የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መፍትኄ
ረቡዕ፣ መስከረም 4 2015በሰሜን ኢትዮጵያ መቋጫ አጥቶ የቀጠለው ጦርነት በተፋላሚ ኃይላት መካከል መተማመን ካልተፈጠረ በሰላም የመፈታት እድሉ እጅግ ጠባብ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ገለጹ። ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ባለፈው እሁድ የተኩስ አቁም ጥሪ ቢያቀርብም ገቢራዊ የሚሆነው ግን ተፋላሚዎቹ ከግል የፖለቲካ ዓለማ ይልቅ ለሕዝቡ ሰቆቃ ቅድሚያ መስጠት ከቻሉ ብቻ ነው ተብሏል።
ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ለሦስተኛ ዙር በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚያሳዩ መረጃዎች በርካታ ናቸው። ለአምስት ወራት ያህል ተፋላሚ ኃይላት የተናጥል የተኩስ አቁም ጥሪ አውጀው ወደ ሰላማዊ መፍትኄ ይኬዳል የሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ይህ ጦርነት በአገሪቱ ላይ የሚያደርሰው ዘርፈ ብዙ ጫና አሁንም እንደቀጠለ ነው።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ሴኔሳ ደምሴ እንደሚሉት፤ «ከጅምሩም አላስፈላጊ የነበረው ጦርነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውይይት ባህል ባለመኖሩ፣ በአፍሪቃ ቀንድ የጂኦ-ፖለቲካ ሁናቴ ውስጥ የተዋንያን መበራከት እና የተደራዳሪዎች የድርድር ቅድመ ሁኔታ ማብዛት» አስቀድሞም ለዚህ ጦርነት እልባቱ ቅርብ እንዳልሆነ ጉልህ ማሳያዎች ነበሩ ይላሉ።
ባለፈው እሁድ መስከረም 01 ቀን፣ 2015 ዓ.ም. ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የተኩስ አቁም ጥሪ እና የሰላም ድርድር ጥያቄን ማቅረቡን ተከትሎ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመደምደም በጎ ርምጃ ነው በማለት በአዎንታዊነት ቢቀበሉም እስካሁን የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ዝምታን የመረጠ መስሏል።
የሰሜን ኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ለሚከታተሉትና መሰረቱን በትግራይ ያደረገው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን በምክትል ሊቀመንበርነት ለሚመሩት ፖለቲከኛ መስፍን ደሳለኝ፤ ይህ የሕወሓት ጥሪ ያልጠበቁት ነበር። እንደ አቶ መስፍን ምልከታ «ብቸኛው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መቋጫ መንገድ ሰላማዊ ድርድር በመሆኑ» ተስፋን ሰንቀዋል። አቶ መስፍን በሰላማዊ ድርድሩ መቀጠል ላይ ግን አሁንም ጥሪጣሬ አላቸው። «ተፋላሚ ኃይላቱ ምን ያህል ከግል ፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ወጥተው በጦርነቱ እየተጎዳ ያለውን ህዝብ እና የአገር ጉዳት ቅድሚያ ሰጥተው ይመለከቱታል» የሚለውን ሐሳብም በጥያቄነት ያነሱታል። በጦርነት ውስጥ ያሉ ተፋላሚ አካላት አሁንም ቢሆን ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው በትኩረት ከሰሩበት ግን ከዚህ ጦርነት አገርና ህዝብን የማላቀቅ እድል ይኖራልም ባይ ናቸው ፖለቲከኛ መስፍን ደሳለኝ።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር ሴኔሳ ደምሴ በሰሜን ኢትዮጵያ በሰላማዊ ድርድር ጦርነቱን የመቋጨት ውሳኔን ያራቀው ዋነኛው ምክኒያት በተፋላሚ ኃይላት መካከል የሚስተዋለው የአለመተማመን አባዜ ነው ይላሉ፡፡ «ሕወሓት ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ያሳያቸው ተለዋዋጭና ያልተጨበጠ ባህሪ የኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን እንዲለው ሳያስገድደው አልቀረም» ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ ጦርነቱ ባጠረ ጊዜ ይደመደማል የሚል ግምት እንደሌላቸውም ነው ያመለከቱት።
ሕወሓት በመስረም 01 ቀን፣ 2015ቱ የሰላም ጥሪው ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቆ በአፍሪቃ ኅብረቱ ድርድር ጥላ ስር ለመወያየት መስማማቱን ዐሳውቋል። ይህ የሕወሓት ጥሪ ከቀረበበት ከእሁድ ወዲህም ጭምር ጦርነቱ አልቆመም። ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻም በትግራይ ክልል መዲና መቀለ ከሦሰት ጊዜ ያላነሰ የአየር ድብደባ በመንግስት መከወኑ ተዘግቧል።
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ