1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ዉሉ ድጋፍና ተቃዉሞ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29 2015

በጀርመን የአማራ ማሕበር «የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎች የሆኑ የአማራው አጽመ ርስቶችን ከ 100 ኪ.ሜ በላይ በተደጋጋሚ ለሱዳን ሲያስወርሩ እና አሳልፈው ሲሰጡ የኖሩት ሕወሃትና ብልጽግና የሰላም ስምምነት መድረኩን ለራሳቸው የፖለቲካ ችግር መፍቻነት እና ጊዜ ለመግዣነት ተጠቅመውበታል» ሲል ተችቷል።

Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

የሰላም ስምምነቱ ጀርመን በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ዕይታ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግሥትና የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ባለሥልጣናት ባለፈዉ ሳምንት የተፈራረሙት ግጭት የማቆም ስምምነት እዚሕ ጀርመን ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ድጋፍም፣ ቅሬታም፣ ተቃዉሞም ገጥሞታል። ባለፈዉ ሳምንት ሮብ በተፈረመዉ ስምምነት መሠረት ህወሓት ትጥቅ ስለሚፈታበት ስልትና ሒደት የሁለቱ ወገኖች የጦር አዛዦች ናይሮቢ-ኬንያ ዉስጥ እየተነጋገሩ ነዉ። የፍራንክፈርቱ ወኪላችን እንዳላልካቸዉ ፈቃደ ያነጋገራቸዉ ጀርመን የሚኖሩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተንታኞች፣ ምሑራንና የማኅበራት መሪዎች ሰላም ለማስፈን የሚደረገዉን ጥረት እኩል ይደግፉታል። ይሁንና አስተያየት ሰጪዎቹ በስምምነቱ ይዘትና በገቢራዊነቱ ላይ የተለያየ አስተያየት አላቸዉ።
 ስምምነቱ በጀርመን ነዋሪ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ጥርጣሬን እና ተቃውሞን እያስተናገደ ይገኛል። በጀርመን የአማራ ማህበር «የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎች የሆኑ የአማራው አጽመ ርስቶችን ከ 100 ኪ.ሜ በላይ በተደጋጋሚ ለሱዳን ሲያስወርሩ እና አሳልፈው ሲሰጡ የኖሩት ሕወሃትና ብልጽግና የሰላም ስምምነት መድረኩን ለራሳቸው የፖለቲካ ችግር መፍቻነት እና ጊዜ ለመግዣነት ተጠቅመውበታል» ሲል ተችቷል። የማህበሩ ሊቀመንበር ኢንጂነር ተፈሪ አበጋዝ ሕወሃት በዋና ጠላትነት ፈርጆት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት የተፈጸመበት የአማራው ወኪሎች ባልተሳተፉበት የሰላም ስምምነት አወዛጋቢ አካባቢዎች እሳቸው ኢ-ፍትሃዊ ነው ባሉት ህገመንግስቱ መሰረት ይፈታል መባሉንም ተቃውመዋል:: በትግራይ የተቃውሞ ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉት የሕግ ባለሙያው አቶ ዮናስ መብራቱ በበኩላቸው ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ አያሌ አስከፊ የመብት ጥሰቶች ቢፈጸሙም ስምምነቱ በግልጽ ተጠያቂነትን የማያሰፍን እና ፍትህን የማያረጋግጥ ነው ሲሉ ተችተውታል:: ባለሙያው የኤርትራ ጦር ባልወጣበትና የኢትዮጵያ ጥምር ጦርም ስጋት በሆነበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ስምምነት የትግራይን ሕዝብ ለአደጋ የሚያጋልጥ እና መሬት ላይ ወርዶ ሊተገበር የማይችል ነው ሲሉም ገልጸዋል።ከፕሪቶሪያ መልስ ላቅ ያለው ተስፋ እና ትንሹ ስጋት

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትና የትግራይ ክልል ኃይሎች ለ 2 ዓመታት የዘለቀውን ግጭት ለማብቃት በደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶሪያው ድርድር ከቀናት በፊት የደረሱበት የሰላም ስምምነት በጀርመን ነዋሪ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ዘንድም ከፍተኛ ደስታን ጥርጣሬን እና ተቃውሞን እያስተናገደ ይገኛል:: የቀድሞ ንጉሳውያን ቤተሰብ አባል እና በጀርመን መንግሥት የአፍሪቃና የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች የፖለቲካ አማካሪና ተንታኝ ልዑል ዶክተር አስፋ ወሰን አስራተ ካሳ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው እና ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት ያደረሰው ጦርነት ማብቃቱ በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ለዚህ ሁሉ ችግር አንዱ ዋንኛ መንስኤ ነው የሚሉት ቋንቋን እና ብሄርን መሰረት ያደረገው የፌደራሊዝም አወቃቀር የተመሰረተበት ሕገመንግስት እንዲለወጥ ጠይቀዋል::
"ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ 500 ሺህ በላይ ሰዎች በጦርነቱ ሳቢያ ሕይወታቸውን አጥተዋል:: እጅግ አሳዛኝ እና አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ በአንዲት ሃገር ወንድማማችና እህትማማች ሕዝቦች መካከል የተካሄደ ግጭት በመሆኑ በፍጹም ሊቆምና ሰላም ሊሰፍን ይገባል:: እኔም ይህ አስከፊ ቀውስ በማብቃቱ በእጅጉ በጣም ደስ ብሎኛል:: ሆኖም በስምምነቱ ላይ የሕወሃት ኃይሎች በሙሉ ትጥቅ ይፈታሉ የሚለው ሃሳብ ያለፉት 30 ዓመታት ታሪክን ስንመረምር በተግባር ተፈጻሚነቱ ላይ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድደን ነው:: የጦር መሳሪያዎቻቸውን በየ ጉድጓዱና ዋሻው ካልደበቁና እንደተባለው ትጥቅ የማስፈታቱ ስራ በተጨባጭ የሚከናወን ከሆነ በ እውነቱ ሌላውም የስምምነቱ አንቀጽ ይፈጸማል የሚል ሙሉ እምነት ሊኖረን ይችላል:: ከዚሁ ጋር ሳይጠቀስ የማይታለፈው የችግሮቻችን ሁሉ ዋናው መፍቻ ቁልፍ በኃይል የተጫነብን እና ኢትዮጵያንም ሊያፈርስ የተቃረበው የሕገመንግስቱ ጉዳይ ነው:: እንደሚባለው ቋንቋን እና ብሔርን መሰረት ያደረገው ሕገመንግስቱ እውነተኛ የፌደራልም ሆነ የዴሞክራሲያዊ መንግሥታዊ የአስተዳደር አወቃቀር ሥርዓትን የሚከተል አይደለም:: በመሆኑም ከውጪው የተወሰነ የሚጠቅመንን ወስደን ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ለኢትዮጵያም ለመላው ሕዝቧም የሚጠቅም የተሻሻለ እውነተኛ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገመንግሥትን ማበርከት ይኖርብናል" ሲሉ ልዑል ዶክትር አስፋ ወሰን አስራተ ካሳ ምክረ ሃሳባቸውን ለግሰዋል::

ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ ካሳምስል DW

በኤርላንገን ኑረንበርግ ፍሬድሪሽ አሌክሳንደር ዩኒቨርሲቲ በህግ የዶክትሬት መመረቂያቸውን በመስራት ላይ የሚገኙት እና በዲያስፖራ የትግራይ የትግራይ የተቃውሞ ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉት አቶ ዮናስ መብራቱ ስምምነቱ አያሌ ችግሮችና ክፍተቶች አሉት ሲሉ ለዶይቼ ቨለ ገልጸዋል:: ባለሙያው ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ አያሌ አስከፊ የመብት ጥሰቶች ቢፈጸሙም ስምምነቱ አንዳንድ ጉዳዮች በሽግግሩ ወቅት ይታያሉ ከማለት በስተቀር በግልጽ ተጠያቂነትን የማያሰፍን እና ፍትህን የማያረጋግጥ ነው ሲሉ ተችተውታል:: የኤርትራ ጦር ባልወጣበትና የኢትዮጵያ ጥምር ጦርም ስጋት በሆነበት ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ የትግራይ ኃይሎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ስምምነት ዶክተር ዓብይ "በስምምነቱ መቶ በመቶ ፍላጎታችንን አሳክተናል" እንዳሉት የትግራይን ሕዝብ ለአደጋ የሚያጋልጥ በኃይል የተጫነ እና መሬት ላይ ወርዶ ሊተገበር የማይችል ነው የሚል ዕምነት እንዳላቸውም አቶ ዮናስ ገልጸዋል::

በጀርመን የአማራ ማህበር "የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎች የሆኑ የአማራው አጽመ ርስቶችን ከ 100 ኪ.ሜ በላይ በተደጋጋሚ ለሱዳን ሲያስወርሩ እና አሳልፈው ሲሰጡ የኖሩት ሕወሃትና ብልጽግና የሰላም ስምምነት መድረኩን ለራሳቸው የፖለቲካ ችግር መፍቻነት እና ጊዜ ለመግዣነት ተጠቅመውበታል" ሲል ተችቷል:: የማህበሩ ሊቀመንበር ኢንጂነር ተፈሪ አበጋዝ ሕወሃት በዋና ጠላትነት ፈርጆት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት የተፈጸመበት የአማራው ወኪሎች ባልተሳተፉበት የሰላም ስምምነት አንቀጽ 10 መሰረት አወዛጋቢ አካባቢዎች እሳቸው ኢ-ፍትሃዊ ነው ባሉት ህገመንግስቱ መሰረት ይፈታል መባሉንም ተቃውመዋል:: ሕገመንግስቱ ከመጸደቁ በፊት በፖለቲካ ውሳኔ እና በኃይል ትህነግ ወደ ትግራይ ያካለላቸውን የአማራው አካባቢዎች ህገ መንግስቱን አስታኮ ለሕወሃት ለማስረከብ ዳር ዳር ማለትም ዘላቂ ሰላም ከማስፈን ይልቅ በሕዝቦች መካከል የማያባራ ቅረኔን የሚፈጥር ተጨባጭ ውጤት የማያመጣና አደገኛ አዝማሚያ ነው ሲሉ አስረድተዋል:: አሁን በሕወሃትና በብልጽግና መካከል እየተደረገ ያለው የሰላም ስምምነት መድረክ በ 1983 ዓ.ም ሕወሃት እና ኦነግ የፈጸሙትን የተሳሳተ ድርድር የደገመ ነው ሲሉ የነቀፉት ኢንጂነር ተፈሪ የአማራ ክልልን የሚመራው አዴፓ ካለፈው ስህተቱ የማይማር እና ቆሜለታለሁ የሚለውንም ሕዝብ ጥቅም ያስጠብቃል የሚል ዕምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል::ስለሰላም ስምምነቱ በዉጭ የሚኖሩ የትግራይ ፖለቲከኞችና ተወላጆች አስተያየት

የሰላም ስምምነቱ የአፍሪቃን ችግር በአፍሪቃውያን መፍታት እንደሚቻል በግጭቶች ሰበብ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ለሚፈጽሙ ምዕራባውያን ሃገራት አስተማሪ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡንም ነበሩ:: አቶ አፈወርቅ ተፈራ በጀርመን የኢትዮጵያውያን ውይይትና ትብብር መድረክ ሊቀመንበር ናቸው:: ስምምነቱ በእጅጉ እንዳስደሰታቸው ቢገልጹም የተግባር አፈጻጸሙ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል በማለት አስገንዝበዋል::
"የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ብዙ እርቀት ቢጓዝም በሕወሃት እምቢ ባይነት ጥረቱ ስኬት ሳያመጣ ቆይቷል" ያሉት አቶ አፈወርቅ ሆኖም የአያሌ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው ንብረትን ያወደመውና ለቀጣናው ጭምር ከፍተኛ ስጋት ሆኖ የቆየው ግጭት በሰላም እልባት ማግኘቱ በእጅጉ አስደስቶኛል ብለዋል:: በጦርነቱ አካባቢ የሚገኙ ሕዝቦች ያልተገደበ ሰብዓዊ አገልግሎት አቅርቦት ሊያገኙ ይገባል ያሉት አቶ አፈወርቅ ይህንንም ለማረጋገጥ ሕወሃት ለገባው ስምምነት ተገዢ በመሆን ሙሉ ለሙሉ ትጥቁን ፈቶ ሙሉ ለሙሉ ሰላም ሊሰፍን ይገባል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:: የስምምነቱ አፈጻጸም ብዙ ያልተገለጹ ዝርዝር ጉዳዮች ሊኖሩት ቢችሉም በስምምነቱ መሰረት ገቢራዊ እንደሚሆን ግን ተስፋ አደርጋለሁ ነው ያሉን ።

እንዳልካቸው ፈቃደ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW