የሰብአዊ መብት ጥሰት መቀጠል፤ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አባቶች የመቀሌ ጉዞ እና ሱዳን
ዓርብ፣ ሐምሌ 7 2015
በኢትዮጵያ ተባብሶ የቀጠለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የመብት ተሟጋቾች ስጋት ፤ ወደ ትግራይ ያቀኑት የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን አባቶች ያልሰመረ ጉዞ ፤ እንዲሁም የሱዳን ተፋላሚዎች ለማቀራረብ ያለመው የኢጋድ እና ሌሎች የሱዳን አጎራባች ሃገራት የሰላም ጥረት የሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ትኩረት ነው ፤ በኢትዮጵያ መልኩን ቀይሮ በቀጠለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና በመብት ተሟጋቾች ስጋት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አባቶች የመቀሌ ጉዞን እንዲሁም የሱዳንን ቀውስ ለመፍታት ጥረት በሚደረገዉ ጥረት ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ይቃኛል።
ባገባደድነዉ ሳምንት ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ግልገል በለስ ከተማ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው 18 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው፤ ሌሎች በርካቶች መቁሰላቸዉ ተዘግቧል።ጥቃቱን ተከትሎ ቁጥራቸው በውል ያልተገለጸ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ አጎራባች ቀበሌዎች እና ወረዳዎች ለመሰደድ ተገደዋል።በጥቃቱ ምክንያት መንግስት ለሰላማዊ ሰዎች ተገቢውን ከለላ አልሰጠም በማለት እየተወቀሰ ነዉ። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ መልኩን የቀየረ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ መሆኑን ኢሰመኮ ከትናንት በስትያ ባወጣው መግለጫ ዐስታውቋል። ዜጎች ተገደው ይሰወራሉ፣ ተጠርጣሪዎች ኢ ሰብአዊ በሆነ መልኩ ይያዛሉ ሲል በመግለጫው ወቅሷል ። በዚሁ ላይ በርካቶች ሃሳባቸውን በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ገጾች ተቀባብለዋል።
ስሜ ማማሩ የተባሉ በፌስ ቡክ ባጋሩት ሃሳብ የሀገሪቱን ዜጎች እንደ ሶስተኛ ዜጋ በመቁጠር መንግስት ያፍናል፣ ይገላል፣ ፣ያፈናቅላል። ታጣቂዎችም ከመንግስት ጋር በመናበብ ያንኑ ያደርጋሉ ፣ ሀገር እና ህዝብ ያወቀው ሃቅ ነው » ብለዋል።
እንዴ ወሎ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው « በሰብአዊ መብት በኩል በጭራሽ ከለላ የለም ፤ ሰው ወጥቶ መግባት እየከበደው ነው » ብለዋል።
ሀብታሙ ደመቀ የተባሉ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ላይ ወቀሳ አዘል ሃሳብ ባሰፈሩበት አስተያየታቸው « ኮሚሽኑ አካፋን አካፋ በማለት እየሆነ ያለውን ነባራዊ ችግር በጥናት ላይ ተመስርቶ በግልጽ አማርኛ ማስቀመጥ ሲገባው ለሴራ ፖለቲከኞቹ ሽፋን የመስጠት ያህል እየሸፋፈነ ሪፖርት ሲያቀርብ በመኖሩ በታሪክ ፊት የተጠያቂነት ድርሻ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ » ብለዋል።
አጉሻ ነሲሃ በበኩላቸው «ጉሙዝ አሁንም ፍትህ እየጠየቀ ነዉ » በማለት ባሰፈሩት ሃሳባቸው ፤የሚናገርለት ሚዲያ ባይኖረዉም፤ የሚመሠክርለት ካሜራ ቢነሳዉም ፤ የሚፅፍለት ጋዜጠኛ ባይወጣለትም፤ የሚወክለዉ አመራር ባይሾምለትም ፤ በአጠቃላይ እንደ ዜጋ ባይቆጠርም መብቱ እስካልተከበረለት ድረስ ያበጠ እያበጠ ይፈነዳታል እንጂ ሀቁን ደብቆ ማስመሠል አገርን አታስቀጥልም» ብለዋል።
ፍቅር ያሸንፋል በሚል ስም የግልገል በለሱን ጥቃት በተመለከተ ፌስ ቡክ ላይ በሰፈረ አስተያየት ፤ ይህን ያደረገው በመንግስት የሚቀለብ ሽፍታ ቡድን ሲሆን ብሬን፣ላውንቸር፣እና ሌሎች መሳሪያዎችን እንደታጠቀ በግልገል በለስ ከተማ ውስጥ በየሆቴሉ የፈለጉትን ይጠቀማሉ፤ አይከፍሉም ፤ ኬላ ዘርግተው ብር ይቀበላሉ ፤ ከልካይ የላቸውም ፤ አሁን ደግሞ በታጠቁት መሳሪያ ሰውን ሲጨፈጭፉ ሲገድሉ አድረዋል። ገዳዩ ቡድን ከገደለም በኋላ ተመልሰው መንግስት ወዳዘጋጀላቸው ካምፕ በመመለስ እንደተለመደው በሬ ታርዶለት ሲመገብ ውሏል። መንግስት ባለበት ሀገር እንደዚህ ግፍ እየተፈፀመ ነው።» ብለዋል።
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህ ቤክርስትያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ማትያስ የተመራ የአባቶች ልዑክ ወደ ትግራይ መቀሌ ተጉዞ ነበር ። ልዑካኑ ወደ ትግራይ ሲያቀኑ በሰሜን ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት የተሻገረውን ጦርነት ተከትሎ በኃይማኖቱ አባቶች መካከል ሻክሮ የነበረውን ግንኙነት ለማሻሻል ያለመ ነበር ተብሏል። ነገር ግን ልዑካኑ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ጋር ከመገናኘት ውጭ ከትግራይ አባቶች ጋር መገናኘት አለመቻላቸው ተዘግቧል። ምክንያቱ ደግሞ የትግራይ አባቶች ልዑኩን ለማግኘት አለመፈለጋቸው እንደሆነ ነው የተገለጸው። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ልዑካኑን ተቀብለው አነጋግረዋል። መንግስታቸው በክልሉ የኃይማኖት አባቶች ውሳኔ ጣልቃ እንደማይገባም ለልዑካኑ ገልጸውላቸዋል። አባ ማትያስ በዚሁ ጊዜ በጦርነቱ ምክንያት “በሕዝቡ ላይ የደረሰው መከራ ከባድ እና ታይቶ የማይታወቅ ነው” በማለት የቅዱስ ሲኖዶስ ይፋዊ ይቅርታን በወቅቱ አስታውሰዋል። ለጦርነት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ቤተክርስትያኒቱ የለገሰችውን «የ20 ሚሊዮን ብር ድጋፍም »ለመስተዳድሩ አስረክበዋል። የቤተክርስትያኒቱ አባቶች የመቀለ ጉዞ እና ያልተሳካውን የእርቅ ፍላጎት በተመለከተ በርካቶች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካንነት አስተያየታቸው ሲያጋሩ ቆይተዋል። ከእነዚህ ውስጥ
በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ቲቦር ናዥ በትዊተር ባሰፈሩት መልዕክት ፤ የአባቶቹን ጉዞ ተምሳሌት ሲሉ ነው የገለጹት ። አምባሳደር ቲቦር በጉዞው «ቤተክርስትያኒቱ የሰሜኑን ጦርነት ለማስቆም ብዙ ጥረት ባታደርግም አሁን ቅዱስነታቸው የመሩት ልዑካን ይፋዊ ይቅርታ ለመጠየቅ እና ችግሩን ለማከም ወደ ትግራይ መጓዛቸው አርአያነት ያለው ተግባር ነው » ብለዋል።
የአምባሰደሩን መልዕክት ተከትሎ በርካታ ሃሳቦች ከግራ እና ከቀኝ ተሰጥቶበት ተመልክተናል። ከእነርሱ ውስጥ አንዱ አልማቃህ በሚል ስም የሰፈረ አስተያየት « ተምሳሌታዊነቱ ከታየዎት እርስዎስ መቼ ነው በይፋ ይቅርታ ለመጠየቅ የሚመጡት በማለት ጠይቋል።
አማራው በሚል ስም አማባሰደሩ ላሰፈሩት መልዕክት አዘል ሃሳብ አስተያየታቸውን ሲሰጡ « የተከበሩ አምባሳደር ከይቅርታ ጋር ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ በቅጡ የገባዎት አይመስለኝም » ይላል። « ራስዎትን በኢትዮጵያ ጉዳዮች ለውጥ ሊያመጡ እና ህይወት ሊያድኑ የሚችሉ እንደሚመስላቸው እንደ አንዳንድ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ይቆጥራሉ ፤ ያ ነው የሚሰማኝ» ብለዋል።
ኤልሳ ትግራይ ፤ ኢትዮጵያ ትግራይን መልሶ መገንባት በሚል መቶ ሚሊዮን ብሮችን ብትሰበስብ እንኳ ይህ ምንም አይደለም ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቀዳሚ ጉዳይ ሊሆን የሚገባዉ የትግራይ ተፈናቃዮችን ወደ ቄዬአቸው ማስመለስ ነው።
ዳዊት ጆቴ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው እዚያው ቲውተር ላይ ባሰፈሩት ሃሳብ ፤ «እኔ እንደ ሰው ማስመሰል አልወድም» ይላሉ ። እንደ እኔ እንደኔ አሉ ዳዊት « ከኃይማኖት አባቶቹ ይልቅ ፖለቲከኞች ተሽለውኛል » ይላሉ ። « ፖለቲከኞቹ እርስ በእርስ ይቅር በተባባሉበት በዚህ ጊዜ የኃይማኖት አባቶቹ ይቅር መባባል ከብዷቸዋል » በማለት ሃሳባቸውን አስፍረዋል።
አጉሻ ነሲሃ በሚል ስም ፌስ ቡክ ላይ በሰፈረ ሃሳብ ደግሞ « ሕገ መንግስትን ማስከበር ትግራይ ቀረ ፐ አቤት ጥበብ » ብለውታል
ክንዱ መሌ ወልዴ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸው ፌስ ቡክ ላይ ባሰፈሩት አስተያየት <<አይደረግም አንድ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ነኝ ከሚል ግለሰብ ሌላው ህዝብ ከነሱ ምን ይማራል?መቸስ ቂም ይዞ ፆለት ሳል ይዞ ስርቆት አይቻልም አይደል የሚባለው>> ብለዋል።
ቦኬ ዎን የተባሉም እንዲሁ በተመሳሳይ ባጋሩት ሃሳባቸው <<ታዲያ ተራው ህዝብ እርስ በእርስ ቢጠላላና ቢበላላ ምን ይገርማል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ይቅርታን ነበር የሰበከው። በእናንተ ችግር ነው ህዝቡ ላይ መዓት የወረደው ። ትውልዱን በስነምግባር አንፃችሁት ቢሆን ኖሮ ማዓት ባልመጣ። እኔም በግሌ ልቤ ደነደነ። የሀገር ጥላቻ ብቻ ሳይሆን ለይቶ መጥላትም አለበት ያሳዝናል>>
መፍትሄ ያልተገኘለት የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ያሳሰባቸው የሱዳን አጎራባች ሃገራት ተፋላሚዎቹን ወደ ሰላም ንግግር ለማምጣት ያለመ ንግግር የኢጋድ መሪዎች ሰሞኑን አዲስ አበባ ፤ ከትናንት ጀምሮ ደግሞ ከኢጋድ ውች ያሉ ሌሎች የጎረቤት ሃገራትን ጨምሮ ካይሮ ግብጽ ውስጥ እየተካሄደ ነው። የጦርነቱ ዳፋ ጭምር ያሳሰባቸው ሃገራቱ ተፋላሚዎቹን ወደ ክብ ጠረጴዛ ለማምጣት ይጣሩ እንጂ ተፈላሚዎቹ ግን አንደኛው በሌላኛው ላይ ድል የመቀዳጀት ዜና ሲያውጁ እየተሰሙ ነው። መሪዎቹ ግን በአዲስ አበባው ስብሰባቸው ስብሰባቸው የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ሱዳን የመላክ ዕቅድ አቅርበዋል። ይህንኑ በተመለከተ ተስፋዬ ወምህረት በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየት
«ሱዳን አሁን ባለበት ሁኔታ ሰላም አስከባሪ እንላክ የሚለው ሀሳብ "ሰላም አስከባሪ" የሚለው ፅንሰ ሀሳብም ሆነ የተልዕኮው ተግባራት ምንና መቼ እንደሆነ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው የሚመስለኝ።
የሰላም አስከባሪ ሀይል ሚና እንደ ስሙ ጦርነት ወይም ግጭት በቆመበት ሰአት የሚሰማራ እንጂ በውጊያ መኽል ሚና እንዲኖረው አይደለም።» ብለዋል።
ካሳሁን ፋንታሁን በበኩላቸው ፤ አይ አዲስ አበባ የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች ነው ቅሉ ! » ሲሉ ጌታቸው ማሞ በበኩላቸው ፤ አይ የእኛ አፍሪቃውያን ነገር አርቆ ማሰብ ተሳነንኮ ይላሉ ፤ «በሱዳን ንጹኃን እያለቁ ነው። ለስልጣን ብቻ የቋመጡ መሪዎች ሀገሪቷን በደም ጎርፍ እያጠቧት ነው፤ አዝናለሁ ፣ ይህ ችግር እኛ ሀገርም አይከሰትም አይባልም መጠንቀቅ ነው እንጂ » የሚል ሃሳብ አስፍረዋል።
ሰለሞን ተሻለ ደግሞ « አላወቅነውም እንጂ እኛምኮ ከእነርሱ አልተሻልንም » ብለዋል። የሆነ ሆኖ በሱዳን ተፋላሚዎች ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጥ ከሚችል አንዳች ስምምነት ካልደረሱ ፤ ቀውሱ ከሱዳን ባሻገር ለወትሮም በተወሳሰበ ችግር ውስጥ ለሚገኘው የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ሃገራት መትረፉ አይቀርም ። መሪዎቹ ተፋላሚዎቹን በእርግጥ ገፍተው ወደ ሰላም ያመጧቸው ወይስ ከንቱ ድካም ሆኖባቸው ይመለሱ ይሆን ? ለዛሬ ይብቃን፤ ጤና ይስጥልን !
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ