1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 12 2015

በዓለም አቀፍ የሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን እንደተለመደው ድል ተቀዳጅተዋል ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከማላዊ አቻው ጋር ለመጋጠም ትናንት ወደ ሞዛምቢክ አቅንቷል ። ነገ ከሚኖረው የአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ምን ይጠበቃል፤ ፋይዳውስ ምንድን ነው?

UEFA Nations League Finale Spanien Kroatien
ምስል Martin Meissner/AP Photo

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በዓለም አቀፍ የሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያውያን እንደተለመደው ድል ተቀዳጅተዋል ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከማላዊ አቻው ጋር ለመጋጠም ትናንት ወደ ሞዛምቢክ አቅንቷል ። ነገ ከሚኖረው የአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ ምን ይጠበቃል፤ ፋይዳውስ ምንድን ነው? ከስፖርት ጋዜጠኛ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። በአውሮጳ የኔሽንስ ሊግ እግር ኳስ የዋንጫ ግጥሚያ ክሮሺያ ትናንት በስፔን ተሸንፋለች ። በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ዋንጫ ለመውሰድ በድጋሚ ጫፍ ደርሳም ሳይሳካላት ቀርቷል ። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከፖላንድ ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ሽንፈት ገጥሞታል ። ከኮሎምቢያ ጋር ለሚኖረው የአቋም መለኪያ ግጥሚያ ጥሪ የተደረገላቸው ተጨዋቾች አሉ ። የመጨረሻ ልምምዱንም ፍራንክፉርት ከተማ ውስጥ ዛሬ ተከናውኗል ።

አትሌቲክስ

ፈረንሳይ ላንጉዊ ውስጥ በተኪያሄደው የኮሪዳ ደ ላንጉዊ የ2023 የ10ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር በሴቶች ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ዓለም ንጉሤ አሸናፊ ሆናለች ። በወንዶች ተመሳሳይ ውድድር የኬንያው ሯጭ ኤማኑኤል ቦር አሸንፏል ።

የአትሌቲክስ ፉክክር በስታዲከም ውስጥ፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Bernd Thissen/picture-alliance/ dpa

አትሌት ዓለም ትናንት ለድል የበቃችው ርቀቱን 30:28 በመሮጥ ነው ። ኬንያውያቱ ሚሪያም ቼቤት እና ሊድያ ቼሩዬት ተከታትለው በመግባት የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል ። አንቺንአሉ ደሴ እና ትእግስት ጋጀው 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል ።  በወንዶቹ ፉክክር ኤማኑኤል ቦር አንደኛ የወጣው ርቀቱን በ27:46 በማጠናቀቅ ነው ።  ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ዳዊት ፈቃዱ እና ሐፍታም ገብረ ሥላሴ በኤማኑኤል ለጥቂት ተቀድመው በተመሳሳይ 27 ደቂቃ ከ48 ሰከንድ በመግባት የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል ።

በዚሁ ቦታ በተካሄደ የ5000 ሜትር የስታዲየም ውስጥ ውድድር ዐሳየች ዐይቸው 15:18.77 በመሮጥ 2ኛ ደረጃ አግኝታለች ። ሆላንድ ውስጥ በተካሄደ እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የ800 ሜትር ውድድር ደግሞ አትሌት ኤርሚያስ ግርማ 1:45.19 በመሮጥ አሸንፏል ።

እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ በሚኖረው የምድብ ጨዋታ ከማላዊ ጋር ለመጋጠም ወደ ሞዛምቢክ ትናንት አቅንቷል ። ኢትዮጵያ እና ማላዊ እስካሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎች፦ ሁለቱም 3 ነጥብ አላቸው ።  ግብፅ በአምስት ጨዋታዎች 12 ነጥብ ሰብስባ ከምድቡ የመጀመሪያ ሆና አልፋለች ። 24 ሃገራት በሚሳተፉበት የአፍሪቃ ዋንጫ ማለፋቸውን ካረጋገጡ   ሃገራት ስምንተኛዋ ሆናለች ።

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በነበረው ጨዋታ 26ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ግብጽን ሲመራ የቆየው የጊኒ ቡድን የማታ ማታ የ2 ለ1 ሽንፈት በማስተናገዱ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ወደ አፍሪቃ ዋንጫ በቀጥታ የማለፍ ዕድሉን አሳልፎ ሰጥቷል ። ነጥቡም በ9 ተወስኗል ። ጊኒ ከቀጣይ ጨዋታዎቹ በአንዱ አቻ መውጣት ብቻ ግብፅን ተከትሎ ለማለፍ ያስችለዋል ። ይህ ሁኔታ ሦስት ነጥብ ላላቸው ኢትዮጵያ እና ማላዊ ምን አንደምታ ይኖረዋል?  አዳዲስ ፊቶችን ወደፊት ማምጣታቸው የተነገረላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አዲሱ አሰልጣኝ ዳንኤል ገብረማርያም ኢትዮጵያ ከምታደርጋቸው ቀጣይ ጨዋታዎች ምን ማግኘት ይችላሉ? የስፖርት ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ጭላንጭል እድል ያላት ማላዊ ናት ይላል ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ ከማላዊ ጋር ይጫወታል

ኢትዮጵያ የመጨረሻ ጨዋታዋን ከግብጽ ጋር ትጫወታለች ። ግብጽ ማለፏን ብታረጋግጥም በመጀመሪያው ጨዋታ በኢትዮጵያ የደረሰባትን ሽንፈት ለመቀልበስ ዓልማ ስለምትገባ ጨዋታዋን ከባድ ሳያደርገው አይቀርም ።

ኔሽንስ ሊግ

በአውሮጳ የኔሽንስ ሊግ የእግር ኳስ የፍጻሜ ግጥሚያ ስፔን በትናንትናው ምሽት የክሮሺያ አቻዋን በፍጹም ቅጣት ምት መለያ አሸንፋ ዋንጫ ወስዳለች ።  በዓለም አቀፍ ውድድሮች በተደጋጋሚ ወደ መጨረሻዎቹ እየተቃረበች ዋንጫ ለናፈቃት ክሮሺያ የትናንቱ ሽንፈት አሳዛኝ ነበር ። በተለይ ደግሞ ለ37 ዓመቱ የክሮሺያ አማካይ ተጨዋች ሉካ ሞድሪች ። የክሮሺያ አሰልጣኝ ዝላትኮ ዳሊች የቡድናቸው አምበል ሉካ ሞድሪች ከዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ገለል እንዳይል ሲሉ ዛሬ ተናግረዋል ።

አሰልጣኙ፦ ክሮሺያ ትናንት ሆላንድ ሮተርዳም ከተማ ውስጥ በፍጹም ቅጣት ምት መለያ ምት በስፔን ብሔራዊ ቡድን 5 ለ4 ከተሸነፈች በኋላ በሰጡት አስተያየት ሉካ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጠዋል ። «እንፈልገዋለን ። ይህ ሥራውን አሁንም ድረስ ያላጠናቀቀው ትውልድ ነው» ሲሉ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ለጋዜጠኞች ዛግሬብ ውስጥ ተናግረዋል ።

የሪያል ማድሪዱ አማካይ ተጨዋች ክሮሺያን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2018 የዓለም ዋንጫ መርቷል ። ባለፈው የዓለም ዋንጫ ደግሞ ቃጠር ውስጥ ቡድኑ የሦስተኛ ደረጃ ይዞ እንዲኢጠናቅቅ አድርጓል ። በኔሽን ሊግስ ለፍጻሜ እንዲቃረብ አስችሏል ። ሁሌም ግን የናፈቃት ዋንጫ ከእጁ ልትገባ አልቻለችም ። ዛሬ ከክሮሺያ ለኅትመት የበቁ ታዋቂ ጋዜጦች አብዛኞቹ በፊት ለፊት ገጻቸው የክሮሺያን ሽንፈት ሲዘግቡ የሉካ ሞድሪችን ፎቶ አያይዘው ነበር ።

የሪያል ማድሪዱ አማካይ ተጨዋች ሉካ ሞድሪች ኳስ ከተቆጣጠረው የስፔኑ አይመሪች ላፖርቴ ጋርምስል Revierfoto/dpa/picture alliance

ሉካ ሞድሪች ስለ ቀጣይ ዓለም አቀፍ ተሳትፎው በዝርዝር ባይሆንም ትናንት፦ «ግልጽ ውሳኔ» ማስተላለፉን ገልጧል ። ከክሮሺያ ሽንፈት በኋላ ከስታዲየሙ ሲወጣ፦ «ዛሬ ምንም ነገር አልነግራችሁም» ብሏል ። ሉካ ሞድሪች ለክሮሺያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ላለፉት 17 ዓመታት ለ166 ጊዜያት መሰለፍ የቻለ አንጋፋ ተጨዋች ነው ።

ለዓለም አቀፍ የወዳጅነት ግጥሚያ ዋርሳው አቅንቶ የነበረው የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ባለፈው ዐርብ በፖላንድ 1 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል ። ለፖላንድ ብቸኛዋን ግብ በ31ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ጃኩቡ ኪቪሮር ነው ። የቀድሞ የጀርመን ቡንደስሊጋ ታዋቂ ተጨዋች ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪን ጨምሮ በርካታ የቡንደስሊጋ ተጨዋቾች በዐርቡ ጨዋታ ዋርሳው ውስጥ ተካፍለዋል ። የጀርመን ቡድን ብዙ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችልም የፖላንድ መረብን ግን ፈጽሞ መድፈር ተስኖት ጨዋታው ተጠናቋል ።

ከኮሎምቢያ ጋር ነገ ለሚኖረው የወዳጅነት ጨዋታ አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ ፍራንክፉርት ውስጥ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዳቸውን አድረገዋል ። ከኮሎምቢያ ጋር ኤሰን ግዛት ውስጥ ለሚኖረው ግጥሚያም ቡድኑ ወደ ጌልዘንኪርሸን ዛሬ ከሰአት አቅንቷል ። አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ሆኖ ዋንጫ ያነሳው አማካይ ኢልካይ ጉንዶዋንን ወደ ቡድኑ ጠርተውታል ።

የጀርመን ቡድን ከሳምንት በፊት ብሬመን ውስጥ ከዩክሬን ቡድን ጋር ሦስት እኩል ሲለያይ የ32 ዓመቱ አማካይ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበረው የዋንጫ ፌሽታ መሰለፍ አልቻለም ። ባለፈው ዐርብ ዋርሳው ውስጥ ቡድኑ ሽንፈት ሲገጥመው ረፍት ላይ ስለነበር ኢልካይ ጉንዶዋን አልተሰለፍም ። በነገው የወዳጅነት ጨዋታ ብዙ ይጠበቅበታል ። አሰልጣኙ ግብ ጠባቂው ማርክ አንድሬ ተር ሽቴገን እና አጥቂው ፍሎሪያን ቪርትስንም ወደ ቡድኑ ጠርተዋል ። እናስ እነዚህ ተጨዋቾች የጀርመን ቡድንን ወደ ናፈቀው የድል መስመር ይመስልሱት ይሆን? የነገ ማታውን ጨዋታ መከታተል ነው ።

የፈረንሳይ ብሔራዊ የእግር ኳስ አጥቂ ኬሊያን እምባፔ ከፊት ለፊቱ ኔይማር አለ ጀርባው የሚታየው ባለነጭ ጸጉርምስል Elyxandro Cegarra/NurPhoto/picture alliance

ኪሊያን ምባፔ

አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲን ያጣው ፓሪ ሳን ጃርሞ ቡድን ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ። ዋና አጥቂው ኬሊያን እምባፔም ከቡድኑ ሊሰናበት እንደሆነ መግለጡ በፓሪ ሳንጃርሞ ውስጥ ተጨማሪ ጫና አሳድሯል ። የፈረንሳይ ብሔራዊ የእግር ኳስ አጥቂ ኬሊያን እምባፔ በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን ከፓሪ ሳንጃርሞ ጋር ውሉን እንደማያድስ ዐሳውቋል ።

ኬሊያን እምባፔ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር በፈረንሳይ እግር ኳስ ዛሬም ድረስ ዝናው ከናኘው ሚሼል ፕላቲኒ ጋር ሊስተካከል ሁለት ግቦች ብቻ ይቀሩታል። ሚሼል ፕላቲኒ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለፈረንሳይ ቡድን 41 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈ የግብ ቀበኛ ነበር ። ኬሊያን እምባፔ ከፓሪ ሳንጃርሞ ወደየት እንደሚያቀና በውል ዐልታወቀም ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW