የሰብል ስብሰባ ዘመቻ
ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 13 2015
በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን የደረሱ ሰብሎችን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል በዞኑ ያሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ተማሪዎች በሰብል ስብሰባ ላይ መሆናቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፣ የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ ባለፉት ሶስት ቀናት በተሰራው የሰብል ስብሰባ ስራ ከ84 ከመቶ በላይ ሰብል መሰብሰቡን አረጋግጧል፣ የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት የአማራ ክልልን ጨምሮ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባዎች ቀላል ዝንብ ሊጥል እንደሚችል ተንብየዋል፡፡
የበጋው ደረቅ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚስተዋልበት ወቅት በመሆኑ በቀጣዮቹ ቀናት በአረብ ምድር ላይ ያለው ዝቅተኛ የአየር ግፊት እንደሚጨምርና በዚህም ምክንያት ቀላል ዝናብ ሊያስከትሉ የሚችሉ የዳመና ሽፋኖች በአንዳንድ አካባቢዎች መከሰታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት አስታውቋል፡፡
ይህን ተከትሎም በአማራ ክልል በተለይም በምስራቅ ጎጃም ዞን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ እንደሆነ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ከታህሳስ 10-14/2015 ዓ ም በዞኑ ያሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ከ365 ሺህ በላይ ተማሪዎችና ከ20ሺህ በላይ መምህራን በሰብል ስብሰባ መሰማራታቸውን የምስርቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታሁን ፈንቴ ገልፀዋል፡፡
“የሰብል ስብሰባ ስራው በዘመቻ መልክ ለአንድ ሳምንት ሰብስበን የመማር ማስተማር ስራችንን እንቀጥል፣ ለምን አናከናውንም? የሚል አቋም ተወስዶ ከታህሳስ 10 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 14/2015 ዓም መላ ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው ሰብል እየተሰበሰበ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ የሰብል ስብሰባ ዘመቻ መምህራንም ተሳታፊዎች ናቸው፣ 924 አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 72 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሰብል ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ ናቸው ማለት ነው፡፡ በዘመቻው የተሳተፉ ከ360ሺህ በላይ ተማሪዎች ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
የምስራቀረ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ቸኮል በበኩላቸው፣ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎችን ከብክነት ለመታደግ ተማሪዎችና የከተማ ነዋሪዎች በሰብል ማሰባሰብ ስራ በማሰማራት ለመሰብሰብ ከደረሰው ሰብል ውስጥ 84 ከመቶ የሚሆነው ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ መሰብሰቡን አብራርተዋል፡፡
“614ሺህ 489 ሄክታር በመኸር ተሸፍኗል፣ ይህ በምስራቅ ጎጃም ታሪክ የመጀመሪያው ነው፣ ከፍተኛ የማሳ ሽፋን ያለው ነው፣ ባለንበት ወቅት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስላለ፣ ይህ ደግሞ በሰብል ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያስከትላል፣ ከዚህ አደጋ አርሶ አደሩን ለመታደግ፣ ታስቦ ተማሪዎቹን፣ ለአንድ ሳምንት ያክል ወላጆቻቸውን እንዲያግዙ መምህራንም ይህን እንዲያስተባብሩ የከተማ ነዋሪዎችም ወጣቶችም በተመሳሳይ ይህን እንዲያስተባብሩ የሚያደርግ አቅጣጫ ተቀምጦ ሥራ እየተሰራ ነው ያለው፣ እስካሁን በጣም አሪፍ ነው ይህን ዘመቻ ከማድረጋችን በፊት የሰብል አሰባሰብ ስራችን 50 ከመቶ አልደረሰም ነበር፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ 84 ከመቶ በላይ ተሰብስቧል፣ በዚህ ሳምንት የመጣ ውጤት ነው፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ምርት ከሰበሰቡ አርሶ አደሮች መካከል የደጀን ወረዳ ነዋሪው አቶ ሀሳቤ ተረፈ አንዱ ናቸው፡፡
“ በገንዘብ የቀን ሰራተኛ እየገዛን እናሳጭዳለን፣ ልጆችም አሉኝ፣ ሰሞኑን ደግሞ ተማሪዎችም አሉ፣ ትምህርት ቤት ዝግ ስለሆነ ልጆችም አሉ ተማሪዎች ያጨዱት ሰኞና ማክሰኞ ነው፡፡”
በምስራቅ ጎጃም ዞን የአማኑኤል አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ይሁን ጌታቸውና በትምህርት ቤቱ የ12ኛ ክፍል ተማሪው ሳሙኤል አስማረን አስተያየት ጠይቀናል፡፡
(መምህር ይሁን ጌታቸው)፣ “የዘጋነው ከታህሳስ 10 እስከ 14/2015 ዓ ም ነው፣ ሁሉም የትምህርት ቤቱ ተማሪዎችና መምህራን አሁን ያለውን ወቅታዊ ዝናብ አስመልክቶ፣ ሰብል ለመሰብሰብ ተሰማርተዋል ማለት ነው፡፡ ”
(ተማሪ ሳሙኤል አስማረ)፣ “ የአማኑኤል ዙሪያ ተማሪ ነኝ፣ የቤተሰቦቻችን ሰብል ለመሰብሰብ ከታህሳስ 10 እስከ 14/2015 ዓም ለ5 ቀናት ያክል ትምህርት ቤት ተዘግቷል፣ የቤተሰቦቼን ሰብል እየሰበሰብኩ ነው፣ ከጎረቤቶቻችን፣ ከሰፈር ሰዎች ጋ በደቦ ነው ሰብል እየሰበሰብን ያለነው እየተሰበሰበ ነው ጥሩ እየሄደልን ነው፡፡”
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚትዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂ መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አሳምነው ተሾመ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በምርት ላይ ብዙም ተፅኖ የሌለው ቀላል ዝናብ እንደሚጥል ጠቁመው ሆኖም አርሶ አደሩ ምርቱን እንዲሰበስብ አሳስበዋል፡፡
“ደረቅ ፀሐያማውና ነፋሻማው የአየር ሁኔታ የሚያመዝንበት ወቅት ነው፣ በክረምት የሚዘሩ አዝርዕት ለመሰብሰብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን በሚቀጥሉት ቀናት በአረብ ምድር ላይ፣ በቀይ ባህር አካባቢ የተወሰነ ዝቅተኛ የአየር ግፊት እየተፈጠረ ስለሆነ ያ ደግሞ ለብዙ የአገራችን አካባቢዎች ለደመና ሽፋን መጨመር አዎንታዊ ሚና ይኖራል ማለት ነው፤ ስለዚህ በብዙ አካባቢዎች ላይ የደመና ሽፋን መጨመር ሊኖር ይችላል፣ ስለዚህ ማህበረሰቡ የደረሱ ሰብሎችን በተለይም ከወዲሁ መሰብሰብ አለበት፡፡ ”
ባለሙያው አክለውም የሚገኘውን ዝናብ አርሶ አደሩ ለተጨማሪ የምርት ስራ እንዲያውሉ መክረዋል፡፡
በዋናነት ሰሞኑን እየተሰበሰቡ ያሉ ሰብሎች ጤፍና ስንዴ መሆናቸውንም ለማወቅ ችለናል፡፡
በአማራ ክልል በ2014/15ዓ ም የምኸር ወቅት 4.72 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑንና 143 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ