የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ
ዓርብ፣ ጥር 20 2014
ትግራይ ክልል ውስጥ ተጀምሮ ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎችም ተስፋፍቶ ይሄን ያሕል ተብሎ በተጨባጭ ያልተገለፀ ንፁሃን ዜጎች እና በሁለቱም ተፋላሚ የፀጥታ ኃይላት ላይ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ በመንግሥት እና የሕዝብ የንብረት ላይም ውድመት አስከትሏል።
ጦርነቱ የዜጎችን መደበኛ ሕይወት በእጅጉ አናግቷል። ከአፀደ ሕፃናት እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ በመማር ላይ የነበሩትን ተማሪዎች እና መምህራንን ጨምሮ ከሥራቸው አደናቅፏቸዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው 4120 የትምህርት ተቋማት በጦርነቱ ሳቢያ ውድመት ደርሶባቸዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ቢሆኑ ጦርነቱ ውስብስብ ችግር ካደረሰባቸው ተቋማት መካከል ናቸው። በተለይም በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ሲማሩ ዓመታትን ያሳለፉ ተማሪዎች የጦርነቱን መባባስ ተከትሎ ከየተቋሞቻቸው እንዲወጡ የነበረው የወላጆች ጥያቄ፣ ጭንቀትና አቤቱታ ከፍተኛ ነበር። ተማሪዎቹም ቢሆን የቻሉት እና አቅም የነበራቸው በእግር ያላቸው ንብረት ማለትም ስልክ፣ ኮምፒውተር፣ ልብስ እና ጫማ በመሸጥ ከጦርነቱ ቀጣና ለመውጣት ጥረት አድርገው ሲሳካላቸው አብዛኛዎቹ ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ ጭምር ነበር ወደየ ቤተሰቦቻቸው ለመቀላቀል የበቁት።
ጦርነቱ በእነዚህ ተማሪዎች ራእይ ላይ ትልቅ እንቅፋት እንደጋረጠባቸው ገልፀዋል። አንዳንዶቹ በማዕረግ ተመርቀው ሥራም ይዘው ሕይወትን ለመጀመር ወራቶች ብቻ ሲቀሩ ያንን ክስተት ማስተናገዳቸው አስከፍቷቸዋል።
ሌሎች በበኩላቸው በችግር ውስጥ ሆነው ያስተማሯቸውን ቤተሰቦቻቸውን የሚረዱበት ጊዜ መቃረቡን እያለሙ ባለበት ወቅት ለዚህ ችግር መዳረጋቸው አሁን ድረስ የቤተሰብ ጥገኛ የመሆን ከባድ የሥነ ልቦና ስሜት ፈጥሮባቸዋል።
እነዚህ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትግራይ ክልል ውስጥ እያሉ የመብራት፣ የስልክ ፣ የኢንተርኔት እና የባንክ አገልግሎቶች ባለመኖሩ ከመቸገራቸው በላይ የጦርነቱ አስፈሪ ድባብ የፈጠረባቸው ጭንቀት ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ተማሪዎቹ ከክልሉ ከወጡ በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር ወደ ሌሎች ተቋማት በፍጥነት ሊመድባቸው ባለመቻሉም ሌላ ያልጠበቁት ችግር እንደገጠማቸውና ለስምንት ወራት ያህል ያለምንም መፍትሔ መንገላታታቸው በራሱ ፈተና ሆኖባቸው እንደቆየ ተናግረዋል።
ይህ ሁኔታ ብዙ ወጣቶች ወደማያውቁት ሱስ ውስጥ እንዲገቡ፣ የተስፋ ማጣት ሥሜት ውስጥ እንዲገቡም እንዳደረጋቸው ደጋግመው አስገንዝበዋል። ደረሰብን ያሉት የሥነ ልቦና ጫና ቀላል እንዳልሆነም በምሬት ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከገቡ ጀምሮ እስካሁን የተማሩበት የትምህርት ማስረጃ ስለመኖር አለመኖሩ ከትምህርት ሚኒስቴር ማረጋገጫ ባለማግኘታቸው ሰነድ አልባ ተማሪ የመሆን ስሜት ፈጥሮባቸዋል።
ጉዳቱ ከዚህም ተሻግሮ ቤተሰቦቻቸውን ለተጨማሪ ወጪ የዳረገ የኢኮኖሚ ጥያቄም ይዞባቸው የመጣ መሆኑን ገልፀዋል። ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች እንደወጣ የሚናገረውና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ይማር የነበረው ተመራቂ ተማሪ ዘርፉ ሸኖ ቤተሰቦቹን ተመርቆ ሥራም አፈላልጎ ለመርዳት የነበረው ውጥን ከመደናቀፉ በላይ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በእግሩ በራያ በኩል አቆራርጦ የወጣ እና ከለበሰው ሸሚዝ ፣ ጫማ እና ሱሪ በቀር ሌላውን ዕቃውን ሸጦ ምንም ይዞ አልተመለሰም። "ይህንን ሁሉ ጨርሼ ከመጣሁ በኋላ ልብስ ለመግዛት ብር ያስፈልገኛል፣ ይህንንም እንደገና ከቤተሰብ ነው የማገኘው።ይህንን ለማሟላት አሁን ( ወደተመደበበት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለመመለስ ) እንደ አዲስ ተማሪ ሆኜ ነው የምገባው። አንሶላ ፣ ብርድ ልብስ፣ ልብስ፣ ኤሌክትሮኒክስ ማለትም ስልክና ከተቻለም ኮምፒውተር ያስፈልጋል ፣ ግን ያንን ለማሟላት ለቤተሰብ ከባድ ሆኗል" በማለት ይገልፃል።
የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪ የነበረው ሌላኛው ወጣት ብስራት ፋንታሁን የደረሰበትን ዙሪያ መለስ ችግር ከተመለከተ በኃላ "ጦርነት አያስፈልግም። የእርስ በርስ ጦርነት መጨረሻው ሞት እና እልቂት ነው። ሁሉንም ነገር ነው የሚጎዳው። ስለዚህ ይህ ነገር ቆሞ ወደቀደመው ሰላም መመለስ አለብን " ይላል።
ትምህርት ሚኒስቴር ትግራይ ክልል ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩ ብዙ ተማሪዎችን ከብዙ መጉላላት በኋላ ወደ ሌሎች ክልሎች ሲመድብ አማራ ክልል ውስጥ ወደሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መድቤያችኋለሁ ብሏቸው የነበሩ ተማሪዎች የትምህርት ተቋሞቹ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ እና ከመቀበል አቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ምክንያት ሳይቀበሏቸው ለስምንት ወራት ሲጉላሉ ቆይተዋል። ይሁንና ከብዙ ውትወታ እና ጥያቄ በኋላ ተማሪዎቹ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ወደ ተመደቡባቸው ተቋማት እንደሚጠሩ ዩኒቨርሲቲዎቹም፣ ትምህርት ሚኒስቴርም ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።ተማሪዎቹም የዘገየ ውሳኔ ቢሆንም በዚህ ደስተኞች ሆነዋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ