የሰላም ጉባኤ በጋምቤላ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 23 2018
ጉባኤው በዋናነት በሁለቱ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከፌደራል ባለሥጣናት ጋር መምከራቸው ተገልጿል።
‹‹የሰዓት ዕላፊ ገደብ ከተጣለ ወዲህ በጋምቤላ ከተማ ጸጥታው ተሻሽሏል››
ኢትዮጵያውስጥ በጋምቤላ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለመቆጣጠር፣ ግጭቱ በተከሰተባቸው ቦታዎች ከታጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ በተጨማሪ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ የክልሉ መንግሥት አመልክቷል። አቶ ኦዶል አጉዋ በጋምቤላ ከተማ የሀገር ሽማግሌ ሲሆኑ ግጭት በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው የኑዌርና አኙዋ ወረዳዎች የማኅበረሰብ ተወካዮችና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት የሰላም ጉባኤ ተካሂዷል።
በውይይቱ ከተነሱ ነጥቦች መካከል የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ሰላማዊ በሆነ መልኩ መፍታት፣ በጋምቤላ ከተማ ዙሪያ፣አቦል የተባለ ወረዳና ኢታንግ ልዩ ወረዳ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የሚደርሱ ታጣቂዎችም ትጥቅ እንዲፈቱ የሚሉት እንደሚገኙበት አብራርተዋል። በክልሉ ዋና ከተማ ሰዓት እላፊ ገደብ ከታወጀ ወዲህ አንጻራዊ ሰላም አለ ያሉት አቶ ኦዶል በምሽት አልፎ አልፎ ተኩስ የሚከፍቱ ግለሰቦች እንዳሉም ጠቁመዋል።
ግጭት ለመፍታት ያለመ ውይይት በጋምቤላ
በጋምቤላ ከተማ በተካደው የሰላም ጉባኤ የተሳተፉ የሁለቱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ድምበር አቋርጠው ጥቃት ይፈጽማሉ ያሏቸው ታጣቂዎች እንዳሉ ጥያቄ ያነሱ ሲሆን እስካሁን በግጭት መካከል የተጎዳም ሆነ እርምጃ የተወሰደበት ድምበር ጥሶ የገባ ታጣቂ ሃይል ግን አለመገኘቱን ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ተናግረዋል። በክልሉ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ግጭት የተስተዋለባቸው እንደ ኢታንግ ልዩ ወረዳና አቦል የተባለ ወረዳ ያሉ ስፍራዎች ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት የደረሰባቸው ቦታዎች እንደሆነም አመልክተዋል። በክልሉ ዋና ከተማ እንደ ጀመረው ውይይት በሁሉም ግጭት የተከሰተባቸው ወረዳዎች የሰላም ጉባኤ እንደሚካሄድ ተገልጸዋል።
በክልሉ በተለይም ወደ ላሬ የተባለ የኑዌር ዞን ወረዳ የሚወስዱ መንገዶች ዝግ ሆነው መቆየታቸውን የተናገሩት ሌላው አስተያየት ሰጪም የሰዎች እንቅስቃሴ በአካባቢው ተገድቦ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በክልሉ ተርፋም በተባለው ቦታም ብሔርን መሰረት ባደረገው ጥቃትም ባለፈው ሳምንት በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውንም አብራርተዋል።
በክልሉ የተጀመረውን የሰላም ጉባኤና ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታን ማብራሪያ የጠየቅናቸው የክልሉ ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማበር ኮር ከተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸው በጉዳዩ ላይ ግን ዝርዝር መረጃ መስጠት አልፈለጉም። በጋምቤላ ክልል በኅዳር ወር መጨረሻ ከላረ ወረዳ ወደ ጋምቤላ እያቀና በነበረ ተሽከርካሪ ላይ አቦል በተባለው የክልሉ አንድ ወረዳ ውስጥ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ በተስፋፋው የጸጥታ ችግር ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳት መድረሱን ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።
ነጋሳ ደሳለኝ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ