1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዋንዳው የዘር ፍጅት መሪ ከዋኒ በቁጥጥር ስር መዋል እና የወንጀለኞች ሽሽት መጨረሻ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 15 2012

እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ሚያዝያ 6, 1994 ዓ.ም በሩዋንዳ በስልጣን ላይ የነበሩ አክራሪ የሁቱ ጎሳ አመራሮች ፣ የፖለቲካ ደጋፊዎቻቸውና የታጠቁ ሚሊሻዎች ስልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀልን በማቀነባበር ለ 100 ያህል ተከታታይ ቀናት እጅግ አሰቃቂ የሚባል ግድያ የወንጀል ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል::

Gesucht-Poster Felicien Kabuga
ምስል picture-alliance/abaca/E. Hockstein

በርዋንዳ የዘር ፍጅት ተሳትፎ የነበራቸው ሰው መያዝ ምን አንድምታ አለው?

This browser does not support the audio element.

እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ሚያዝያ 6, 1994 ዓ.ም በሩዋንዳ በስልጣን ላይ የነበሩ አክራሪ የሁቱ ጎሳ አመራሮች ፣ የፖለቲካ ደጋፊዎቻቸውና የታጠቁ ሚሊሻዎች ስልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀልን በማቀነባበር ለ 100 ያህል ተከታታይ ቀናት በተለይም በአናሳዎቹ የቱትሲ ማህበረሰብ አባላትና ለዘብተኛ ሁቱዎች ላይ እጅግ አሰቃቂ የሚባል ግድያ የወንጀል ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል:: በጥቃቱም ከ 800ሺህ በላይ ሰላማዊ ሰዎች በግፍ ሕይወታቸን ማጣታቸው ይነገራል::ለዘር ዕልቂቱ መንስኤ የሆነው የሁቱ ጎሳ ተወላጅ የነበሩት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጁቬናል ሀብያሪማና ተሳፍረውበት የነበረው አውሮፕላን በተተኮሰ መሳሪያ ከተመታ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ሲሆን ይህም ክስተት ቀደም ሲል እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ1993 ዓ.ም የሁቱ እና ቱትሲ ጎሳ አባላት በጋራ ጥምር መንግስት ለመመስረት የጀመሩትን የሰላም ጥረት እንዲደናቀፍ አድርጎታል:: "አካዙ" በሚል ስያሜ የሚታወቀው ሁቱ መራሹ የፖለቲካ አመራሮችና የልሂቃን ኢመደበኛ የአደረጃጀት ቡድንም የዘር ዕልቂቱ ከመቀስቀሱ አንድ ዓመት አስቀድሞ በሩዋንዳ የቱትሲ ጎሳ አባላትን ለመፍጀት የሚረዳ ዕቅድ መንደፉ ይነገራል:: ለዚህም ዕኩይ ዓላማ ስኬት አባላቱ የራሳቸውን የራዲዮ ጣቢያ /ኮሊንስ/ እስከማቋቋም ደርሰው ነበር:: በሩዋንዳ የዘር ማጥፋቱ ዕልቂት እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1994 ዓ.ም ሲቀሰቀስም እነዚሁ የፖለቲካ አመራሮችና ልሂቃን ጥላቻን በመስበክና የዘር ፍጅት ለሚፈፅሙ የሁቱ ነፍሰ ገዳይ ሚሊሻዎች /ኢንተርሀሞይ እና ኢምፑዛሙጋምቢ/ "ቱትሲዎች ከምድረ ገፅ እንዲጠፉ" የሚያስገነዝቡ የአመፅና የጥላቻ መልዕክቶችን በማስተላለፍና በማደፋፈር ከዚም ሌላ ግድያ እንዲፈፀምባቸው የሚፈልጓቸውን የቱትሲ ተወላጆች ስም ዝርዝር ጭምር እንዲገለፅ በማድረግ ሩዋንዳ የምድር ሲዖል እስክትመስል ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች በተገኙበት ቦታ ሁሉ እንደ እንስሳ እየታደኑ በግፍ እንዲጨፈጨፉ አመራር በመስጠት በዓለም አሰቃቂው ወንጀል እንዲፈፀም አድርገዋል ተብለው ዛሬም ድረስ በታሪክ ሲወቀሱ ይኖራሉ:: ለሩዋንዳው የዘር ፍጅት የምፅአት ዘመን አሰቃቂነት አንድ ማሳያ የሚሆነው ከኪጋሊ 30 ማይልስ ርቀት በምትገኘው ትልቋ የኒያማታ ከተማ ነዋሪ ከነበሩ 120 ሺህ ዜጎች በ 45 ቀናት የዘር ፍጅት ከስድስት ቱትሲዎች አምስቱ እንዲገደሉ ተፈርዶባቸው በሕይወት መትረፍ የቻሉት ከ 50 ሺህ ያነሱ ብቻ ሆነው መገኘታቸው ነው:: ይህን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲመሩ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል ደግሞ የቀድሞው ባለሃብት ፌሊሲዬን ካቡጋ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል:: ግለሰቡ የሟቹ ፕሬዝዳንት ሀብያሪማና የቅርብ ወዳጅና አማካሪ ብቻ ሳይሆኑ ሴት ልጃቸውና የፕሬዝዳንቱ ወንድ ልጅ በጋብቻ የተሳሰሩ ጭምር ነበሩ::

በወቅቱ ለነበረው ሁቱ መራሹ ጊዜያዊ መንግስትና ለአክራሪ የሁቱ ገዳይ ሚሊሽያዎች የሎጂስቲክና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ቀውሱ እንዲባባስ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል ስትል የምትወነጅላቸውን "የፎ ደ ዴፎንስ ናሲዮናል" ድርጅት አንዱ መስራች ካቡጋ ዩናይትድስቴትስ ያሉበትን ለሚጠቁም 5 ሚልዩን ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ ስትል አስታውቃ ነበር:: ተጠርጣሪው ባለፈ ግንቦት 8,2012 ዓ.ም ፓሪስ አቅራቢያ በፖሊስ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው አስቀድሞ አንየህ ሱዩህ ሴን አዝኒዬር በተባለ አካባቢ እዛው ፈረንሳይ ውስጥ ማንነታቸውን ደብቀው ይኖሩ ነበር ተብሏል:: እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 1994 ዓ.ም በሩዋንዳው የዘር ፍጅትና በሰባት የተለያዩ ወንጀሎች ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላም ግለሰቡ ስማቸውን በመቀየርና ሃሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ላለፉት 26 ዓመታት በጀርመን፣ ቤልጅየም፣ ኮንጎ ኪንሻሳ፣ ኬንያና ስዊዘርላንድ ውስጥ ሀገር እየቀያየሩ በሽሽት መኖራቸውን የፈረሳይ የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል::

ስሙን መግለፅ ያልፈለገ በሩዋንዳ የካቡጋ ትውልድ መንደር ሙኢንጋ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ ተጠርጣሪው ለዘር ዕልቂቱ መባባስ ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው ጥላቻ ቀስቃሽ የራዲዮ ጣቢያ ከመስራቾቹ አንዱ ነበሩ ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል:: "እሱ በወቅቱ በሁቱና ቱትሲ ጎሳዎች መካከል የጥላቻን እሳት በማቀጣጠል የሚታወቀው የአር.ቲ.ኤል.ኤም /RTLM/ የሚሌ ኮሊንስ የራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ አንዱ መስራች ነበር:: ግለሰቡ በርካታ ገጀራዎችን ለነፍሰገዳዮች በማከፋፈል በሺዎች የሚቆጠሩ ሩዋንዳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲያልቁ መንስኤ ሆኗል:: አሁን በካቡጋ መታሰር በጣም ደስተኞች ነን:: ለሩዋንዳ ተላልፎ እንዲሰጥና የፍርድ ሂደቱ እዚህ እንዲካሄድ ነው ፍላጎታችን::"

የዶይቼ ቨለ የአፍሪቃ ፕሮግራም ጋዜጠኛና ተንታኝ ፍሬድ ሙቩኒ "የተባበሩት መንግሥታት ሥምምነት እንደሚያብራራው የሩዋንዳውን የዘር ዕልቂት በማስተባበርና በመደገፍ የወንጀል ተሳትፎ ነበራቸው የሚባሉ ተጠርጣሪዎችን የፍርድ ሂደት የመከታተል ስልጣን የተሰጠው በፀጥታው ምክር ቤት ሥር የተቋቋመው ዓለማቀፉ የወጀለኞች ፍርድቤት ነው" ሲል ይገልፃል:: በእርግጥም ፌሊሲዬን ካቡጋ የዚህ ከፍተኛ ወንጀል የፈፀመ ቡድን አንዱ አካል ናቸው:: በዘር ማጥፋቱ ወንጀል እንደ መከላከያ ሚኒስትሩ አውግስቲን ቢዚማናና በወቅቱ የደህንነት ሃላፊ የነበሩት ፕሮቴስ ሚራንያ ሚናም የላቀ እንደነበር አይዘነጋም ሲልም ጠቅሷል::

"በእርግጥ ካቡጋ ከዋናዎቹ አንዱ ናቸው:: ለዚህም ነው በዓለማቀፉ የወንጀል ችሎት የስምምነት መርህ መሰረት ጉዳያቸውን በሩዋንዳ ችሎት መታየት የማይችለው:: የመንግሥታቱ ድርጅት ችሎት በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በታዋቂ ግለሰቦችና በንግድ ድርጅቶች አማካኝነት የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ይመረምራል::  የዘር ማጥፋት ወንጀሉን ያደራጁና ያመቻቹ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ማለቴ ነው::"

ምስል picture-alliance/AP Photo/R. Mazalan

የሩዋንዳ መንግሥት በዘር ማጥፋት ዕልቂቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራቸው በተባሉ ከ 1000 የሚልቁ ተጠርጣሪዎች ላይ በሰባት ከፍተኛ የወንጀል ክሶች የእስር ማዘዣ እንደተቆረጠባቸውና ከእነዚህም መካከል ቢዚማናና ሚራንያ እንደሚገኙበት ይፋ አድርጓል:: ዘ ሄግ በሚገኘው ዓለማቀፉ ፍርድቤት የሩዋንዳን ወንጀል የሚከታተሉት ዋና አቃቤ ህግ ሰርጌይ ብራሜርትዝ "የግለሰቡ በፖሊስ ታድኖ በቁጥጥር ስር መዋል በሀገራት መካከል ትብብር ካለ ወንጀል ፈፅመው የሚሸሸጉ ተጠርጣሪዎች የትም መደበቅ እንደማይችሉ ያመላከተ ነው" ሲሉ አስረድተዋል:: ፍርድ ቤቱ ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ውስጥ በ 33 አገራት ውስጥ ተሸሽገው በሚኖሩ ከ 1,100 በላይ ተጠርጣሪዎች ላይ የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ አውጥቶባቸዋል:: በሩዋንዳ የሚገኘው የፖሊስ ኃይልም ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ኃይል ጋር በቅንጅት በውጭ ሀገራት በነጻነት የሚኖሩ የቀድሞ ወንጀለኖችን ተከታትሎ ለፍርድ ለማቅረብ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ነው ብሏል የዶይቼ ቨለ ጋዜጠኛ ሙቩኒ:: እንደሱ ዕምነት ከሆነ አሁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች በአፍሪቃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በወንጀል ተፈላጊ ግለሰቦችም በአውሮጳ በስደት ተሸሽገው ይገኛሉ ነው ያለው::

" በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጠርጣሪዎች እንደ ዩጋንዳ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ማላዊ፣ ካሜሩን አልያም ዚምባብዌን በመሳሰሉ የአፍሪቃ ሀገራት ተሸሽገው ይገኛሉ:: ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በወንጀል ተፈላጊ ግለሰቦችም በአውሮጳ በተለይም በፈረንሳይ፣ ቤልጅየም፣ ኔዘርላንድ ወይም ጀርመን ውስጥ ማንነታቸውን ደብቀው ይኖራሉ

የሚል ዕምነት አለ"

ተጨማሪ ወነጀለኞች በቅርቡ በቁጥጥር ስር ይውሉ ይሆን?

ተጠርጣሪ ወንጀለኞቹ ለረጅም ጊዜያት ሳይያዙ ተደብቀው ሊኖሩ የሚችሉት እንዴት ነው? ለሚለው ጥያቄም ዘገባው ሲያብራራ "አብዛኛዎቹ ወንጀል ፈፃሚዎች ከፍተኛ ሃብት ስላላቸውና ከሚሸሸጉባቸው ሀገራት የመንግስት አመራሮች ጋርም የጠበቀ ግንኙነት ስለሚፈጥሩ ነው" ሲል ይፋ አድርጓል:: ከዚህ ሌላ ጉቦና ማማለያ ለሰዎች እንደሚሰጡ የሚገልፀው ጋዜጠኛ ሙቩኒ ከሟቹ የቀድሞ የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ጋር አንዳንዶቹ በቅርብ የተቆራኙ እንደነበሩ እናውቃለን ሲልም በምሳሌ ያብራራል::

የእነዚህ መንግሥታት የፀጥታ ኃይሎችም ወንጀለኞቹ ታድነው በዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ፊት እንዳይቀርቡ ጥበቃና ከለላ ያደርጉላቸዋል ብሏል:: በአውሮጳ ሀገራትም ቢሆን ፖሊስ እና የፍትህ አካላት ከአሁን ቀደም ወንጀለኞቹን ለህግ የማቅረቡን ጉዳይ ወደ ጎን ገሸሽ ያደረጉት ሲሆን በዓለማቀፉ ችሎት የሩዋንዳን ወንጀል ከሚከታተሉ መርማሪዎችም ጋር በበቂ ሁኔታ አልሰሩም የሚል ዕምነት እንዳለው ገልጿል፡፡ ሩዋንዳ በፈረንሳይ ተሸሽገው ይኖራሉ ተብለው የሚጠረጠሩ 30 ያህል የዘርማጥፋት ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ለዓለማቀፉ ችሎት ተላልፈው እንዲሰጡላት የፍርድ ቤት የማሰሪያ ትዕዛዝ ብትሰጥም እስካሁን በቂ ድጋፍ አለማግኘቷን የሩዋንዳው የፍትህ ሚኒስትር ጆንስቶን ቡሲንጌይም ለዶይቼ ቨለ ተናግረዋል ፡፡ ከነዚህም መካከል የቀድሞው ሟቹ ፕሬዝዳንት ሃብሪምማና ባለቤት አጌይት ሀብያሪማናና የመንግሥት ስራዎችና ኢነርጂ ሚኒስትር የነበሩት የሰንት ታዲንስጊምቫ ሪኪኪ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

 "በመረጃችን መሰረት የወንጀል ተጠርጣሪው ግለሰብ በተገኙበት እንዲያዙ በዓለማቀፉ ፍርድ ቤት የክስ ዋራንት ቢቆረጥባቸውም ላለፉት 25 ዓመታት በበርካታ የአውሮጳ ሀገራት በነፃነት ሲዘዋወሩ ነበር::በየትኛውም ሀገር ግን አልታሰሩም:: ፈረንሳይ አሁን ከእኛ ጋት መልካም ትብብር ማድረጓና ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ማዋሏ አስደስቶናል:: ግንኙነታችንን ወደ አዲስና የተሻለ ደረጃ ከፍ የሚያደርገውም  ነው:: ይህ መልዕክት ለመላው ዓለም ጥሩ የማንቂያ ደውል ነው::አሁንም ለሁሉም ሀገራት የተሸሸጉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ለፍርድ እንድናቀርባቸው አሳልፈው እንዲሰጡን ነው የምንጠይቀው:: "

ምስል DW/I. Mugabi

በፌሊሲዬን ካቡጋ ላይ የሚጀመረው የፍርድ ሂደት በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል የተሳተፉና የተባበሩ ሌሎች የተሸሸጉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ላይ የተጀመረውን የአደና ዘመቻ ያጠናክረዋል የሚል ዕምነት እንዳላቸው የዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ኔትዎርክ ፕሬዝዳንት ፓትሪክ ቦድዋም ተናግረዋል::"ይህ ጉዳይ ዓለማቀፉ የወንጀል ችሎት ከአሁን ቀደም ያወጣቸውን የእስር ማዘዣዎች ዳግም ለማስፈፀም ያግዛል::  ዓለማቀፍ የህግ መርሆች ተፈፃሚነትም እንደገና መነቃቃት ይጀምራል" ነው ያሉት ቦድዋ::የሩዋንዳው የዶይቼ ቨለ ዘጋቢ ሙቩኒም " አንድ ነገር ግልፅ መሆን ያለበት በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ ብቻ በሩዋንዳው የወንጀል ድርጊት በተሳተፉና በተባበሩ ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራውና ክትትሉ ተጠናክሮ ቀጥሏል::" ብሏል::ተጠርጣሪው ግለሰብ በፈረንሳይ ተገቢው ምርመራ ተደርጎላቸው እንዳበቃ የሩዋንዳን የዘር ማጥፋት ወንጀል ወደሚከታተለው ዓለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ተላልፈው በዛው የፍርድ ሂደቱ የሚቀጥል ይሆናል::

በርካታ ሩዋንዳውያን በዘር ማጥፋት ወንጀሉ የተጠረጠሩ ሁሉ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ ይፈልጋሉ:: ማንም ሆነ ማን ጥፋተኛ እስከሆነ ድረስ ህጋዊ ፍርድ እና ተመጣጣኝ ቅጣት ማግኘት አለበት ነው የሚሉት:: በህግ ሊጠየቁ የሚገባቸው ወንጀለኞች እንዳሻቸው ተሸሽገው እንዲኖሩ አይፈቅዱም::በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ከፍተኛ ሚና ነበራቸው የሚባሉትና የዕልቂት አንዱ ጠንሳሽ ፌሊሲዬን ካቡጋ ከ 26 ዓመታት ሽሽት በኋላ በዓለማቀፉ ማህበረስብ ትብብር ታድኖ ለፍርድ መቅረብ በዓለም ዙሪያ ፣በወደፊቷ አፍሪቃም ሆነ በየሀገራቱ የዘር ፍጅት እና የሰው ልጅ ላይ አስፈሪ ሰቆቃ ለሚፈፅሙ አምባገነኖችና ወንጀለኞች ሁሉ አስተማሪና ጥሩ የማንቂያ ደውል ሆኖ ተቆጥሯል::

ሲሊቫኑስ ኬርሜራ

ኤሪክ ቱፖና

እንዳልካቸው ፈቃደ

ታምራት ዲንሳ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW