1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሰቆጣ አካባቢ ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች የጋራ ውሳኔ

ኢሳያስ ገላው
ዓርብ፣ ኅዳር 18 2019

በአማራ ክልል ዋግ ህምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች የኑሮ ውድነትንና ድርቅን ተከትሎ በአቅም ማነስ የሚፈጠር ማኅበራዊ መገለልን ለመከላከል፣ በሰርግ፣ በበዓላትና በኃዘን ወቅት የሚወጡ ከፍተኛ ወጪዎችንና የድግስ ፉክክሮችን የሚገታ የጋራ የማኅበረሰብ ስምምነት አፀደቁ።

አማራ ክልል ዋግ ህምራ ሰቆጣ ከተማ
አማራ ክልል ዋግ ህምራ ሰቆጣ ከተማ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

የሰቆጣ አካባቢ ነዋሪዎችና የሃይማኖት አባቶች የጋራ ውሳኔ

This browser does not support the audio element.

 

በሰቆጣ ከተማ ማኅበራዊ መገለልን ለመከላከልና አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስቆም የማኅበረሰብ ስምምነት ተላለፈ። በአማራ ክልል ዋግ ህምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች የኑሮ ውድነትንና ድርቅን ተከትሎ በአቅም ማነስ የሚፈጠር ማኅበራዊ መገለልን ለመከላከል፣ በሰርግ፣ በበዓላትና በኃዘን ወቅት የሚወጡ ከፍተኛ ወጪዎችንና የድግስ ፉክክሮችን የሚገታ የጋራ የማኅበረሰብ ስምምነት አጽድቀዋል።

የስምምነቱ መነሻ

በ አማራ ክልል የዋግ ህምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የኢኮኖሚ አቅም ማጣት የሚፈጥረውን ማኅበራዊ መገለል ለመከላከልና አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማስቆም የሚያስችሉ የማኅበረሰብ ስምምነት ውሳኔዎችን አሳለፉ። ውሳኔው በአካባቢው ባለው የድርቅና የኑሮ ውድነት ሁኔታ ውስጥ በሰርግ፣ በበዓላትና በኃዘን ወቅት የሚወጡ ከፍተኛ ወጪዎችንና አዳዲስ መጤ ልማዶችን ለመግታት ያለመ መሆኑ ተገልጿል። የኮሚቴው አባል የሆኑት ሊቀ ትጉሀን ማርቆስ የአካባቢው ማኅበራዊ መስተጋብር አቅመ ደካሞችን እያገለለ የመጣ መሆኑን ይናገራሉ። የድርቅ፣ የግጭትና የሃብት ውድድር ተጽዕኖ

የሀገር ሽማግሌው አቶ ጌጡ አበበ እንደሚሉት ደግሞ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በአቅም ማነስ ከማኅበራዊ ሕይወት እየተገለሉ መጥተዋል። በዚያ ላይ በድግሶች የሚታየው ወጪና ፉክክር የድሃውን ማኅበረሰብ ሞራል የሚጎዳ ሆኖ ቆይቷል ሲሉም አክለዋል።

የተዝካርና የሃይማኖታዊ ስርዓቶች አፈጻጸም

የዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሊቀ ኅሩያን ቄስ ኃይሉ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ሕዝቡን የማይጫኑና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ መሆን እንደሚገባቸው አንስተዋል።

«ተዝካር የሚባለው ቀደም ብለን እኛም አካባቢ እንደው በትንሽ ነገር ቢሆን ጥሩ አይደለም። ሁለት በሬ ሦስት በሬ እያረደ እንዲህ የሚሆነው ነገር ትክክል አይደለም። ተዝካር ማለት ማሰብ ነው፣ መጸለይ ነው፣ በጸሎት ነው የሚታሰበው። ከዚህ ውጭ ደግሞ ጸበል ጻድቅ ነው ለሚመጣው ሰው። ከዚህ ውጭ ግን እንደው እልፍ ያለው ነገር ትክክል አይደለም። ይሄ የተከለከለ ነገር አይደለም ቤተ ክርስቲያን እንደምታስገድድ ተደርጎ ግን መወሰድ የለበትም።»

የቅጣት እርምጃዎችና አፈጻጸም

ማኅበረሰቡ የራሱን ችግር ለመፍታት በፈቃደኝነት የተስማማበት መመሪያ እንደመሆኑ ስምምነቱን ተላልፈው የተገኙ የማኅበረሰቡ አባላት በቤተ ክርስቲያን አባቶች አልያም በመስጂድ ኢማሞች ቅጣት እንደሚወሰድባቸው ኮሚቴዎቹ አስታውቀዋል።

«ቃል ለመቀበል ተብሎ አምስት ሰው ብቻ ይበቃል የተባለበትን እንደባለፈው 150 ሰው ይዞ መሄድ፣ በሬ ማረድ፣ ያለአግባብ ወጪ ማውጣት እንደዛ ያደረገ ካለ ደግሞ 50 ሺህ ብር ይቀጣል። ይሄን የባረከ ቄስ 10 ሺህ ብር ይቀጣል።ይሄን ያደረገውን ልጁንም 50 ሺህ ብሩን እንዲከፍል ካላደረገይቀጣል። ግን ማን ይቅጣ የሚለውን ሙስሊም ከሆነ የመስጂድ የሚቆጣጠረው አካል እርምጃ ይወስዳል፣ ክርስቲያን ከሆነ በንስሃ አባቱ አማካኝነት ቅጣቱን ይቀጣል።»

በአካባቢው ሽምግልና፣ ቅልቅልና መልስ ከሰርግ ያልተናነሰ ወጪ በማስከተል ነዋሪዎችን ሲያማርሩ የቆዩ ልማዶች መሆናቸው ተገልጿል። ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Seyoum Getu/DW

 

የአብሮነት መጠናከርና የይሉኝታ ግፊት መቀነስ

የሰቆጣ ከተማ ባህል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ካሣ ከበደም ማኅበረሰቡ በስምምነት ያወጣው ደንብ የዋግ ህምራን ሕዝብ አብሮነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

«የአንድ አካባቢ መገለጫ ትልቁ ነገር ደግሞ ባህሉ፣ አመጋገቡ፣ አለባበሱ እና የእርስ በእርስ ያለው የመስተጋብር እሴት ስለሆነ ይሄንን የሚያጠናክር ነው የነበረው ለበርካታ ዘመናት እና አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያው ሰዉ በይሉኝታ ወይም ደግሞ በቃ ይሄን አድርጓልና ለምን ለእኔ አልተደረገ ብለው በልጆች ግፊት እና በተለያየ የባህል ግፊት ምክንያት ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚያወጣ የነበረውን ያን እያዳነ ነው። ሁለተኛ ማህበረሰብ አሁን እንደየ አቅሙ እንዲኖር ተግባብቶ ተደማምጦ እንዲኖር የሚያደርግ ነው።»

ከሰርግ ያልተናነሰ ወጪ የሚያስከትሉ ልማዶች

በአካባቢው ሽምግልና፣ ቅልቅልና መልስ ከሰርግ ያልተናነሰ ወጪ በማስከተል ነዋሪዎችን ሲያማርሩ የቆዩ ልማዶች መሆናቸው ተገልጿል።

ኢሳያስ ገላው

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

 

Edited by:ሸዋዬ ለገሠ/Shewaye Legesse
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW