1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ 21 ሰዎች ግድያ በሶማሌ ክልል

ሐሙስ፣ መጋቢት 28 2009

በኢትዮጵያ፤ በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጎርጎሮሳዊዉ  ሰኔ 2016 በ 21 ሰወች  ላይ የተፈፀመዉ ግድያ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ «ሂዉማን ራይትስ ወች»  የተባለዉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አሳሰበ።

Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

No Justice in Somali Region Killings - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

ድርጅቱ ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ እንዳመለከተዉ ግድያዉ በክልሉ ልዩ ሀይል ፓሊስ የተፈጸመ ቢሆንም  እስካሁን ድረስ  ፍትህ አለማግኘቱ አሳዛኝ ነዉ ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ዛሬ ከናይሮቢ ባወጣዉ መግለጫ እንዳመለከተዉ በሶማሌ ክልል ጃማክ ዱባድ በተባለች መንደር  በክልሉ« ልዩ ሀይል » በተባሉ ፓሊሶች ቢያንስ 21 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል። በጎርጎሮሳዊዉ ሰኔ 2016 የአንድ የፓሊስ መኮንን በአካባቢዉ ነጋዴወች  መቁሰሉን ተከትሎ የልዩ ፓሊስ አባላቱ ወደ መንደሪቱ ዘልቀዉ በመግባት ፤ተኩስ ከፍተዉ  14 ወንዶችንና 7 ሴቶችን መግደላቸዉን ከግድያዉ አምልጠዉ ወደ ጎረቤት ሶማሌ ላንድ የተሰደዱ የመንደሪቱ ነዋሪወችን አነጋግሬ አረጋግጫለሁ ሲል ድርጅቱ በመግለጫዉ አመልክቷል። ከግድያዉ በተጨማሪም በቤትና በሱቆች ላይ ዘረፋ መካሄዱን ገልጿል። ይሁን እንጅ ድርጊቱን በተመለከተ እስካሁን ድረስ በወንጀል የተጠየቁና ለፍርድ የቀረቡ ሰወች አለመኖራቸዉን መግለጫዉ ጠቅሶ የኢትዮጵያ መንግስት በአፋጣኝ ምርመራ ሊያካሂድ ይገባዋል ሲል አሳስቧል። በመንግስት በኩል አሁንም ድረስ ግድያዉ ፍትህ እንዲያገኝ የማድረግ ፍላጎት አለመታየቱ አሳዛኝ ነዉ ሲልም ድርጅቱ ዘርዝሯል። በመሆኑም ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ሊጣራ እንደሚገባ የድርጅቱ የሶማሊያና በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ተመራማሪ ሊቲሽያ ባደር አብራርተዋል።

  «ቢያንስ ቢያንስ ለግድያዉና ለተፈፀመዉ ዘረፋ  ተጎጅወቹ ካሳ ማግኜት አለባቸዉ። ይህ ደግሞ የፌደራል መንግስቱና የክልሉ ባለስልጣናት ሀላፊነት ነዉ። በእዉነት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት መጀመር ያስፈልጋል። ይህ ክስተት ብቸኛ አይደለም ባለፉት 2 አስርተ አመታት በተደጋጋሚ የተፈጸመ ነዉ።በመሆኑም ትኩረት የሚፈልግ ነዉ። ስለዚህ የክልሉ ባለስልጣናት ቦታዉን ለዓለም አቀፍ ምርመራ ክፍት እንዲያደርጉ ለመገፋፋትለኢትዮጵያ መንግስት ጊዜዉ አሁን ነዉ።ለምሳሌ የተባበሩት መንግስታት ባለሙያወች ይህንን የግድያወንጀል እንዲያጣሩ መፍቀድ ያስፈልጋል። »

ምስል DW/J. Jeffrey

 ድርጅቱ በጎርጎሮሳዊዉ ከታህሳስ እስከ የካቲት 2017 በ31 የመንደሪቱ ነዋሪወች ላይ አደረኩት ባለዉ ማጣራት  በክልሉ ያለፍርድ እስር፣ ግድያና ማሰቃየት በልዩ ሀይል ፓሊስ ይፈጽማል ብሏል። በቅርብ አገኘሁት ባለዉ መረጃ መሰረት ደግሞ  ከሶማሌ ክልል ዉጭ በኦሮሚያ ክልልና ሶማሊያ ዉስጥም ድርጊቱ ይፈጸማል ሲሉ ተመራማሪዋ ባደር ይናገራሉ።
«ታዉቃላችሁ የልዩ  ሀይል ፓሊስ ከሶማሌ ክልል ዉጭ በኦሮሚያ ክልልና በሶማሊያ ዉስጥም ይህንን ድርጊት መፈጸም መጀመሩን ማስረጃወች አሉ። እኔ እነደማስበዉ አሁን ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነዉ።»

በሶማሌ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት መቀጠሉን  ባደር ገልጸዉ ችግሩን ለመፍታት የፌደራልና የክልሉ መንግስት እንዲሁም የአለም አቀፉ ህብረተሰብ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አስገንዝበዋል። የሀገሪቱ መንግስትም ቢሆን ለነጻ የመገናኛ ብዙሃንና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ክልሉን ክፍት ሊያደርግ ይገባል ሲሉም ጨምረዉ ገልጸዋል።መግለጫዉን በተመለከተ የመንግስትን ምላሽ ለማካተት ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም።
ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW