1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

በሰራተኞች ቀን የኢትዮጵያ ሀኪሞችና መምህራን ጥሪ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 23 2017

ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም በጎላ ሁኔታ ድምጻቸውን ከፍ አድረገው ስለ የስራ ሁኔታቸውና ተመጣጣኝ የደመወዝ ሁኔታ እያነሱ የሚገኙት ሀኪሞችና መምህራን እንደ ዛሬ ያለው የሰራተኞች ቀን ለችግሮቻቸው እልባት የሚያመጣ መሆን ነበረበት ይላሉ፡፡

የህክምና መሳሪያዎች እና መድሓኒቶች
ምስል፦ picture alliance/Bildagentur-online/Ohde

በሰራተኞች ቀን የኢትዮጵያ ሀኪሞችና መምህራን ጥሪ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ ውስጥ እየናረ ከመጣው የኑሮ ሁኔታ አንጻር መላው የመንግስት ሰራተኛው በክፍያ ተመጣጣኝነት ላይ ሰፊ ጥያቄ ቢያነሱም፤ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከሚሰጡት አገልግሎትና የትምህርት ዝግጅታቸው አኳያ የጤና ባለሙያዎችና የመምህራን ጉዳይ ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡

የሀኪሞቹ ጥያቄና ብርቱ ፈተናው

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በጤና ባለሙያዎች  እየተነሳ ባለው የተመጣጣኝ ደመወዝ ጥያቄ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን የሚገልጹት አንድ ሀኪም በትምህርቱ ዓለም ያሳለፉት ድካም የዛሬን ህይወት ለማሻሻል ቢሆንም የሆነው ሌላ ነውና እንደዛሬ ያለው ዕለት እልባት ይዞላቸው እንዲመጣ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ “በትምህርትም በምንም እራሳችንን አበልጽገን ግን ደግሞ በምንሰራው ስራ ልክ የሚሰጠው ክብርና ዋጋ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። አሁን ባጋጠመን የኑሮ ውድነት ምክንያት ልጅ ወልደን የማናሳድግበት ደረጃ ላይ ደርሰናል” በማለት በሚከፈላቸው ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን አማረዋል፡፡ እናም እንደ ዛሬ ያለው የሰራተኞች ቀን ተመጣጣኝ ደመወዝ የሚታይበት የሰራተኞች ቀን ለውጥ እንደሚያመጣላቸውም ተስፋ ያደርጋሉ፡፡

የሰራተኞች ቀን ለሀኪሞች ጥያቄ ምን ፋይዳ አለው?

ሌላም አስተያየት ሰጪ ሀኪም ሀሳባቸውን ቀጠሉ “ከኛ አኳያ የላባደሮች ቀን ብሎ ማክበሩ ቀልድ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት ሀኪሙ፤ አሰሪዎች እንኳን ለሰራተኞች ቀን አደረሳችሁ ቢሉም ዞር ብለው ግን የሰራተኞቻቸውን ላብ ያብሳሉ ወይ ነው ጥያቄው፡፡" የጤና ባለሙያዎች ከባድ ያሉት ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪው፤ እያነሱት ያለውም ከሚከፈላቸው ዝቅተኛ ደመወዝ አኳያ የመኖር አለመኖር ጥያቄን እያነሱ መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡

ምስል፦ Eshete Bekele/DW

ስርዓተ ትምህርቱን ለማዳን የመምህራን አቤቱታ

ሌላው በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ በአነስተኛ የደመወዝ ክፍያ ብርቱ ፈተና ውስጥ እንደሚገኙ የሚገለጸው  የመመህራን ጉዳይ  ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እና የትምህርት ባለሙያ ሆነው የሚሰሩ አንድ አስተያየት ሰጪ አሁናዊውን የመምህራን የአነስተኛ ክፍያውን ፈተና ከዛሬው የሰራተኞች ቀን አስፈላጊነት ጋር አያይዘው አንስተውታል፡፡ “ምናልባት እንደጥያቄ ሊነሳ የሚገባው ይህ ዕለት የእኛ ቀን ነው የመምህራን ቀን ነው ተብሎስ ይታሰባል ወይ የሚለው ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ እለቱ የሆነ የብሔራዊ በዓል ተደርጎ ከመታሰብ ውጪ በትምህርት ቤቶች አሊያም በትምህርት ተቋማት ምንም እንቅስቃሴ አለመስተዋሉን እለቱ ለይስሙላ ብቻ የሚከበር እንዳይሆን ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ መምህርነታቸው በሰጡን አስተያየት ግን “የኢትዮጵያ መምህራን ጉዳይ የመምህራን ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋ ታዳጊዎች ውድቀት ስለሚሆን የሁሉም ወላጆች ጉዳይ መሆን ነበረበት” በማለት ሁሉም ዜጋ ለመምህራን መብት መጮህ ያለውን ተገቢነት አንስተዋል፡፡

መምህሩ አከሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ወድቋል እየተባለ የሚነገርለት ስርዓተ ትምህርቱን የማዳን አንደኛው መንገድም ይህ ነው፡፡ “ትምህርት በመመሪያ ወይም በስርዓተ ትምህርት ሳይሆን የመምህሩን ጥያቄ በመመለስ ነው በዋናነት የሚስተካከለው” ሲሉም አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡
ዛሬ የታወሰውን የሰራተኞች ቀን አስመልክቶ ትናንት መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማሕበራት ኮንፌደሬሽን መብታቸዉን ለማስከበር በሚጠይቁ ሠራተኞች ላይ አሠሪዎች የሚያደርሱት ጫናና በደል እንዲቆም መጠየቁ ይታወሳል። 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW