1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 07 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 7 2013

ለአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) ግጥሚያ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ነገ የፈረንሳይ ቡድን ይጠብቀዋል። ቅዳሜ ዕለት በነበረው የዴንማርክና ፊንላንድ ግጥሚያ አማካዩ ክርስቲያን ኤሪክሰን በድንገት ሜዳ ውስጥ መዝለፍለፉ በርካቶችን አስደንግጧል። በደቡብ አሜሪካው የኮፓ አሜሪካ የእግር ኳስ የመክፈቻ ጨዋታ የብራዚል ቡድን ድል ቀንቶታል።

EURO 2020 | Dänemark - Finnland Christian Eriksen
ምስል Friedemann Vogel/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ለአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) የምድብ ግጥሚያ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ነገ የፈረንሳይ ቡድን ይጠብቀዋል። ቅዳሜ ዕለት በነበረው የዴንማርክ እና ፊንላንድ ግጥሚያ አማካዩ ክርስቲያን ኤሪክሰን በድንገት ሜዳ ውስጥ መዝለፍለፉ በርካቶችን አስደንግጧል። በደቡብ አሜሪካው የኮፓ አሜሪካ የእግር ኳስ የመክፈቻ ጨዋታ የብራዚል ቡድን ድል ቀንቶታል። ዛሬ በኢትዮጵያ አቆጣጠር እኩለ ሌሊት ላይ አርጀንቲና ከቺሊ ጋር ይፋለማሉ።  በፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ግጥሚያ 19ኛ ድሉን ትናንት ያስመዘገበው ኖቫክ ጄኮቪች ከሮጄር ፌዴሬር እና ራፋኤል ናዳል ጋር ተቀራርቧል።  

እግር ኳስ

ባሳለፍነው ዐርብ በጀመረው የአውሮጳ ሻምፒዮና የእግር ኳስ ፉክክር በመክፈቻው ጣሊያን ቱርክን 3 ለ0 ድል ስታደርግ፤ በበነጋታው ቅዳሜ ዕለት ሦስት ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ዌልስ ከስዊትዘርላንድ አንድ እኩል፤ ቤልጂየም ከሩስያ 3 ለ 0 ተጠናቋል። በመላው ዓለም በርካቶችን ያስደነገጠ አጋጣሚ የተከሰተበት ግጥሚያ በዴንማርክ እና ፊንላንድ መካከልም ተከናውኗል። በሁለቱ የስካንዴኒቪያን ሃገራት መካከል የተከናወነው ግጥሚያ በፊንላንድ ታሪካዊ የ1 ለ0 ድል ተጠናቋል።  ብቸኛዋን ግብ በ60ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ጀርመን ሌቨርኩሰን ቡድን ውስጥ የሚጫወተው የ26 ዓመቱ ጆዬል ፖህጃንፓሎ ነው። ዴንማርኮች አቻ ሊያደርጋቸው የሚችል የፍጹም ቅጣት ምት ዕድል አግኝተው በበረኛ ተጨናግፎባቸዋል።

በእለቱ ለኢንተር ሚላን በአጥቂነት የሚጫወተው የዴንማርክ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ተሰላፊው ክሪስቲያን ኤሪክሰን ማንም ሳይነካው በድንገት ሜዳ ላይ ተዝለፍልፎ ወድቋል። በዚህም ምክንያት ጨዋታው ለሁለት ሰአታት ግድም ተቋርጧል። ከዚያም የመጀመሪያው አጋማሽ ቀሪ አራት ደቂቃዎችን ተጫውተው ከአምስት ደቂቃ ረፍት በኋላ ሁለተኛው አጋማሽ ጀምሯል።

ክሪስቲያን ኤሪክሰን ድንገት ተዝለፍልፎ እንደወደቀ የዴንማርክ ቡድን አባላት ከበውትምስል Wolfgang Rattay/AP Photo/picture alliance

ክሪስቲያን ኤሪክሰን

የዴንማርክ እግር ኳስ ቡድን ሐኪም ሞርቴን ቦዬሰን በቅዳሜው ግጥሚያ ክሪስቲያን ኤሪክሰን በምን ምክንያት ተዝለፍልፎ እንደወደቀ እንደማያውቁ ተናግረዋል። ተዝለፍልፎ በወደቀበት ወቅት የልብ ምቱ መደበኛ ስልቱን እንዲከተል የመጀመሪያ ርዳታ እንደሰጡት እሳቸው ግን የልብ ሐኪም አለመሆናቸውን ጠቁመዋል። የልብ ምት ስልቱን ለማስተካከል ደረቱ ላይ የሚጫን መሣሪያ የተጠቀሙትም አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ እና ፈጣን ውጤት እንደተመዘገበም ተናግረዋል።  

የዴንማርክ አሰልጣኝ ካስፐር ሒዩልማንድ በበኩላቸው ዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሃገን በየሚገኝ ሐኪም ቤት የገባው ክርስቲያን ኤሪክሰን አደጋውን በተመለከተ ብዙም ትዝ እንደማይለው ተናግረዋል።  «ብዙም አላስታውስም፤ ይልቅ ስለእናንተ ነው በጣም የተጨነቅሁት፤ እንዴት ሆነላችሁ ሲል መልሶ እንደጠየቃቸውም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ከክርስቲያን ኤሪክሰን አደጋ በኋላ ጨዋታው ለሁለት ሰአታት ግድም ተቋርጦ መቀጠሉን በተመለከተም ቀጣዩን ብለዋል።

«መለስ ብዬ ሳስበው ሁለት አጣብቂኝ ነገሮች ውስጥ የገቡ ተጨዋቾችን በተመለከተ የተሰጠው ውሳኔ የተሳሳተ ይመስለኛል። ተጨዋቾቹ ድንጋጤ ውስጥ ነበሩ፤ የሚወዱት የልብ ጓደኛቸውን ያጡ እንደሆንም በእውነቱ ግራ የተጋቡ ተጨዋቾች እንዲጫወቱ ነው የተደረገው። መጫወት አይገባንም ነበር የሚል ስሜት ይሰማኛል።»

የዴንማርክ አማካይ፦ ክሪስቲያን ኤሪክሰን (ፎቶ ከማኅደር)ምስል HANNAH MCKAY/REUTERS

አሰልጣኝ ካስፐር ሒዩልማንድ አያይዘውም በክርስቲያን ኤሪክሰን ድንገተኛ የሜዳ ውስጥ መዝለፍለፍና መውደቅ ግራ የተጋቡ ተጨዋቾቻቸው ሜዳ ውስጥ ያሳዩትን ብቃትም አወድሰዋል። አሰልጣኙ እንዳሉት ከድንገተኛ አደጋው በኋላ ጨዋታው ሁለት ሰአት ተቋርጦ ዳግም መጀመሩ ተገቢ አልነበረም ይሆን? ሌሎች ጉዳዮችንም አካቶ ስለጫወታው አጠር ያለ ማብራሪያ እንዲሰጠን የሐትሪክ ስፖርት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና አርታኢ ይስሐቅ በላይን በስልክ አነጋግረነዋል።  

በቅዳሜው የዴንማርክ እና ፊንላንድ ጨዋታ የክርስቲያን ኤሪክሰን ድንገት ሜዳ ላይ መዝለፍለፍ በእግር ኳስ ስፖርት አፍቃሪው ዘንድ ብርቱ ድንጋጤ ነው የፈጠረው። መሰል አደጋዎች እጅግ ለሕይወት አስጊ መሆናቸው ይታወቃል። በቅዳሜው አደጋ የዛሬ 18 ዓመት ግድም የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን የመሐል ተጨዋች ላይ የደረሰውን ያስታወሱም አሉ። አማካዩ ማርክ ቪቪያን ፎዬ ቡድኑ ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ከኮሎምቢያ ጋር በነበረው ግጥሚያ ድንገት ሜዳ ውስጥ ተዝለፍልፎ ከወደቀ በኋላ የልብ ምቱን ስልት ለመመለስ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ መሞቱ ወዲያው ነበር የተነገረው።  ክርስቲያን ኤሪክሰን በዓለም ዙሪያ የሚታወቅ ድንቅ ተጨዋች ነው። አደጋው ምን አይነት ስሜት ነው የፈጠረው? ይስሐቅ እንደሚለው ኢትዮጵያ ውስጥ

ኮፓ አሜሪካ

የደቡብ አሜሪካ ሃገራት ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኖችን የሚያሳትፈው የኮፓ አሜሪካ  ውድድር ሁለተኛ ግጥሚያ ዛሬ ተከናውኖ ኮሎምቢያ ኤኳዶርን 1 ለ0 አሸንፏል። ዛሬ እኩለ ሌሊት ላይ ደግሞ የአርጀንቲና እና የቺሌ ቡድን ይጋጠማሉ። በነገው ዕለት ፓራጓይ ከቦሊቪያ፤ ሐሙስ እለት ኮሎምቢያ ከቬኔዙዌላ እንዲሁም ዐርብ ሌሊት 9 ሰአት ላይ ብራዚል ከፔሩ ጋር ይጫወታሉ። ትናንት በኮፓ አሜሪካ የመክፈቻ ግጥሚያ ብራዚል የቬኔዙዌላ ቡድንን 3 ለ0 ድል አድርጓል። ኤስታዲዮ ናሲዮናል ዴ ብራዚሊያ ስታዲየም ውስጥ በተደረገው ግጥሚያ ግቦቹን ማርኪኞስ፣ ኔይማር እና ጋብሪዬል ባርቦሳ አስቆጥረዋል።  64ኛው ደቂቃ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ግብ ያስቆጠረው ኔይማር 23ኛው ደቂቃ ላይም ማርኪኞስ የመጀመሪያዋን ኳስ ከመረብ እንዲያሳርፍ በስተግራ በኩል አመቻችቷል። የቬኔዙዌላ ቡድን 12 ተጨዋቾች እና አሰልጣኙ በጨዋታው ዋዜማ ባደረጉት ምርመራ የኮሮና ተሐዋሲ ተገኝቶባቸዋል።       

በፈረንሳይ ፍጻሜ፦ ኖቫክ ጄኮቪች ሽቴፋኖስ ጺጺፓስን ከአሸነፈ በኋላምስል Benoit Tessier/REUTERS

አንድ መቶ ዓመት ግድም በተቃረበው የኮፓ አሜሪካ እግር ኳስ ግጥሚያ ታሪክ ለ15 ጊዜያት ዋንጫውን በመውሰድ ኡራጓይን የሚስተካከል የለም። አርጀንቲና በ14 ዋንጫዎች ሲከተል፤ የብራዚል ቡድን ለ9 ጊዜያት የዋንጫ ባለቤት በመሆን ሦስተኛ ደረጃን ይዟል።   ፓራጓይ፣ ቺሌ እና ፔሩ እያንዳንዳቸው ለሁለት ጊዜያት የፍጻሜ ግጥሚያዎችን ሲያሸንፉ፤ ኮሎምቢያ እና ቦሊቪያ አንድ አንድ ጊዜ ዋንጫ መውሰድ ችለዋል።

የሜዳ ቴኒስ

ኖቫክ ጄኮቪች ፈረንሳይ በተካኼደው የሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ውድድ ላይ 2 ለባዶ ከመመራት ተነስቶ ሽቴፋኖስ ጺጺፓስን ድል አድርጓል። ኖቫክ 6-7 እና 2-6 ሲመራ ቆይቶ  በቀጣዮቹ ዙሮች በተከታታይ 6-3፤ 6-2 እና 6-4 ማሸነፍ ችሏል። የ22 ዓመቱ ግሪካዊ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የፍጻሜ ግጥሚያ ለ19 ጊዜያት የፍጻሜ አሸናፊ ከኾነው ተጋጣሚው ልምድ ቀስሟል። የ34 ዓመቱ ሠርቢያዊ የሜዳ ቴኒስ ዕውቅ ተጨዋች በትናንቱ ድል ራፋኤል ናዳል እና ሮጄር ፌዴሬር ላይ ተቃርቧል። ሁለቱ ተቀናቃኞቹ እስካሁን 20 የፍጻሜ ውድድሮችን አሸንፈዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW