1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ማብቂያው የት ይሆን?

ረቡዕ፣ ጥቅምት 9 2015

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች የመንግሥት ጥምር ጦር ሽሬን ጨምሮ ቢያንስ ሦስት የትግራይ ክልል ከተሞችን መቆጣጠራቸውን አረጋግጠዋል። ሦስተኛ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ጦርነት ማለቂያው ወዴት ይሆን? የአፍሪካ የአደራዳሪነት ሚናስ ምን ያህል ገፍቶ ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል?

Äthiopien  | Bürgerkrieg
ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የሕግ እና ሰብዓዊ መብት ተንታኝ እይታ

This browser does not support the audio element.

ሁለት ዓመታትን ሊደፍን የሁለት ሳምንታት ዕድሜ የቀረው በሰሜን ኢትዮጵያ የተጫረው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ጥምር ኃይሎች ስልታዊቷን የሽረ ከተማን ጨምሮ አላማጣ እና ኮረምን መቆጣጠራቸውን፤ በእነዚህ አከባቢዎችም ከረድኤት ድርጅቶች ጋር በመሆን አስፈላጊ ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል። በሰሜን ኢትዮጵያ መንግሥትን የሚፋለሙት ኃይሎች በበኩላቸው የሽረ ከተማ በመንግሥት ኃይሎች መያዝ «የተለመደ የጦርነት መገፋፋት ነው» በማለት የጦርነቱን ቀጣይነት የሚያመላክት መግለጫ አውጥተዋል። የሆነ ሆኖ ይህ ሁለት ዓመታት የተጠጋው ጦርነት በሰብዓዊ መብት፣ በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ እያደረሰው ያለው ጫና በበርካቶች እየተወገዘ ይገኛል።የኢትዮጵያ መንግሥት መግለጫ እና የተመድ ማሳሰቢያ

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ማዕከል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አቶ በፍቃዱ ዲሪባ ለዶይቼ ቬለ (DW) በሰጡት አስተያየት ጦርነቱ ተፋላሚዎችን በመጨረሻም ወደ ሰላማዊ ድርድር ካላመራ መፍትሄው ቅርብ አይመስልም ይላሉ። በዚሁ በሰሜን ኢትዮጵያ አሁን እየተካሄደ ባለው ሦስተኛ ዙር የተፋፋመ ጦርነት በፊት በመጀመሪያዎቹ የጦርነቱ ሁለት ምዕራፎች የወታደራዊ የበላይነት የወሰዱ ተፋላሚዎች ለሰላም በር ዝግ ማድረጋቸው ጦርነቱን ከማራዘም ሌላ ያመጣው ውጤት የለምም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ የሁለቱም ተፋላሚ ቡድኖች ሚና ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም በማስገንዘብ። እንደ ተንታኙ ማብራሪያ የኢትዮጵያ ጥምር ጦር እንደ ከዚህ ቀደሙ ዳግም የትግራይ ክልልን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እና አዲስ አስተዳደራዊ መዋቅር ማደራጀትም ለዘላቂው ሰላም ዋስትና አይደለም። በመሆኑም ተፋላሚ ኃይላቱ የኃይል ሚዛናቸው ላይ ያልተመሰረተ ከልብ ለሆነ ድርድር መሰናዳት ይኖርባቸዋልም ይላሉ።

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር ያለውን እንቅስቃሴ ያሳያል የተባለው የሳተላይት ምስልምስል MAXAR/REUTERS

 «ህወሓትም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ለእውነተኛ ሰላም ቁርጠኛ ከሆኑ በሚያጠቁበትም ሆነ በሚጠቁበት ጊዜ ለሰላሙ በራቸውን መክፈት አለባቸው» ሲሉም ሀሳባቸውን ገልጸዋል።  በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም የአህጉራት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣናት ውትውታ እና ተማጽእኖያቸውን እያሰሙ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ከትናንት በስቲያ የመንግሥት ጥምር ጦር ሽረን ጨምሮ ቁልፍ ወታደራዊ ሚና አላቸው የተባሉ የትግራይ አከባቢዎችን መቆጣጠራቸው ይፋ ከመደረጉም አስቀድሞ «ኢትዮጵያ ውስጥ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ ነው» በማለት ተፋላሚ ኃይላት ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ ጠይቀዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊውን ጨምሮ ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ህብረትም ጦርነቱ እንዲቆም ብሎም በኢትዮጵያው የውስጥ ጦርነት ተሳትፎ እያደረገ ነው ያሉት የኤርትራ መንግሥት ሠራዊቱን ከኢትዮጵያ እንዲያስወጣ በማለት ጥሪ እያቀረቡ ነው። ከኢትዮጵያ መንግሥት ጥምር ጦር ጋር የሚዋጋው ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመሆን እያጠቁት እንደሚገኙና በተደጋጋሚ ወታደራዊ እርምጃ እንደወሰደባቸው በከዚህ በፊት መግለጫዎቹ አመልክቷል። በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግን ስለዚህ ጉዳይ ማስተባባያም ሆነ ማረጋገጫ አልተሰጠበትም። እንደ የሕግ ባለሙያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በፍቃዱ ድሪባ ግን የኤርትራ ሠራዊት ተሳትፎ አገር አቀፋዊውን ጦርነት ወደ ዓለም አቀፋዊነት ሊያሸጋግረው ይችላል። ተመድ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው ያለው ጦርነት ባስቸኳይ እንዲቆም ሰሞኑን ሲጠይቅ፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አንደሚባለው ጦርነቱ ከቁጥጥር ውጪ የወጣው ወደ አጎራባች ክልሎች በተዛመተ ጊዜ ነበር በማለት በትዊተር መልስ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች በዛላንበሳ ድንበር በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ምስል Alexander Joe/AFP/dpa/picture-alliance

 ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW