1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብቶች ይዞታ የገመገመው የተመድ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን መድረክ

ረቡዕ፣ ኅዳር 4 2017

የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብቶች ይዞታ ለአራተኛ ጊዜ ጄኔቫ ላይ ትናንት ገመገመ። አጠቃላይ ወቅታዊ ግምገማ የሚካሄድበት ይህ መድረክ ባለፈው በሦስተኛው የግምገማ ተመሳሳይ መድረክ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሰብአዊ መብት አያያዙን በተመለከተ የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ተመልክቷል።

Schweiz | UN-Zentrale in Genf
ምስል Siavosh Hosseini/SOPA Images/ZUMA Press/picture alliance

የሰብአዊ መብቶች ይዞታ ግምገማ

This browser does not support the audio element.

 በዚህ መድረክ በፍትህ ሚኒስትሩ የተመራ የመንግሥት ልዑካን ቡድን በመገኘት የተሰጡት ምክረ ሃሳቦችን በመፈጸም ሂደት ተገኙ ያላቸውን ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለጉባኤው አቅርቧል። ቀደም ባሉት መድረኮች በሀገሪቱ የሃሳብና መገናኛ ብዙሃን ነጻነት ጋር በተገናኘ ያሉ አፋኝ ሕጎች፤ በጾታዊ ጥቃትና ግጭት ጦርነት ያስከተላቸው ተፈናቃዮችን ችግሮች እንዲሁም ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከቱ የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል።  የልዑካኑ ቡድን መሪ የፍትህ ሚኒስትሩ በላይሁን ይርጋ ባቀረቡት የመንግሥት ዘገባ በምክረ ሃሳብ ለተዘረዘሩት ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ማግኘት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ነው ያመለከቱት።  

ካለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ እስከ ፊታችን ዓርብ ዕለት በሚዘልፈው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች መድረክ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ14 ሃገራት የሰብአዊ መብት ይዞታ ይገመገማል። አጠቃላይ ወቅታዊ ግምገማ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ቡድን የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤቱ አባል የሆኑ 47 ሃገራትን አቀፈ ነው። ሆኖም ግን በግምገማው 193ቱም የመንግሥታቱ ድርጅት አባል ሃገራት መሳተፍ ይችላሉ። የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብቶች ይዞታ በተመለከተ ከመንግሥት፤ ከሀገር ውስጥ እና ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች፤ እንዲሁም ከሲቪክ ተቋማት የሚቀርቡለትን ዘገባዎች ይቃኛል።  

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ይዞታከዚህ ቀደም በጎርጎሪዮሳዊው 2009፤ 2014 እና 2019 ላይም ተገምግሟል። በ2019 ዓ,ም የለውጥ ጎዳና ላይ ናት በሚል ከበርካታ ተሳታፊ ሃገራት አዎንታዊ አስተያየት ተሰጥቷት እንደነበር መረጃዎቹ ያሳያሉ። ትናንት ይህ ግምገማ ከመቅረቡ አስቀድሞ ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተው CPJ ኢትዮጵያ ለፕሬስ ነጻነት ቁርጠኝነቷን ለመድረኩ እንታረጋግጥ ጠይቋል።

 የመንግሥታቱ ድርጅትን የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የግምገማን በተመለከተ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ያሬድ ኃይለማርያም እንደሚሉት ከዚህ በፊት በተሰጡት ምክረ ሃሳቦች መሠረት የተሻሻሉ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ የተባባሱም አሉ። 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW