1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ማስከበርና የባሕር በር እያነቃነቁት ያለው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ

ሰለሞን ሙጬ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 21 2017

"አሁን የኢትዮጵያ አትሳተፊም መባል ብቻ አይደለም ጉዳዩን ውስብስብ ያደረገው። ተፃራሪ የሆነችው ግብጽ ደግሞ እንደምትሳተፍበት መታመኑ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ያላትን የተቀባይነት ደረጃ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል" ተንታኝ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከጂቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦመር ጊሌ ጋር ትናንት ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከጂቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦመር ጊሌ ጋር ትናንት ተወያይተዋል።ምስል Solomon Muche/DW

የሰላም ማስከበርና የባሕር በር እያነቃነቁት ያለው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ

This browser does not support the audio element.

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉት ሀገራት በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ምክንያት አሰላለፋቸው ሲለዋወጥ እየተስተዋለ ነው።

ጉዳዮቹ ራሱን ችሎ መቆም ያልቻለውን የሶማሊያን መንግሥት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቁ ዓለም አቀፍ ተልዕኮ እና የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄ እና ይዞት የመጣው ተጓዳኝ ስበት ናቸው።

በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ የግብጽ ጉልህ ተሳታፊ ሆኖ ብቅ ማለት ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው የመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ጋር ተዳምሮ በቀጣናው ያላት አወንታዊ ተፅዕኖ ላይ ጫናዎች እንዲመጡባት አድርጓል።

ለመሆኑ ሰሞነኛው የዚህ አካባቢ ሁናቴ ምን ምልክ ይዟል? የዘርፉን ተንታኞች አነጋግረናል።

የግብጽ የአካባቢው ጉዳይ ላይ መግባት ያስከተለው ለውጥ

ምንም እንኳን ሱዳንም፣ ኢትዮጵያም ውስጥ ጦርነቶች ቢኖሩም የአካባቢው ዐበይት ጉዳዮች ሆነው የሚታዩት ቀጣናዊ ጉዳዮች የተባበሩት መንግሥታት ይሁንታ የሰጠው የአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ የሰላም ማስከበር ስምሪት እና የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳዮች የላቁ ትኩረት ሳቢ ጉዳዮች ናቸው።

ሶማሊያ ከሉዓላዊነቷ ጋር በተገናኘ ከኢትዮጵያ ጋር ለአንድ ዓመት ግድም የቆየችበትን ብርቱ ውዝግብ አንካራ ውስጥ በመፍታት የስምምነት ውል ብትፈርምም ኢትዮጵያ ለዓመታት መልካም ተግባር ፈጽማበታለች በሚባለው የሰላም ማስከበር ተግባሯ እንዳትቀጥል አሁንም በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የመቃወም ዝንባሌ ማሳየቷ ተስተውሏል። 

በአንፃሩ የግብጽ ወደዚህ ኃላፊነት የመግባት ሁኔታ ኢትዮጵያ እዚያ ባሉት ቋሚ መልዕክተኛዋ በኩል ሶማሊያ ውስጥ ሽብርተኝነትን በመዋጋት እና «በቀጣናው ገንቢ ሚና የሌላቸው» ያለቻቸው አካላት ግዴለሽ ጥረታቸውን እንዲያስቀሩ ሊመከሩ ይገባል የሚል መልዕክት አስተላልፋለች።

የግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ መግባት በአካባቢው ሀገራት ዘንድ ትብብር እና መተማመንን መቀነሱን ይነገራል።ምስል WHA/picture alliance

የግብፅ በእነዚህ ሁለት ጉዳዮች ላይ መግባት በአካባቢው ሀገራት ዘንድ ትብብር እና መተማመንን መቀነሱን በውጭ እና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ምርምር የሚያደርጉት ዶክተር ወርቁ ያዕቆብ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

"የግብጽ እንቅስቃሴ በሕብረት መንፈስ ሲተባበሩ የነበሩ ሀገሮችን [ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ] የማሻከር አይነት እንደምታ ያለው ነገር እንዲታይ አድርጓል"።

ኢትዮጵያ በአዲሱ የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ካልተሳተፈች ጉልህ ጥያቄዎችን ያስነሳል - ተንታኝ

ሌላኛው የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ እንደሚሉት እነዚህ ሁለት ጉዳዮች "በአንድ ወይም በሌላ ተያያዥነት ያላቸው መሠረታዊ ሁኔታዎች" ናቸው። ኢትዮጵያ ነገ የሚጠናቀቀውን አትሚስ የተባለው የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በሚተካው ማዕቀፍ ውስጥ ካልተሳተፈች ጉልህ ጥያቄዎችን ያስነሳልም ብለዋል።

 "አሁን የኢትዮጵያ አትሳተፊም መባል ብቻ አይደለም ጉዳዩን ውስብስብ ያደረገው። ተፃራሪ የሆነችው ግብጽ ደግሞ እንደምትሳተፍበት መታመኑ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ያላትን የተቀባይነት ደረጃ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል"። ብለዋል።

የሶማሊያ አጋር የማብዛት እንቅስቃሴ 

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማሕሙድ ሰሞኑን ወደ አስመራ፣ ትናንት ደግሞ ወደ ጅቡቲ ተጉዘዋል። ዶክተር ወርቁ ያዕቆብ እንደሚሉት ይህ አጋር የመፈለግ ጥረት ማሳያ ነው። ሶማሊያ ከግብጽ እና ኤርትራ ጋር አስመራ ውስጥ ያደረገችው  የሦስትዮሽ የፀጥታ እና የደህንነት ውል ተቀጥላ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ስለመሆኑም ይነገራል።

"በግብጽ አነቃቂነት ወይም አነሳሽነት በሚባል ደረጃ ያለው ሁኔታ አካባቢውን በትብብር መንፈስ ከሚሠሩበት ነገር ይልቅ ወደ ክፍፍል፣ ወደ አንድነት ሳይሆን ወደ ውጥረት ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ እንዲገቡ ያደረገ ይመስለኛል"።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከሶማሊያ ጋር እሰጥ አገባ ማስገባቱንምስል ASHRAF SHAZLY/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ

ግብጽየባሕር በር መጠቀምን በተመለከተ ከባሕሩ ተዋሳኝ ሀገር ውጪ ሌሎች የመጠቀም መብት አይኖራቸውም ከማለት አልፋ የኢትዮጵያን እና የሶማሊያን ጉዳይ በአንክሮ በመከታተል ላይ መሆኗን መግለጿ፣ ኤርትራም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አማካሪ በኩል ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ ያደረጉት ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል በሚል አስተያየት መስጠታቸው ለዓለም አቀፍ ሕግና ዲፕሎማሲ ተንታኙ ጥሩ ምልክት አይደለም።

"የግብጽ አቋም የማስቆጣት ዓላማ ያለው አዛዥ ነኝ ከሚል አመለካከት የሚነሳ ይመስለኛል እንጂ ዓለም አቀፍ ባሕር ላይ እከሌ ልትመጪ አትችይም እከሌ መምጣት ትችያለሽ የሚል ፈቃጅ ወይም ከልካይ አካል አትመስለኝም ግብጽ" ብለዋል።

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና የመስጠት ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።ምስል Rick Scuteri/AP Photo/picture alliance

የዶናልድ ፕራምፕ ወደ ስልጣን መመለስ በአፍሪካ ቀንድ ምን ያስከትል ይሆን

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ከጂቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦመር ጊሌ ጋር ትናንት ተወያይተው "ሁለቱ ሀገራት በቀጣናው ያለውን መረጋጋት እና ትብብር ለመደገፍ ተስማምተዋል" ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። የሶማሊያው ፕሬዝዳንትም ትናንት እዚያው ጅቡቲ ውስጥ ነበሩ። በሌላ በኩል አሜሪካ ከግብጽ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ሀገር ስለመሆኑ ሁለቱም ተንታኞች ይስማማሉ። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን የመመለሳቸው ነገር ለግብጽ ትልቅ ዕድልም መሆኑ እንደማይቀር ይጠቀሳል።

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና የመስጠት ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችል የሚገልፁት ባለሙያዎቹ ያም ሆኖ የራስ ገዟ ሶማሊላንድ የፀጥታ ኃይሎች ሶሞኑን ኢትዮጵያ ውስጥ በሶማሌ ክልል ሞት እና የአካል ጉዳት ያስከተለ ጥቃት የማድረሳቸው አዝማሚያ የአካባቢው ሌላ ተጨማሪ ዐቢይ ጉዳይ እንደነበርም ገልፀዋል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW