1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችአፍሪቃ

የሰብአዊ ቀውስና የእርዳታ ጥሪ በኮንጎ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ቅዳሜ፣ የካቲት 22 2017

ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክልፍ የተቀሰቀሰው ግጭት አልሰከነም። በሩዋንዳ ይደገፋል የሚባለው M 23 አማጺ ቡድን በተቆጣጠረው ቡኩቩ በተባለችው መንደር ትናንት ሰልፍ ሲያካሂድ በተከሰተው ፍንዳታ ቢያንስ 11 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።

ምሥራቅ ኮንጎ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የM23 አማጽያን
ምሥራቅ ኮንጎ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የM23 አማጽያንምስል፦ Jospin Mwisha/AFP

የሰብአዊ ቀውስና የእርዳታ ጥሪ በኮንጎ

This browser does not support the audio element.

ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ ደግሞ ቆስለዋል። የኪንሻሳ መንግሥት እና አማጺው ቡድን በጥቃቱ አንዳቸው ሌላቸውን እየከሰሱ ነው። በስፍራው የተገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥቃቱ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ባይ ናቸው። የመጀመሪያው ፍንዳታ በቦታው የነበሩትን አደናገጠ። ከሁለተኛው ፍንዳታ አስቀድሞም ሰው ራሱን ለማዳን መራወጥ ጀመረ። በዚህ መሀል የሰው ደም እና ጫማ በየቦታው ተበታትኖ ይታይ እንደነበር የአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘጋቢ ተናግሯል። ጉዳት የተደረባቸውም ለእርዳታ ሲጣሩ ተመልክቷል። የሞቱትን ለመቅበር በሐይቁ ላይ ሲጓዙ ከነበሩት አንዷ የሆነውን እንዲህ ነው የገለጹት፤

«አዲሶቹ መሪዎች የሚሉትን ለመስማት ወደ ሰልፉ ሄዱ። ማምለጥ አልቻሉም፤ እዚያው ነው የሞቱት። ለዚህ ነው ወደ ቀብር የምንሄደው፤ ምንም ማድረግ አንችልም። እንደውም ሐይቁ ላይ መንቀሳቀስ በመጀመሩ ደስ ብሎናል።»

የአማጺው ቡድን የተጠናከረው ጥቃት

አካባቢውን የM23 አማጽያን ከተቆጣጠሩት አንድ ወር ገደማ ሆኗል። ሐሙስ ዕለት በተዘጋጀው የአደባባይ ሰልፍ ላይ አማጺው ቡድን አባል የሆነበት ስብስብ የበላይ ሀላፊ ኮሎኔል ናንጋ ንግግር አድርገው ከመድረኩ ሲወርዱ ፍንዳታው መከሰቱን ነው የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘጋቢ የገለጸው። የፍንዳታው ምክንያት አልተገለጸም። ፕሬዝደንት ፊሊክስ ቼሲኬዲ ድርጊቱን «አስከፊ የሽብር ተግባር» ብለውታል። 

በማዕድን ሀብት የበለጸገው ምሥራቃዊ ኮንጎ የግጭት ትርምስ ቀጣና ከሆነ በመሰንበቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ሕይወታቸው ከተመሰቃቀለ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል። ስፍራው እንደማግኔት የሳባቸው የአጎራባች ሃገራት በአማጽያን ሽፋን ሰላም ከራቀው አካባቢ በረከቱን ለመቋደስ እጃቸውን አስረዝመዋል በሚል በየጊዜው ይወቀሳሉ። ክሱን ውድቅ ቢያደርጉም።

ሐሙስ ዕለት በደረሰው ፍንዳታ የሞቱት በርካቶች መሆናቸውን የሚገልጹት ከአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ፤ ያላባራው ጦርነት የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖራቸው ማድረጉን ይናገራሉ።

«በእውነቱ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው፤ ቡኩቩም ጎማም ወንዶች ሞተዋል። ሰዎች አልተረጋጉም፤ ያልተረጋጉት ጦርነት ስለቀጠለ ነው፤ እናም እንደሚታወቀው ጦርነት ካለ ማንም ሊረጋጋ አይችልም፤ ከምንም በላይ የተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ አይኖርም፤ ምክንያቱም ጥቃቶች እዚህም እዚያም አሉ።»

ለስደት የተዳረገው ሕዝብ ሰቆቃ

አማጺው ቡድን M23 በርካታ ሕዝብ የሚኖርባት ጎማ ከተማን ባለፈው ጥር ወር ላይ ነበር የተቆጣጠረው። ከዚያም ጎረቤት ወደሆነችው ቡኩቩ ገባ። በዚህ ጊዜ ውስጥ በሺህ ዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ በርካቶችም ተፈናቅለዋል። ቡድኑ ጥቃቱን አጠናክሮ ወደ ደቡብ ኪቩ ክፍለ ሃገር በመግፋት ከቡሩንዲ ድንበር አቅራቢያ ውጊያውን ቀጠለ። በዓለም እጅግ ውድና ብርቅ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶች ኮልታን፤ ወርቅ፣ ኒኬል፤ ኮባልትና መዳብን ጨምሮ በዚህ አካባቢ በብዛት ተከማችተው እንደሚገኙ ይነገራል። አማጺ ቡድኑ እነዚህን ማዕድናት በሕገወጥ መንገድ አውጥቶ ለገበያ እንደሚያቀርብ ይታመናል።

 

የአካባቢው ኅብረተሰብ ግን በማባራው ግጭት ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው። የተመድም በከፋ ሰቆቃ ውስጥ ለሚገኙት የኮንጎ ተፈናቃይ ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ከሀገሪቱ መንግሥትና ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን የገንዘብ ድጋፍ ጥሪ አቅርቧል። የተመድ የዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ፤

«ዛሬ ኪንሻሳ ውስጥ ከተጓዳኞቻችን ጋር እና ከኮንጎ መንግሥት ጋር በጋራ በ2025 የሰብአዊነት ምላሽ የሚሰጥ እቅድ ይፋ አድርገናል። እቅዱ ሕይወት አድን እርዳታና 7,8 ሚሊየን የሚሆኑ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ወገኖችን ጨምሮ ከ11 ሚሊየን ለሚበልጡ ወንዶች፤ ሴቶች እና ልጆች ከለላ ለመስጠት 2,5 ቢሊየን ዶላር ይፈልጋል።»

በግጭት ሰቆቃ ውስጥ የሚገኙት የምሥራቅ ኮንጎ አካባቢ ነዋሪዎች በወረርሽኝ እና በተፈጥሮ አደጋዎችም እየተጎዱ መሆኑ ነው የተገለጸው። የተመድ እንደሚለው 21,2 ሚሊየን የኮንጎ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ውጊያው ባለማባራቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ የኮንጎ ዜጎች ወደ ቡሩንዲ ለመሻገር መገደዳቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ። እስካሁንም ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ቡሩንዲ ግዛት ገብተዋል። ብዙዎቹም ሩሲዚ ወንዝን በዋና ማቋረጣቸው ነው የነገረው። በዚህ መንገድ ከሞት ሲሸሹም ከ20 የሚበልጡት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ቡሩንዲ መድረስ የቻሉት እዚያው ኮንጎ በአካባቢያቸው ቢቆዩ ኖሮ በአማጺው ቡድን M23 ተገደው ለውትድርና ይመለመሉ እንደነበር ነው የተናገሩት። አማጽያኑ በጥቃታቸው እየገፉበት በመሆኑ ግን ጎረቤት ቡሩንዲም ገብተውም ቢሆን የደኅንነታቸው ጉዳይ አስተማማኝ አይደለም።

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW