1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላምና የእርቅ ውትወታዎች ለምን ውጤት አልባ ሆኑ?

ዓርብ፣ መጋቢት 13 2016

ከመንግስት ጋር ትጥቅ አንስተው ከሚፋለሙ ኃይሎች ጋር እርቅ እንዲወርድ "ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ" የሚል ሀሳብ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ አስታወቀ። ከዓመት በፊት 35 ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሰላም መድረክ እንዲመቻችና አጥፊዎች የሚዳኙበት መድረክ እንዲፈጠር ጠይቀዉ ነበር።

አንድነት ፓርክ በአዲስ አበባ ከተማ
አንድነት ፓርክ በአዲስ አበባ ከተማ ምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

የሰላምና የእርቅ ውትወታዎች ለምን ውጤት አልባ ሆኑ?

This browser does not support the audio element.

የሰላምና የእርቅ ውትወታዎች ለምን ውጤት አልባ ሆኑ? 

በመንግስት እና ከመንግስት ጋር ትጥቅ አንስተው በሚፋለሙ ኃይሎች መካከል እርቅ እንዲወርድ ለማድረግ "ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ" የሚል ሀሳብ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ አስታወቀ። ከዓመት በፊት 35 ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አገር አቀፍ "የሰላም መድረክ እንዲመቻች እና አጥፊዎች የሚዳኙበት ገለልተኛ ምርመራ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን" ሲሉ በሕብረት ቢጠይቁም ጥሪያቸው ምላሽ ያገኘ አይመስለም። ለመሆኑ በፖለቲካ ፓርቲዎች በሲቪክ ድርጅቶች፣ በግለሰቦች፣ በውጪ መንግሥታትና ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ፣ ጦርነት እንዲቆም፣ አንድነትና ትብብር እንዲጠናከር የሚቀርቡ ጥሪዎች እና ውትወታዎች ለምን መፍትሔ አልባ ፣ ሰሚ የለሽ ሆኑ ? 

 

"ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ" የሚል ጥሪ ቀረበ 

ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ በኢትዮጵያ ያሉ "የእርስ በርስ ግጭቶችን ለማስቆም" ያዘጋጀውን የእርቅ እና የሰላም ሀሳብ በተመለከተ የፓርቲውን ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብዱልቃድር አደምን ጠይቀናቸዋል። "ግጭቶች አሉ። በእነዚህ ግጭቶች ምክንያት የሰው ሕይወት ይጠፋል፣ ንብረት ይወድማል። ዜጎች ከቦታቸው ይፈናቀላሉ። እና በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው ሀገራችን። የዚህ እንቅስቃሴ አላማው በመንግሥት እና በትጥቅ ወይም ነፍጥ አንስተው ከመንግሥት ጋር እየታገሉ ፣ እየተዋጉ ያሉ ወገኖችን እንዲታረቁና ሀገራችን ላይ ሰላም እንዲመጣ" ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥሪዎችና ውጤታቸው ምንና ምን ናቸው? 
 

ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በልዩ ልዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ ሀገራትና መንግሥታት የሰላም ጥሪሳይቀርብ የቀረበት ጊዜ የለም። 35 አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች "የኢዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ" በሚል ከዓመት በፊት አገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲመቻች ገለልተኛ ምርመራ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ቢጠይቁም መፍትሔው ግን ርቋል። ከእነዚህ የሲቪክ ድርጅቶች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ይገኝበታል። የጥሪያችሁ ውጤት ምን ላይ ደረሰ የሚለውን የተቋሙን ኃላፊ አቶ ያሬድ ኃይለማርያምን ጠይቀናል።

አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

"ያደረግናቸው ጥሪዎች ሁሉ አሁንም ቢሆን መልስ አላገኙም። ጦርነቱ እንዲያውም ተባብሶ በአማራ ክልልም፣ በኦሮሚያም ግጭቶች ተባብሰው ብዙ ሰው እየተጎዳ ነው" ብለዋል። 

የሰላም ጥሪ አቅራቢ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች  "የታመቁ ቅራኔዎች ወደ ነውጥ እንዳይሸጋገሩ ለመከላከል፣ ነውጥ አዘል ግጭቶች በሰላማዊ ንግግሮች እንዲፈቱ እና የሰላም ጅምሮች ሁሉን አካታች እና ዘላቂ እንዲሆኑ" በማለት ጠይቀው ነበር። እውነታው ግን ጦርነት አሁንም ሀገርን እየበላ ይገኛል። ዜጎች እርስ በርስ እየተዋጉ ፣ ኢኮኖሚ እየደቀቀ ይገኛል። እነዚህ ጥሪዎች ለምን መፍትሔ አጡ ? አቶ ያሬድ "እኔ እንደሚገባኝ የመንግሥትን ቁርጠኝነት ነው የሚፈልገው" 

ለኢትዮጵያ ሰላም ዘላቂው መፍትሔው ምን ይሆን ? 
 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር ) ከዚህ በፊት ላቀረብንላቸው መሰል ጥያቄዎች "ኢትዮጵያ ውስጥ ከፖለቲካ ፍላጎት የሚመነጩ ቀውሶች ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፣ ለዘላቂ መፍትሔውም ይህ እጅግ አስፈላጊ ነው" ብለው ነበር። ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ችግሩ እየተባባሰ ዝም አንልም በሚል አዲስ የእርቅ ሀሳብ አቅርቧል። "የዜጎች ሕይወት እየጠፋ፣ ሀገር እየፈረሰ ቁጭ ማለት ተገቢ ነው ብለን አናስብም። ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ የእርቅ ጥሪውን በዋናነት ወደ መንግሥት በሀገር ሽማግሌዎች በኩል ይዞ እንደሚሄድ ገልጿል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቆም፣ ግጭትና ጥላቻ እንዲወገድ፣ ሰላም እንዲሰፍን፣ እኩልነትና ፍትሓዊነት እንዲሰፍን እና አንድነት እንዲጠናከር የሚቀርቡ ጥሪዎች ለምን ውጤት አልባ፣ ሰሚም ያጡ ሆኑ ?  

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW