1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በመግለጫው የተመላከቱ ጥሰቶች

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ የካቲት 26 2018

የአውሮፓ ሕብረት አባላቱንና ሌሎችን ጨምሮ 41 ሀገሮችን ወክሎ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት የሲቪክና የመገናኛ ብዙኃን ምሕዳሩ በብርቱ ሊጤን እንደሚገባ አሳስቧል። ይህ ጥሪ የቀረበው በስዊዘርላንድ ጃኔቫ በመከናወን ላይ ባለው 61ኛው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ነው።

በስዊዘርላንድ ጃኔቫ በመከናወን ላይ ያለው 61ኛው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤ
በስዊዘርላንድ ጃኔቫ በመከናወን ላይ ያለው 61ኛው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤምስል፦ Fabrice Coffrini/AFP/Getty Images

ተቀዛቅዟል የተባለው የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ የሲቪክ ምኅዳር መጥበብ እጅግ እንዳሳሰባቸው የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ በጀኔቫን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ለ61ኛውየተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በቀረበ ሪፖርት ላይ ገለፁ።

ሃገራቱ ኢትዮጵያ ውስጥ «በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ማስፈራራትና ትንኮሳ፣ የዘፈቀደ እሥራት፣ የነጻ ብዙኃን መገናኛ ተቋማት እና ጋዜጠኞች መታሰርን ጨምሮ የሲቪል ምኅዳር መጥበብ» እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በፊት እንዳይፀድቅ ኢሰመኮ ውትወታ እያደረገ መሆኑን ሰሞኑን ገልጿል። ሲቪክ ድርጅቶች ግን በጉዳዩ ላይ አሁንም ሥጋት እንዳላቸው እየገለፁ ነው።


በመግለጫው የተመላከቱ ጥሰቶች ምንድን ናቸው?


የአውሮፓ ሕብረት አባላቱንና ሌሎችን ጨምሮ 41 አገሮችን ወክሎ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት የሲቪክና የመገናኛ ብዙኃን ምሕዳሩ በብርቱ ሊጤን እንደሚገባ አሳስቧል። ይህ ጥሪ የቀረበው በስዊዘርላንድ ጃኔቫ በመከናወን ላይ ባለው 61ኛው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ነው።

በኢትዮጵያ ያለው የሲቪክ ምኅዳር የበለጠ የመጥበብ አደጋ ውስጥ መሆኑ ይበልጥ እንዳሳዘነው የገለፀው ሕብረቱና የወከላቸው ሃገራት መገለጫ «የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ቀጣይነት ያለው ማስፈራራት እና ትንኮሳ፣ ነጻ መገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች ላይ ያለው የዘፈቀደ እሥራትን ይጨምራል» ብሏል።

ለሁሉም የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ሙሉ በሙሉ መከበር ነፃ የሲቪል ማኅበረሰብ እና የመገናኛ ብዙኃን ምኅዳር መኖር የግድ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ እነዚህ «ለነፃ እና ፍትሐዊ ምርጫ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው» ይላል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎቿን እንድታከብር እና «የአሁኑን አሉታዊ አዝማሚያ እንድትቀይር» ጥሪ አድርገዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተረዥ ስብሰባውን ሲከፍቱምስል፦ United Nations/Handout/Anadolu/IMAGO

በሰሜን ኢትዮጵያ በቅርቡ የተከሰቱትን ወታደራዊ ግጭቶችን እና ፍጥጫዎችን ጨምሮ የተስተዋሉ ክስተቶችን «በከፍተኛ ሥጋት እየተከታተልን ነው» ያሉት እነዚህ አካላት፣ «ለሲቪሎች እና ለቀጣናዊ መረጋጋት ከባድ መዘዝ የሚያስከትል አዲስ ግጭትን ለመከላከል በሁሉም ወገኖች ፈጣን ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ነው» ሲሉ አሳስበዋል።

በጉዳዩ ላይ የመንግሥትን ምላሽ ለማካተት ወደ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ደውለናል። ኃላፊው «ቅዳሜ የሲቪክ ድርጅቶች ሚና በምርጫ ወቅት» የሚል ውይይት ስለሚደረግ በዚያ ተገኝተን እንድንጠይቅ ጋብዘውናል። በመሆኑም ስለዚህ መግለጫ ቀጥተኛ ምላሽ አላገኘንም።

ሀላፊው ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ግን  ሲቪክ ድርጅቶች «በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ መስኮች የሚያደርጉት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ» ተናግረዋል።


ተቀዛቅዟል የተባለው የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ


የአውሮፓ ሕብረት እና የወከላቸው ሃገራት ባወጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ጀምራው በነበረውና አሁን በተቀዛቀዘውየሽግግር ፍትሕ ሂደት ሥጋት እንዳላቸው ጠቅሰዋል። «የተጠያቂነት ሂደቶችን ጨምሮ ተዓማኒነት ያለው የሽግግር ፍትሕ ለተጎጂዎች እና ለተረፉ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እና እርቅ ለማረጋገጥም ወሳኝ» መሆኑን በማጉላት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ እና በሰብአዊ መብቶች ሕግ ላይ ለሚፈጸሙ ጥሰቶች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ፈጣን እና ወሳኝ ያሏቸውን ርምጃዎችን እንድትወስድ ጥሪ አቅርበዋል። ሰሞኑን መግለጫ ሲሰጡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጀኔቭ ስዊትዘርላንድ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፅሕፈት ቤትምስል፦ Siavosh Hosseini/SOPA Images/ZUMA Press/picture alliance

የአውሮፓ ሕብረት ልዑክ በጀኔቫን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ባወጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሌሎች ተዋናዮች በሙሉ በግጭት አካባቢዎች በተለይ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ «ቀጣይነት ያለውየሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እና በደሎችን ለማስቆም ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስዱ» ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሀገሪቱን የሰብአዊ መብት አያያዝ ይጎዳል በሚል ሥጋት የደቀነውን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ ከ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በፊት እንዳይፀድቅ ውትወታ እያደረገ መሆኑን ገልጿል። ከትናንት በፊት ያነጋገርናቸው አንድ የዘርፉ ተዋናይ ግን ሕጉ ከምርጫው በኋላም ከፀደቀ የሚያስከትለው ያሉት አደጋ ቀላል አይደለም።

አርባ ሁለት የዓለም ሃገራትበኢትዮጵያ የሲቪል ምህዳርየመጥበብ ሥጋት እንዳላቸው ለተባበሩት መንግሥታት ባቀረቡት የጋራ መግለጫ፣ «የሲቪሎች ግድያ እና ጉዳት፣ ማሰቃየት፣ በግዳጅ መሰወር፣ በዘፈቀደ የሚፈጸሙ እሥሮች እና መሰወሮች፣ በሲቪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲሁም በተለያዩ ተዋናዮች የሚፈጸሙ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆኑ የጾታ እና ፆታዊ ጥቃቶች» መኖራቸውን በመግለጽ፣ በአስቸኳይ እንዲቆም ያሳሰበ ጭምር ነው።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW