1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላማዊ ሰዎች ግድያ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 25 2016

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በተከታታይ በተፈጸመ እና ንጹሃን ላይ ያነጣጠረ ግድያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 40 መድረሱን የአይን እማኞች ለዶቼ ቬለ ተናገሩ። የአይን እማኞቹ በሰጡን አስተያየት ከህዳር 13 ጀምሮ - ህዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በተለያዩ ቦታዎች በተፈጸመው ግድያ ህጻናትና አዛውንቶችም ጭምር የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል።

የአስፋልት መንገድ
በአከባቢው የተፈጸመውን ሰሞነኛውን አሰቃቂ ድርጊት ተመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የአከባቢው ነዋሪ፤ ነገሩ ህዝቡን ወደ ፍርሃት የከተተ ብለውታል፡፡ምስል Seyoum Getu/DW

የሰላማዊ ሰዎች ግድያ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ

This browser does not support the audio element.

ሰኞ ጠዋት በአምስት ሰዎች ላይ የተፈጸመን ግድያ ጨምሮ በአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ በተከታታይነት በተለያዩ ቀናት እና ስፍራዎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ አነጣጥሮ በተፈጸመ ግድያ በርካቶች መጎዳታቸው ተነግሯል፡፡ ዘመድ እንደተገደለባቸው ገልጸው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ያጋሩት አንድ የአከባቢው ነዋሪ እንደሚሉት ግድያው በተለያዩ ቀናት የተፈጸመ ነው፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት እኚህ አስተያየት ሰጪ ግድያው ከህጻን እስከ ሽማግሌ ያልለየ ብለውታልም፡፡  

እገታ፣ግድያና ሁከት በኦሮሚያ ክልል

በተከታታይነት ተፈጽሞ ከ40 ሰዎች በላይ ቀጥፏል የተባለው ይህ የሽርካው ጥቃት ሾሌ ዲገሉ በተባለ ቀበሌ ቶሌ መድሃኒዓለም በሚባል ስፍራ ህዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት 1፡00 ገደማ በተፈጸመ ጥቃት 17 ሰዎች መገደላቸውን የአይን እማኙ አስረድተዋል፡፡ “17ቱ የሞቱት ቶሌ መድሃኒዓለም ይባላል አጥቢያ ቦታው፡፡ ከዚያን ፊጤ በሚባል ቦታ ደግሞ 8 ሰዎች ተገደሉ፡፡ እንደገና ደግሞ ለቡ ሴሩ በሚባል ስፍራ 10 ሰው ተገድለዋል” ብለዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው 8 ሰዎች እና 10 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃቱ ደግሞ ህዳር 17 ቀን 2016 ዓ.ም. የተፈጸመ ነው፡፡ ግድያው ቀጥሎ ትናት ሰኞ ጠዋትም 1፡00 ሰዓት ላይ ጢጆ በምትባል ስፍራ አምስት ሰዎች ጎቤሳ የሚባል የወረዳው ከተማ አድረው ወደ ገጠር ቀየያቸው ሲጓዙ መገደላቸውን አመልክተዋል፡፡ አስተያየት ሰጪው ግድያውን የሚፈጽሙት የታጠቁ አካላት ነው ከማለት ውጪ ማንነታቸውን አላብራሩም፡፡  

ለተፈጸመው ግድያ አነሳሽ ምክንያት ኖረው ይሆን? 

ገዳዮቹ ሰላማዊ ሰዎቹን ሲገድሉ የሚጠይቁትና የሚያቀርቡላቸው ምክንያትም እንዳልነበረ የአይን እማኙ ተናግረዋል፡፡ “ያው እንዲሁ ገብተው ነው የገደሏቸው፡፡ ምንም ምክኒያት የላቸውም፡፡ አሁን የስምንቱ ማታ አንድ ሰዓት ከ08 ደቂቃ ልጁ ከብት ሲያስር ቤተሰብ ጥራ ካሉት በኋላ ነው አሰልፈው ገድለዋቸው ያለፉት፡፡ አባትና እናቱ ሽማግሌ ናቸው፡፡ ሁለት ህጻናትም ነበሩ፡፡ አንድ የስምንት ዓመት ታዳጊ ታፋዋ ላይ ተመታ ተርፋ ሆስፒታል ገብታለች፡፡ የሰባት ወር ህጻን እዛው አስከሬን ላይ ስታለቅስ ነው ያደረችው፡፡ አንድ አባት ከነባለቤቱ እና ሁለት ልጆቹ አልፈዋል፡፡ ወንድምየው ግን እንደምንም በአጥር ዘሎ በማምለት ህይወቱን አትርፏል” ሲሉ አስተያየታቸውን አብራርተዋል፡፡ 

ግድያው የፈጠረው አለመረጋጋት 

በአርሲ ዞን ሺርካ ወረዳ ሃይማኖት ላይ አነጣጥሮ ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች፡፡   ምስል Seyoum Getu/DW

የአይን እማኝ አስተያየት ሰጪው በጅምላ የተገደሉቱ ሰላማዊ ዜጎች እና በብዛት የአንድ ቤተሰብ አባላትም ናቸው ብለዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ንጹሃኑ ላይ ተኩሰው እንደገደሉዋቸውም አመልክተዋል፡፡ 

በአከባቢው የተፈጸመውን ሰሞነኛውን አሰቃቂ ድርጊት ተመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የአከባቢው ነዋሪ፤ ነገሩ ህዝቡን ወደ ፍርሃት የከተተ ብለውታል፡፡ “ህዝቡ በፍርሃት ነው ያለው፡፡ የሁለት ኣመት እና ነፍስጡር ሳይቀር ነው ያለቁ፡፡ ሰው የጭካኔ ትግ ላይ ደርሷል የሚስብል የሚዘገንን ነው የተፈጸመው፡፡ ያው አሁን ሰው እየለቀቀ ወደሚቀርበው ከተማ እየሸሸ ነው፡፡ በርግጥ የመንግስት ሃይል መከላከያን ጨምሮ አሁን በአከባቢው ተሰማርቶ ህዝቡን እያረጋጋ ነው፡፡ ግን ሰው በአዕምሮም ተጎድተዋል” ይላሉ፡፡ 

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ጨምሮ በተከታታይ በአርሲ ዞን ሺርካ ወረዳ ሃይማኖት ላይ አነጣጥሮ ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት ቢያንስ 36 ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ህዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች፡፡   

ስለግድያው ባለስልጣናት ምን ይላሉ? 

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአርሲ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮሚሽነር አዳሙ አባተ ግድያ መፈጸሙን በማረጋገጥ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እያዋለ የምርመራ ሂደት ላይ ይገኛል በማለት ዝርዝር መረጃዎችን ሳይናገሩ ቀርተዋል፡፡ “አሁን ጉዳዩን እያጣራን በምርመራ ላይ ስለሆንን በዚህ ላይ መግለጫ መስጠት አልችልም፡፡ አሁን እያጣራን ስለሆነ ማብራሪያ መስጠት አልችልም ብያለሁ፡፡ ወንጀሉን በመስራት የተጠረጠሩ በርካቶችን ቁጥጥር ስር እያዋልን ነው፡፡ ግድያው ተፈጽሟል፡፡ ለዚያም ነው መርመራን የምናደርገው፡አሁን ተጠርጣሪዎቹን ቁጥጥር ስር በምናውልበት ወቅት መግለጫ መስጠት ሂደቱን ስለሚያደናቅፍ ነው” ብለዋል፡፡ 

ዶይቼ ቬሌ ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ብደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡ ኃላፊው ከሰሞኑ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ማብራሪያ በሺርካ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው፤ ለተፈጸመው ወንጀልም “ሸነ” ያሉት እና እራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራት” ብሎ የሚጠራን ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ ለመገናኛ ብዙሃን የተናገሩት የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በፊናቸው ታጣቂዎቻቸው ይህን እርምጃ እንዳልወሰዱ በመግለጽ ክሱን አስተባብለዋል፡፡  

የአርሲ ዞኑ ሺርካ ወረዳ በርካታ የክርስትና እና እስልማና ሃይማኖት ተከታዮች የሚኖሩበት ነው፡፡ በቅርቡ በታንዛንያ ሲካሄድ ቆይቶ የተደናቀፈው የመንግስት እና ታጣቂዎች ሰላማዊ ድርድር ተከትሎ በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች አለመረጋጋቱ ስለመቀጠሉም ይነገራል፡፡ 
ሥዩም ጌቱ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW