የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ የእንኳን አደረሳችሁ መልክት
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 17 2015
ማስታወቂያ
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በየዓመቱ በሚያሰሙት በገና በዓል በባሕላዊ ንግግርራቸዉ ላይ በዩክሬን እየተካሄደ ያለዉ ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ። ከሁለት ዓመት የኮቪድ እገዳ በኋላ የ 86 ዓመቱ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበዉ ህዝብ በትናንትዉ እለት ባደረጉት ንግግር በስቃይ ላይ ያሉትን ሁሉ ለማገዝ አንድነት እንዲጠናከር፤ የጦር መሳሪያ ነጎድጓድ ድምፅ ዝም እንዲል፤ ይህን ትርጉም የለሽ ጦርነት በአፋጣኝ ለማስቆም ፈጣሪ ኃይል ያላቸውን ሰዎች አዕምሮ እንዲበራ ሲሉ ፀሎት አሰምተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በዩክሬን ያለው ጦርነት በሶርያ፣ በምያንማርን፣ በኢራን፣ በሄይቲ እና በአፍሪቃ ሳህል ክልልን ጨምሮ በሌሎች ቦታዎች በተከሰቱ ግጭቶች ለተጎዱ ሰዎች ያለው ስጋት መቀነስ እንደሌለበት ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በእስራኤላውያን እና በፍልስጤማውያን መካከል ያለዉን ግጭት ለማብረድ ውይይት እንዲደረግ ጠይቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አሁን ያለንበት ወቅት ከባድ የሰላም ረሃብ እየገጠመን ጊዜ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ