1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የራያ አላማጣ ተፈናቃዮች መመለስና ውዝግቡ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 11 2016

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከራያ አላማጣ ተፈናቅለው በትግራይ የተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ ወገኖች ወደ ራያ አላማጣ መመለስ መጀመራቸውን የትግራይ ክልል መንግሥት አስታውቋል። ከጦርነቱ በኋላ በአማራ ክልል ስር ያለው የራያ አላማጣ ጊዜያዊ አስተዳደር ደግሞ ወደ አካባቢው እየተመለሱ ያሉት ታጣቂዎችና ነዋሪ ያልነበሩ ናቸው ሲል ይከስሳል።

አላማጣ
አላማጣምስል Alemenew Mekonnen Bahardar/DW

የራ አላማጣ ተፈናቃዮች መመለስና ውዝግቡ

This browser does not support the audio element.

በጥቅምት 2013 ዓ ም በሰሜን ኢትዮጵያ በመከላከያ ሠራዊትና በህወሓት ታጣቂዎች መካከል ተቀስቅሶ የነበረው ጦርነት የበርካቶችን ሕይወት ሲቀጥፍ በሌሎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት አድርሷል። በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ የአማራ፣ የትግራይና የአፋር ክልል ነዋሪዎችን ደግሞ ከቀያቸው አፈናቅሏል።

ጦርነቱ ካፈናቀላቸው የራያ አላማጣ ነዋሪዎች መካከል 14ሺህ የሚሆኑት ትናንት ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ወደ ቀደመ መኖሪያቸው ራያ አላማጣ ወረዳ፣ አላማጣ ከተማ፣ ዋጃ፣ ጥሙጋና መረዋ ጨቀራ ወደተባሉ አካባቢዎች መመለሳቸውን የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ለዶቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል።

የባለሥልጣናቱ ምላሽ

አቶ ኪሮስ እንደሚሉት በጦርነቱ ምክንያት ከ82 ሺህ በላይ የትግራይ ክልል ተወላጆች ተፈናቅለው በመቀሌ፣ መኾኒ፣ በማይጨውና በሌሎች ከተሞች በተፈናቃይ መጠለያ ድንኳኖች ይኖራሉ። አብዛኛዎቹ ተፈናቃዮች ሙሉ በሙሉ ንብረታቸው የወደመባቸው፣ ቤታቸው የፈረሰና ንብረታቸው ለሌሎች ተላልፎ የተሰጠ እንደሆነም ያስረዳሉ። በእርግጥ ቤታቸው ያልፈረሰና ያልወደመባቸው ተፈናቃዮች እንዳሉም አልሸሸጉም። ከ2013 ዓ ም ወዲህ በአማራ ክልል ስር የሚተዳደረው የአላማጣ ከተማ ከንቲባና የወሎ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ አበራ በበኩላቸው ተመላሾቹ አብዛኛዎቹ ታጣቂዎችና ከ2013 በፊት በአካባቢው ይኖሩ ያልነበሩ ናቸው ይላሉ።

«በሕገወጥ መንገድ ተፈናቃይ ናቸው በሚል ተዋጊ ኃይል ነው ወደ አላማጣ ከተማ እንዲገባ የተደረገው፣ አንደኛ ከመንግሥት ስምምነት ውጪ ነው፣ ሁለተኛ የግለሰብ ፍላጎት ነው፣ ማንም የተስማማ የለም።» ሲሉ አቶ ኃይሉ ሂደቱን ተቃውመዋል።

የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የወሎ አማራ ማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ አባል አቶ መንገሻ ቸሩ በበኩላቸው፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ስምምነት የተደረገ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ተመላሾች ከሌሎች የትግራይ ክልል አካባቢዎች እንደመጡ ይናገራሉ።

እንደ አቶ መንገሻ ተፈናቃይ ተብሎ የተመለሰው ታጣቂ የነበረና ከመሀል መቀሌ የመጣ ነው። የአላማጣ ሕዝብ ግን ተፈናቃዩ ወደ ቀየው እንዲመለስ ፈቃደኛ መሆኑን አመልክተዋል። «የአላማጣ ተፈናቃይ ብለው ካስገቡት ውስጥ 95 ከመቶው ተዋጊና ከሐውዜን፣ ከደጋሐሙስና ከመሐል ትግራይ የመጣ ነው» በማለት አስረድተዋል። 

የደቡብ ትግራይ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ተፈናቃዮቹን የአላማጣ ነዋሪዎች በከፍተኛ ደስታ ተቀብለዋቸዋል ነው ያሉት። የሃይማኖት መሪዎች፣ ታላላቅ ሽማግሌዎች «ከዚህ በኋላ ይበቃናል» ብለው እንደተቀበሏቸውም አብራርተዋል።

አቶ ሀፍቱ ይህን ቢሉም ተፈናቃዮቹ ወደ ከተማዋ በገቡበት ወቅት የአካባቢውን የአማራ ተወላጆችን ስነልቦና የሚፈታተን መዝሙርና መፈክር በማሰማታቸው አለመረጋጋቶች ተፈጥረው እንደነበር የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንገሻ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ቢቆዩም በስፍራው የነበረው የፌደራል የፀጥታ ኃይል ሁኔታውን እንዲበርድ ማድረጉን አመልክተዋል።

የተፈናቃዮችን ቁጥር በተመለከተ ሁለቱ አካላት የሚሰጡት መረጃ እጅግ የተራራቀ ነው። የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ትናንት የተመለሱትን ሳይጨምር ተፈናቃዮቹን 68ሺህ ያክል ናቸው ሲሉ፣ የወሎ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ አበራ ደግሞ ያልተመለሱ ተፈናቃዮች ከ500 አይበልጡም ባይ ናቸው።ፎቶ ከማኅደር፤ አላማጣ ከተማ ምስል DW

የአላማጣ ከተማ ነዋሪ አስተያየት

አንድ የአላማጣከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ እንዳሉት ሦስት ተፈናቃይ ጎረቤቶቻቸው ተመልሰዋል፣ ሄደውም ጠይቀዋቸዋል። ሆኖም ሌሎች ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎችም ወደ ከተማዋ መግባታቸውን አስረድተዋል።

ተመላሾቹ በሙሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ መሆናቸውን የጠቀሱልን የደቡብ ትግራይ አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ፣ ከተመላሾች መካከል ከ2013 ዓ ም በፊት የትግራይ ታጣቂ የነበሩ ሚሊሻዎች ከነመሳሪያቸው መመለሳቸውንና ሆኖም ፀጥታውን የሚጠብቀው የፌደራል የፀጥታ ኃይል በመሆኑ ታጣቂዎቹ ፀጥታ እንዲያስጠብቁ ግን ተልዕኮ አይሰጣቸውም ነው ያሉት።

የተፈናቃዮችን ቁጥር በተመለከተ የሁለቱ ወገኖች መረጃ

የተፈናቃዮችን ቁጥር በተመለከተ ሁለቱ አካላት የሚሰጡት መረጃ እጅግ የተራራቀ ነው። የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃፍቱ ኪሮስ ትናንት የተመለሱትን ሳይጨምር ተፈናቃዮቹን 68ሺህ ያክል ናቸው ሲሉ፣ የወሎ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ አበራ ደግሞ ያልተመለሱ ተፈናቃዮች ከ500 አይበልጡም ባይ ናቸው።

ትናንት 14 ሺህ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን የገለፁት አቶ ኪሮስ፣ በቀጣይ ጥቂት ቀናት ሌሎች ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ ቀያቸው የመመለስ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጠዋል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW