣቱን ተከትሎ ብዙዎቹ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው፣ “ የከተማው በጎ አድራጎት ያደረጉ የማህበረሰብ ክፍሎች አሉ፣ የትራንስፖርት ወጪ የሌላቸውን እያጓጓዘነው እዚህ ያለው በተቻለ መጠን ደግሞ የትራንስፖርት ወጪ ሸፍኖ የሚወስድ የማህበረሰብ ክፍል አለ ከዚያው ከተፈናቃዩ፣ እየወጣና ወደየቤቱ እየገባ ያለበት ነባራዊ ሁኔታ ነው ያለው፤ ከትናንትና ማታ ጀምሮ ወንዶች በተለይ ወጥተዋል፣ ህፃናትና ሴቶችን በተመለከተ ደግሞ ከተዋት ጀምሮ ምንም ያለማባራት በተለያዩ ተሸከርካሪዎች እተጫነ እየሄደ ነው ያለ፣ የከተማው ማህበረሰብም አቅሙ በፈቀደ መጠን ለሌላቸው ሀብት በማሰባሰብ ተሸከርካሪ ያላቸው የበጎ አድራጎት ሥራ በመስራት እየመለሰ ያለበት ነባራዊ ሁኔታ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡” ነው ያሉት፡፡
የትግራይ ማዕከላዊ ኮማንድ የተባለው አካል ባለፈው እሁድ በትግራይ ቴሌቪዥን ባሰራጨው መግለጫ፣
“አንጃብቦ ያለውን ጥምር ወረራ በአስተማማኝ መልኩ ለማስተናገድ በደቡብ አቅጣጫ ተቆጣጥረን ከነበረው የአማራ አካባቢዎች ወጥተን የቦታ ማሻሻያ አድርገናል” ብሏል፣ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ጉዳዩን አስመልክቶ ለው ነገር የለም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጨርጨርና ዋጃ በተባሉ አካባቢዎች ዛሬ ከፍተኛ ውጊያ መኖሩን ከአካባቢዎቹ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሓት ኃይሎች ውጊያ ከጀመሩ የዛሬ ወር ጥቅምት 24/2015 ዓ ም ድፍን 2 ዓመት ይሞላቸዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ