የሮማው ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ሲታወሱ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 13 2017
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ-ሊቀነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ዛሬ ጠዋት በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በአጸደ ሥጋ ተለዩ።
ርዕሠ ሊቀነ ጳጳስ ፍራንሲስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2021 ጀምሮ በተለያዩ ሕመሞች ሲሰቃዮ የነበረ ሲሆን በተለይ በዘንድሮዎ ዓመት ለረዥም ጊዜ በሆስፒታል ተኝተው በሕክምና ሲረዱ ቆይተዋል።
ይሁንና ፍራንሲስ ትላን የትንሳኤ በዓልን አስመልክተው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይብቅ ብለው ለእምነቱ ተከታዮች መልካም ትንሳኤ የሚል አጭር መልዕክት አስተላልፈዋል። በሕመም ላይ የሰነበቱት ፍራንሲስ ወንበር ላይ ተቀምጠው በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት "ያለ የእምነት ነጻነት፣ የአስተሳሰብ ነጻነት እና ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት እንዲሁም የሌሎችን አመለካከት ከማክበር ውጪ ሰላም አይኖርም" ብለዋል። የ88 ዓመቱ ፍራንሲስ "አሳሳቢ" ያሉትን ጸረ-ሴማዊነት እና የጋዛን አሳዛኝ እልቂት አውግዘዋልም።
የሊቃጳጳሱ ሞትን ተከትሉ የተለያዩ ኃይማኖት ተቋማት፣ መንግስታት፣ ድርጅቶችና ማሕበራት የሐዘን መልዕክታቸውን እያስተላለፉ ሲሆን የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ «ዓለማችን ታላቅ ሰው አጣች» ሲሉ የሐዘን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ፍራንስሲ ቤተ ክርስቲያኗን በመምራት የመጀመሪያው ደቡብ አሜሪካዊ እና ኢየሱሳዊ ነበሩ። ፍራንሲስ የሚለውን ስማቸውንም አንድም የቤተ ክርስቲያን መሪ ከዚህ በፊት ተጠርቶበት አያውቅም።
ስማቸው የስነ-ምህዳር እና የእንስሳት ጠባቂ ተብሎ በቤተክርስቲያኗ የሚታወቀውን የአሲሲውን ቅዱስ ፍራንሲስን የሚያስታውስ ነው። በቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ ቅዱስ ፍራንሲስ የሀብታም ነጋዴ ልጅ የነበረና በኃላ ግን ሀብቱን ሁሉ ትቶ፣ በፍፁም ድህነት ኢየሱስን የተከተለ እና ፍራንቸስኮ የሚባል ሥርዓት የመሰረተ ነው። የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳሱ ስም በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በቤተ መንግሥት ብዙም ግርማ ሞገስ ያለው አልነበረም።
በጎርጎሪያኑ 2013 ርዕሰ ሊቃነጳጳስ ሆነው የተመረጡት አርጀንቲናዊው የቀድሞው ጆርጅ ማሪዮ ቤርጎሊዮ የአሁኑ ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ ፤ለስደተኞች እና ቤት ለሌላቸው ሰዎች በመቆም እንዲሁም ለአየር ንብረት እና ለአካባቢ ጥበቃ ይታገሉ ነበር።
የጳጳሱ የመጀመሪያ ጉብኝት
በጎርጎሪያኑ መጋቢት 2013 ከሊቀ ጳጳሱ ምርጫ በፊት፣ በቅድመ-ጉባኤው ላይ፣ ካርዲናሎቹ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁኔታ አስተያየቶችን በተለዋወጡበት ጉባኤ ላይ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ “በድፍረት የመናገር ነፃነት” እንዲሰፍን ጠይቀዋል።
በ 2013 ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋዊ ስራ ሲጀምሩ እራሳቸውን ከ‹‹ከምድር ዳርቻ›› ብለው የገለፁት ጳጳሱ የመጀመሪያ ይፋዊ ስራቸው በማኅበረሰብ ዘንድ የተገለሉትን መጎብኘት ነበር።
ይህ ሁሉ ከባህሪያቸው ጋር የሚስማማ ነበር። ጳጻሱ ከቀደምቶቹ መሪዎች በተለየ ከቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከፍ ብሎ በሚገኘው ሐዋርያዊ ቤተ መንግሥት ወደሚባለው ቦታ አልሄዱም። ይልቁንም በጵጵስና ዘመናቸው በሙሉ በቫቲካን የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ በሁለት ክፍሎች ውስጥ ከሰራተኞች እና እንግዶች ጋር ነበር የኖሩት።
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ዓለማቀፋዊነትን እና ካፒታሊዝምን ደጋግመው በመተቸት ጠንካራ የፖለቲካ ንግግር አድርገዋል።ይህም ለድሆች እና ለደቡባዊው የዓለም ክፍል ጠበቃ ሆነው እንዲታዩ አድርጓቸዋል።በጎርጎሪያኑ 2014ም ስደተኞችን በተመለከተ የአውሮፓ ኅብረትን ተችተዋል።
«በተጨማሪም የስደትን ችግር በጋራ መፍታት አስፈላጊ ነው። የሜዲትራኒያን ባህር ትልቅ የመቃብር ቦታ መሆኑን አልተቀበልንም። በየቀኑ በአውሮፓ የባህር ዳርቻዎች በሚያርፉ ጀልባዎች ላይ መጠለያ እና እርዳታ የሚፈልጉ ወንዶች እና ሴቶች አሉ።በአውሮፓ ህብረት ውስጥ የጋራ መደጋገፍ አለመኖር የስደተኞችን ሰብዓዊ ክብር የጉልበት ብዝበዛ እና የማያቋርጥ ማህበራዊ ውጥረትን ለመሳሰሉ ግምት ውስጥ ላልገቡ ችግሮች የተለዬ መፍትሄ ያለመስጠት አደጋ ላይ ይጥላል።»
ፍራንሲስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን ማሻሻያዎችን እንዲተገብር እና በልማት ዕርዳታ እና በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ የበለጠ እንዲሰራ ወትውተዋል።
በጎርጎሪያኑ በ2015ም በኒውዮርክ በዩኤስ ኮንግረስ እና በተባበሩት መንግስታት ፊት ባደረጉበት ንግግር የስደተኞችን ቀውስ አጉልተዋል።
«ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ማግለል የሰው ልጅ ወንድማማችነትን ሙሉ በሙሉ መካድ እና በሰብዓዊ መብቶች እና በአካባቢ ላይ በጣም ከባድ ጥቃት ነው። በሦስት ከባድ ምክንያቶች በእነዚህ ጥቃቶች በጣም የሚጎዱት ድሆች ናቸው። በህብረተሰቡ የተገለሉ፣ በተጣለ ምግብ ለመኖር የተገደዱ እና የአካባቢ ብክለት በሚያስከትለው መዘዝ ያለ አግባብ የሚሰቃዩ ናቸው። እነዚህ ክስተቶች ዛሬ በጣም የተስፋፋውን "የመጣል ባህል" ሳያውቁት ይመሰርታሉ።»
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ክስተት እና የቆሙለት ነገር ለእሳቸው እንግዳ ሆኖ ቆይቷል ። ፍራንሲስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን ማሻሻያዎችን እንዲተገብር እና በልማት ዕርዳታ እና በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ የበለጠ እንዲሰራ ጠይቀዋል።
በማኅብረሰቡ የተገፉትን ጉብኝት
ቻይና እና ሩሲያ በጳጳሱ የ12 ዓመት አገልግሎት ያልተጎበኙ ቦታዎች ቢሆንም ፤ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በህይወት ዘመናቸው 47 የውጪ ጉዞዎችን አድርገዋል።ወደ እስያ፣ አፍሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ባደረጉጓቸው ጉዞዎች ጳጳሱ ሁል ጊዜ ድሆችን የሚፈልጉ እና በድሆች መንደር በመግባት ሰዎች ወደ እሳቸው እንዲቀርቡ ይጋብዙ ነበር። በአውሮፓ ውስጥ ባደረጓቸው ጉዞዎችም ቢሆን ብዙውን ጊዜ የሚጎበኙት በሀብታሙ አህጉር የሚኖሩ ድሆችን ነበር።
ፍራንሲስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፈጣን ማሻሻያዎችን እንዲተገብር እና በልማት ዕርዳታ እና በአየር ንብረት ጥበቃ ረገድ የበለጠ እንዲሰራ ወትውተዋል።
በሌላ በኩል ከእሳቸው በፊት፣ የቫቲካን ሲኖዶስ፣ እስከ አራት ሳምንታት የሚቆዩ ዋና ዋና ክርክሮች፣ የተዘጋጁ የእጅ ጽሑፎች የሚነበቡባቸው አሰልቺ ስብሰባዎች የነበሩ ሲሆን፤ እሳቸው ግን ግልፅ ውይይት እንዲሰፍን ግፊት አድርገዋል።
በዚህም በእሳቸው ዘመን በቤተክስርስቲያኒቱ ውስጥ ሰዎች እንዲነጋገሩ እና እንዲከራከሩ መንገድ ከፍተዋል። ነገር ግን ብዙ ታዛቢዎች በጥቅምት 2024 በተካሄደው እና የቤተ ክርስቲያኗን የወደፊት ሁኔታ ለመቅረጽ ይረዳል ከተባለው ከዓለም ሲኖዶስ ማጠናቀቂያ በኋላ እንኳ ተጨባጭ ለውጦች አልታዩም ሲሉ ይተቻሉ።
ፍራንሲስ በአንድ ወቅት እንደተናገረሩት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ "እረፍት ማጣት" በመኖሩ የአስተምህሮ ሕንጻ ማስፋት እና ማስዋብ የእርሳቸው ስራ አለመሆኑን ገልፀዋል።
በ2023 ተግባራዊ በሆነው እና የጳጳሱን መንግሥት የቫቲካን አስተዳደር አካል የሆነውን የኩሪያ ታሀድሶም አድርገዋል። በሕይወታቸው መገባደጃ ፣ በተለምዶ ለካርዲናሎች ተብለው በተዘጋጁት «ዲካስቴሪ»ተብለው በሚታወቁት የቫቲካን ሚንስተሮች ባልተለመደ ሁኔታ ሁለት መነኮሳትን ሾመዋል።
ፍራንሲስ በአገልግሎት ዘመናቸው በሙሉ በቫቲካን ውስጥ ያለውን ሴራ እና ጥላቻ እንዲሁም በብዙ የቤተክርስቲያኗ ክፍሎች የተፈጸመውን የጾታዊ ጥቃት በደሎችን አይታገሱም ነበር። በዚህም በአንዳንድ ውሳኔዎቻቸው ብዙ ሰዎችን አሳዝነዋል። በመጨረሻዎቹ ዓመታት በዓለም ዙሪያ በርካታ ጳጳሳትን ከስልጣን ቢያነሱም፤ ወጥነት ያለው ውሳኔዎችን አልወሰዱም በሚል ይተቻሉ።ምክንያቱም በዙሪያቸው ባሉ እና ወንጀለኞች ናቸው በተባሉት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ለእሳቸው አስቸጋሪ መስሎ ታይቷል።
ቀረቤታ ከአይሁዶችን እና ሙስሊሞች ጋር
እራሳቸውን “ወንድም ኤጲስ ቆጶስ” ብለው ማስተዋወቅ የሚወዱት ፍራንሲስከሚታወሱባቸው ጉዳዮች መካከል ከአይሁዶች እና ከሙስሊሞች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ያደረጉት ሙከራ ነው።ይህ የጳጳሱ አዲስ አቀራረብም እስካሁን ከነበሩት የቤተክርስቲያኗ መሪዎች በተለዬ ሁኔታ እንዲታወሱ ያደርጋቸዋል።.
የአረብን ባሕረ ገብ መሬት የጎበኙ የመጀመሪያው ጳጳስ ሲሆኑ፤በጎርጎሪያኑ 2019 በአቡ ዳቢ ከሙስሊም መሪዎች እና ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ጋር “በሰው ልጅ ወንድማማችነት ፣ በዓለም ሰላም እና በአንድነት መኖር” ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ሰነድ ተፈራርመዋል። በ2021 ደግሞ ውይይት እና ሃይማኖታዊ ወንድማማችነትን ለማስተዋወቅ ኢራቅ ውስጥ ያሉትን ሺዓዎች ጎበኝተዋል። በዚህ የአገልግሎት ዘመናቸውም ከእስልምና ጋር ያላቸው ግንኙነት ይበልጥ እየጠነከረ መጥቶ ነበር።
ምንም እንኳ በጋዛ የደረሰውን የሰላማዊ ሰዎች ጥቃትን በመተቸታቸው ከአንዳንድ የአይሁዳውያን ጋር የነበራቸው ግንኙነት መበላሸት ቢጀምርም፤ በጎርጎሪያኑ ጥቅምት 2023 በታጣቂ እስላማዊው ቡድን ሃማስ የተፈፀመውን ጥቃት በፍጥነት አውግዘዋል። በኋላም የእስራኤል ታጋቾች እንዲፈቱ ደጋግመው ጠይቀዋል።በጋዛ በሚገኙት አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የክርስቲያኖች ላይ ተፈፀመ ባሉት ጥቃትም እስራኤልን ክፉኛ አውግዘዋል።
የጤና እክሎች ከ2021 ጀምሮ
ርዕሰ ሊቃነጳጳስ ፍራንሲስ ከጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ የጤና ችግሮች እየተሰቃዩ የቆዩ ሲሆን፤ በ2022ም ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ፊት በተሽከርካሪ ወንበር ተቀምጠው ታይተዋል።
በዚህ ሁኔታ የጤናቸው እክል እየጨመረ በመምጣቱ ከአደባባይ አገልግሎት ርቀው ቆይተዋል።ያም ሆኖ በታህሳስ 2024 እሳቸው የከፈቱት በካቶሊክ እምነት በየሩብ ምዕተ-ዓመቱ አንድ ጊዜ የሚከበረው ቅዱስ ዓመት ለልባቸው ቅርብ ሆኖ ቀርቷል።
266ኛው የሮም ሊቀ ጳጳስ ሆነው ቢተክርስቲያኗን ለ12 ዓመታት ያህል ያገለገሉት ፍራንሲስ በጎርጎሪያኑ ታህሳስ 17 ቀን 1936 የተወለዱት ሲሆን፤በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል
በ12 ዓመታት የፍራንሲስ የጵጵስና ዘመን፣ ዓለም ይበልጥ የተከፋፈለ እና በግጭት የተሞላ ይመስላል።እናም ጳጳሱ የማስጠንቀቂያ ድምጽ ሆነው ቆይተዋል። ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በጎርጎሪያኑ 2020 ተከስቶ በነበረው የኮቪድ ወረርሽኝ ሳቢያ የፋሲካ በዓልን በጨለማ እና በዝናብ ብቻቸውን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ያከበሩበት እና ለዓለም ስቃይ አምላካቸውን የተማፀኑበት ከአይረሴ ስራዎቻቸው ውስጥ አንዱ ነው።
ፀሀይ ጫኔ
ዮሃንስ ገብረ እግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ