1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ ቀውስ ስጋት በሶማሊያ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 29 2012

ሶማሊያ ውስጥ ከባድ ጎርፍ፣ የአንበጣ መንጋ ወረራ እና ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተሉት ተፅዕኖ ምክንያት የተከሰተውን ሰብዓዊ ቀውስ ማስወገድ ካልተቻለ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፀጥታውና በፖለቲካው ረገድ የተገኘው መረጋጋት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል እየተነገረ ነው።

Somalia ruft Notstand aus wegen Heuschreckenplage
ምስል picture-alliance/dpa/AP/B. Curtis

ትኩረት በአፍሪካ

This browser does not support the audio element.

ሶማሊያ ውስጥ ከባድ ጎርፍ፣ የአንበጣ መንጋ ወረራ እና ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ባስከተሉት ተፅዕኖ ምክንያት የተከሰተውን ሰብዓዊ ቀውስ ማስወገድ ካልተቻለ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፀጥታውና በፖለቲካው ረገድ የተገኘው መረጋጋት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል እየተነገረ ነው። ይህን የሰብዓዊ ቀውስ ስጋት ለመቀልበስም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ የዕርዳታ ጥሪ ቀርቧል። በሶማሊያ የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የድርጅቱ ኃላፊ ጀስቲን ብራዲ፤ ሶማሊያ ይህን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋም የሚያስችላት አቅም የላትም ይላሉ።

«የሶማሊያ ችግሮችን የመቋቋም አቋም ከጎረቤት ሃገሮች ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው። ይህ በመሆኑም ጎርፉም ሆነ የአንበጣው መንጋ እንዲሁም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ ሰብዓዊ ቀውስ ብቻ ሳይሆን፤ ባለፉት አስርት ዓመታት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ገንዘብ ያፈሰሰበት የሀገሪቱ የፖለቲካ እና የፀጥታ ይዞታ ስኬት ወደነበረበት ሊመልሰው ይችላል።» 

ምስል picture-alliance/dpa/AP/B. Curtis

ይህ እንዳይሆንም ይላሉ ብራዲ፤ ከግሉ ዘርፍ፣ ከሲቪል ማኅበረሰቡ እንዲሁም በሌላው ዓለም ከሚገኙ የሶማሊያ ተወላጆች ጋር ያለውን የትብብር ሥራ አጠናክሮ በሕብረት መሥራት ይገባል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን በጎርፍ ምክንያት ከማዕከላዊ ሶማሊያ ግዛቶች 500 ሺህ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።  ሶማሊያ ግዛቷን ከወረረው የአንበጣ መንጋ ጋር እየታገለች ሲሆን አጋጣሚው የሀገሪቱን የምግብ ዋስትናም አደጋ ላይ በመጣሉ በርካቶች ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳይጋለጡ ተሰግቷል። በተጨማሪም የኮሮና ተሐዋሲ በሶማሊያ እንዳይስፋፋ ጥረት ይደረጋል። 

ካለፈው ኅዳር ወር አንስቶ የተመድ ከሀገሪቱ ባለሥልጣናትና ተባባሪዎች ጋር በመሆን ሶማሊያ ውስጥ በጎርፍ የተጎዱ ወገኖች አስቸኳይ ርዳታ እንዲያገኙ በመሥት ላይ ነው። በዚህም የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታዎችን ከማቅረብ አንስቶ ሕይወት አድን የሆኑ አገልግሎቶችን በስፍራው በሚገኙ ተጓዳኞቹ አማካኝነት ለሕዝቡ እያቀረ ይገኛል። ይህ ተግባርም እስካሁን እንደቀጠለ ነው። የመንግሥታቱ ድርጅት መጠለያዎችን እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ከማቅረብ በተጨማሪም እንደኮሌራ  የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች እና የተመጣጠነ ምግብ እጦትን የሚያስከትሉ ችግሮችን በቅርበት በመከታተል ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ሲረዳ ቆይቷል። 

ምስል AP

በዚህ መሀል ከግማሽ ሚሊየን ሕዝብ የሚበልጥ ተፈናቅሎ ሳለ፤ በቅርቡ በደረሰው ጎርፍ ምክንያት ከአንድ ሚሊየን የሚበልጥ ሕዝብ ተጎድቷል። ጉዳቱ በከፍተኛ ደረጃ ከጸናባቸው አካባቢዎች አንዱ በለድ ወይን ሲሆን አካባቢው ባለፈው ዓመትም የሸበሌ ወንዝ በወረደው ከባድ ዝናብ ሳቢያ ከገደቡ ወጥቶ በመፍሰሱ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ አጋጥሞታል። በአካባቢው የሚገኘው መንግሥታዊ ያልሆነ የልማት ተቋም የፕሮግራም ኃላፊ አብደልካሪም ሁሴን አብዲ እንደሚሉት በወቅቱ 240ሺህ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። 

«ጎርፉ የሰዎችን ንግድና ገበያ እንዳለ ነው የዋጠው። ይህ ደግሞ በርካቶችን ያለገቢ እና የገቢ ምንጭ ባዶ አስቀረ። የሸቀጦች ዋጋ በጣም ናረ፤ አዝመራ በማውደሙ ወደገበያ የሚመጣው በጣም አነስተኛ የምግብ አቅርቦት ዋጋው በጣም ተወደደ።» 

በለድ ወይን በሚገኘው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ የምትገኘው የአራት ልጆች እናት ሀዋ ገዲ እንደ እሷ ላሉት ንብረታቸው ለወደመ በርካታ ቤተሰቦች ርዳታ ጠይቃለች።

 «በጎርፍ ምክንያት ነው ከቡላ ቆዳህ የተፈናቀሉት፤ ውኃ እና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶቻችን በማቅረብ የሚረዱንን ሰብኦዊ ድርጅቶች እናመሰግናለን። ግን ደግሞ ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልገናል። ምግብ እንፈልጋለን፤ የምንበላው ምንም የለንም።»

ምስል AP Graphics

ከጎርጎሪዮሳዊው 1990 ዓ,ም አንስቶ ሶማሊያ 30 ከአየር ንብረት ጋር የተገናኙ አሳሳቢ ገጠመኞችን አሳልፋለች። 12 ጊዜ ድርቅ መትቷታል። ለ18 ጊዜም ጎርፍ አጥለቅልቋታል። ከሦስት ዓመታት በፊት ሶማሊያ ያጋጠማት ኃይለኛ ድርቅ ዜጎቿን ለጠኔ አጋልጦ ነበር።  አሁን ደግሞ ሀገሪቱ እንደሌሎች ሃገራት ሁሉ የኮቪድ 19 ተሐዋሲ ስርጭትን በድንበሯ አካባቢ እየተከላከለች ነው። ሶማሊያ ውስጥ የመጀመሪያው በኮሮና ተሐዋሲ የተያዘ ሰው የተገኘው ባለፈው መጋቢት ወር ነበር። ከዚያ ወዲህም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። አሁን ከ2 ሺህ የሚበልጡ በኮሮና የተያዙ ሰዎች ሶማሊያ ውስጥ አሉ፤ የሞቱት 79 ደርሰዋል። ከበሽታው ያገገሙት ደግሞ ከ400 ይበልጣሉ። በሀገሪቱ ሦስት የኮቪድ 19 መመርመሪያ ማዕከላት በዓለም የጤና ድርጅት ትብብር ተዘጋጅተው በሀርጌሳ ሶማሊ ላንድ ፣ በጋረዌ ፑንትላንድ እና በመቃዲሹ በሶማሊያ ዋና ከተማ እየሠሩ ነው። ወረርሽኙ ከበድ ያለ የማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያው ምስቅልቅልን በመላው ሶማሊያ አስከትሏል። በተሐዋሲው ምክንያት የሥራ ዕድሎች መጥበብ የበርካቶችን ሕይወት አክብዶታል።  ይህ ብቻም አይደለም የአንበጣው መንጋ ሰብሎችን በማውደም ሊያስከትል የሚችለው የምግብ እጥረት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል። የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት እና ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በአንበጣው የተወረሩ አካባቢዎችን ለመርዳት እየተንቀሳቀሰ ነው። እስካሁንም በሀርጌሳ፣ ጋልሙዱግና ፑንትላንድ አንበጣውን የማባረሩ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል። በሶማሊያ የፋኦ ተጠሪ ኢቲኔ ፔተርሽሚት እንደሚሉት ከሆነም የአንበጣው መንጋ በመጪው መስከረም ወር ሶማሊያ ውስጥ ሊበረክት ስለሚችል ሀገሪቱ የከፋ የምግብ እጥረት ሊያጋጥማት ይችላል፤ ወይም ግማሽ ሚሊየን የሚሆን ሕዝቧ ለረሀብ ይጋለጣል።

 

የሱዳን ሰማዕታት አንደኛ ዓመት መታሰቢያ  

ሱዳናውያን ከዓመት በፊት ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ለ30 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩትን የኦማር አልበሽርን አገዛዝ ካስወገዱ በኋላ ተገቢው የማሻሻያ ርምጃ እንዲወሰድ ጎዳና ላይ ወጥተው ድምጻቸውን ሲያሰሙ በርካቶች የተገደሉበትን አንደኛ ዓመት በዚህ ሳምንት አስበዋል። ሰልፈኞቹ ሰማዕታት ያሏቸውን ወገኖቻቸውን ለማሰብ አደባባይ በወጡበት አጋጣሚም ለሟቾቹ ተገቢው ፍትህ እንዲሰጥና ገዳዮችም የእጃቸውን እንዲያገኙ አጽንኦት በመስጠት ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። «አንረሳም ይቅርም አንልም» የሚል በአረብኛ የተጻፈ መፈክር ያነገቡት ሰልፈኞች ጎማዎችን በማንደድ ቁጣቸውን ሲገልጹም ታየታዋል። ረቡዕ ዕለት በተካሄደው ሰልፍ ከተሳታፊዎቹ አንዱ የነበረው መሐመድ ሃይዱብ በዚህ ወቅት አደባባይ ያወጣቸውን ምክንያት ይናገራል።

ምስል Getty Images/AFP/A. Shazily

«ዛሬ በዚህ ሙቀትና የኮሮና ተሐዋሲ ስጋት ባለበት ወደጎዳና የወጣነው በወቅቱ ለተቃውሞ ወጥተው የተገደሉትን በእነሱ ሰማዕትነት ሀገር በመትረፏ ለማስታወስ ነው። በልባችን እናስታውሳቸዋን።»

በወቅቱ ኻርቱም በሚገኘው የሀገሪቱጦር ኃይል ዋና ጽሕፈት ቤት ፊትለፊት ቢያንስ 128 ሰዎች መገደላቸውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መቁሰላቸውን የህክምና ዶክተሮች እና የተቃውሞ ሰልፉ አስተባባሪዎች ይናገራሉ። ባለሥልጣናት ደግሞ የሞቱት 87 ሰዎች ናቸው ባይ ናቸው። ባለፈው መጋቢት ወር ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ለሰብዓዊ መብቶች የሚሠሩ የህክምናባለሙያዎች ቡድን ያወጣው ዘገባ ጥቃቱን ያደረሱት ኃይሎች ግድያ፣ ማሰቃየት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ፆታዊ ጥቃት፣ ሰዎችን በግዳጅ መሰወር እንዲሁም ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶችን መፈጸማቸውን ያመለክታል።  

አልበሽር ከመንበራቸው ከተሰናበቱ ወዲህ የተመሰረተው የሲቪልና ወታደራዊ የሽግግር ባለሥልጣን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር  አብደላ ሀምዶክ ሰልፉ በተካሄደበት ረቡዕ ዕለት ባሰሙት ንግግር ፍትሀዊ ርምጃ እንደሚወሰድ ቃል ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ሰልፈኞቹ በሀገሪቱ አሁን የሚታየው የሽግግር መንፈስ እንዲፈጠር ሕይወታቸውን ለገበሩት ወገኖች የሚጠይቁት ፍርድ ተግባራዊ መሆኑ እንደማይቀር እና ይህ ቃልም እንደማይታጠፍ በቴሌቪዢን በተላለፈው መልእክታቸው ተናግረዋል።  ልጆችና ሌሎች የቤተሰብ አባሎቻቸው የተገደሉባቸው ሰልፈኞች የሱዳንን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት የሚያመለክት ቅርፅ ይዘው በአደባባይ በመውጣት ነው ፍትህ የጠየቁት። የሱዳን ጦር መሪዎች ግን ይህን ክስ ያስተባብላሉ። አልበሽር ከታሰሩ በኋላ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ወደሥልጣን የመጡት የሱዳን የሽግግር ባለሥልጣናት የተፈጸመውን ጥቃት የሚያጣራ ኮሚቴ ቢያቋቁሙም እስካሁን ያቀረበው የምርመራ ውጤት የለም። ቀደም ብሎ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ በሱዳን ወታደራዊ መኮንኖችና አቃብያነ ሕግ የቀረበው የመጀመሪያ የምርመራ ውጤት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችና ሌሎች የፀጥታው ኃይላት በግድያው መሳተፋቸውን አመላክቶ ነበር። ሆኖም ጦሩ ባለሥልጣናት የተወሰደው ርምጃ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ በተሰባሰቡበት አካባቢ ይካሄድ ነበር ያሉትን የአደንዛዥ ዕጽ ሽያጭ ለመከላከል የታቀደ ነበር በማለት ይከራከራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ ባለፈው ጥቅምት ወር አንጋፋ የሕግ ባለሙያ የሆኑት ነቢል አብዲ ምርመራውን እንዲመሩ እና በሦስት ወራት ውስጥ ውጤቱን እንዲያቀርቡ ኃላፊነት ሰጥተው ነበር። አብዲ ለጋዜጠኞ እንደተናገሩት ጉዳዩ ፖለቲካዊ ቃና ያለው ከመሆኑ በላይ በርካታ ራሳቸውን የሚከላከሉ አካላት ያሉበት በመሆኑ ሦስት ወራት ይህን ለማከናወን በቂ ጊዜ አይደለም። እሳቸው እንደሚሉትም ጉዳዩ ኃይል ያላቸውን ሰዎችን ሁሉ የሚያካትት ሳይሆን አይቀርም። ከዚህም ሌላ ምርመራው በኮሮና ተሐዋሲ ወረርሽኝ ምክንያት እየተደናቀፈ ነው። እስካሁን ሱዳን ውስጥ በተሐዋሲው ከአምስት ሺህ ሰዎች በላይ ተይዘዋል፤ የሞቱትም ከሦስት መቶ ይበልጣሉ። በርከት ያለ የዓይን እማኞችን ምስክርነት ያሰባሰቡት ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾች ምርመራው ግልፅነት እንዲኖረው እየጠየቁ ነው። ለሰብዓዊ መብቶች የሚሟገቱት የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉትም ጥቃቱ፤ «በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀልን ጨምሮ ያለመከሰስ መብትን ወደሚያሳጣው ዓለም አቀፍ የወንጀል ደረጃ ከፍ ሊል ይችላል።» በጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ የተሰየሙት የሕግ ባለሙያ እስካሁን መርማሪ ኮሚቴው በርካታ የእማኝነት ቃል እንደደረሰው ቢያመለክቱም ምንነቱን ግን ከማብራራት ተቆጥበዋል። እንዲያም ሆኖ ምንም እንኳን በቂ ማስተማመኛ ቢሰጧቸውም አሁንም እማኝነታቸውን ለኮሚቴው ለመስጠት ፍርሃት ያደረባቸው የተጎጂ ቤተሰቦች መኖራቸውንም አመልክተዋል። ልጃቸውን ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ማለቂያ ላይ የመንግሥት የፀጥታ ኃይላት በሰልፈኞቹ ላይ በወሰዱት ርምጃ ያጡ አንዲት እናት የልጃቸውን ፎቶ እያሳዩ «ይህ ኮሚቴ ለሰማዕታቱ ፍትህ ያስገኛል ብዬ አላምንም።» ነው ያሉት። ለደም አፍሳሾቹ ይቅርታ እንደማያደርጉ እና የሰማዕታቱን መብት ለመጠየቅም ተስፋ እንደማይቆርጡም ተናግረዋል።

ምስል Getty Images/AFP/O. Kose
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW