1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 13 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 13 2014

የፓሪስ ዳያመንድ ሊግ ባለድል አትሌት ሰለሞን ባረጋን አነጋግረናል። ፋሲል ከነማና ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ የሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን እግር ኳስ ውድድሮች ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ ታውቋል። ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ለመኼድ ባቆበቆበበት በአሁኑ ወቅት ሴኔጋላዊው የሊቨርፑል አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ወደ ጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን ሊዛወር ጫፍ ደርሷል።

ምስል Bildbyran/imago

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በሳምንቱ መገባደጃ በፓሪስ ዳያመንድ ሊግ ደማቅ ድል ካስመዘገቡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶቻችን መካከል አትሌት ሰለሞን ባረጋን አነጋግረነዋል። ፋሲል ከነማና ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ የሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን እግር ኳስ ውድድሮች ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ ታውቋል። ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ወደ ሌላ ቡድን ለመኼድ ባቆበቆበበት በአሁኑ ወቅት ሴኔጋላዊው የሊቨርፑል አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ወደ ጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን ሊዛወር ጫፍ ደርሷል። ኹኔታው ለባየርን ሙይንሽን በጨዋታ ሜዳ ታክቲክ እና የአመራር ፖለቲካ ላይ አዲስ ዘመን ፈንጥቋል።  በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን አሁንም አልቀናውም። በካናዳው ፉክክር ድል ፊቷን ወደ ሬድ ቡል ቡድን አዙራለች።

ምስል Haimanot Tiruneh/DW

ፓሪስ እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ከ2014 ዓ.ም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የወንዶችን የ5000 ሜትር ርቀት ባስተናገደችበት የቅዳሜ ምሽት የዳያመንድ ሊግ የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነታቸውን ዐሳይተዋል። በኦሎምፒክ የ5000 ሜትር ርቀት ባለድሉ ሰለሞን ባረጋ የፓሪስ ፉክክር ላይም ዳግም ብቃቱን አስመስክሯል።  በውድድሩ በአምስት ሺህ ሜትር ርቀት 12:56.19 በመሮጥ በድንቅ ኹኔታ በአንደኛነት ያሸነፈው አትሌት ሰለሞን ባረጋን የፓሪስ ወኪላችን ሐይማኖት ጥሩነህ ከውድድሩ በኋላ አነጋግራ ቀጣዩን አጠር ያለ ዘገባ ልካልናለች።

በፓሪስ ዳያመንድ ሊግ ፉክክር የቡሩንዲው ሯጭ ቲዬሪ ንዲኩምዌናዮ 13:05.24 ሰከንድ በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል።  አትሌት ሙክታር እድሪስ በቡሩንዲው ሯጭ የተቀደመው በ1 ደቂቃ ከ30 ሰከንድ ነው።

ምስል Haimanot Tiruneh/DW

በሴቶች የ3000 ሜትር የመሰናክል የሩጫ ውድድርም ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ለድል በቅተዋል። የ22 ዓመቷ ትውልደ ኬኒያዊት ባህሬናዊት አትሌት ዊንፍሬድ ሙቲሌ 8:56.55 በመሮጥ አንደኛ ወጥታለች። የ17 ዓመቷ ታዳጊ ኢትዮጵያዊት  አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ 9 ደቂቃ ከ9. 19 ሰከንድ በበመሮጥ ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች።  ከሲምቦ በ2 ሰከንድ ብቻ ለጥቂት የተቀደመችው መቅደስ አበበ ደግሞ ሦስተኛ ሆና አጠናቃለች። 

እግር ኳስ

ፋሲል ከነማና ቅዱስ ጊዮርጊስ የእግር ኳስ ቡድኖች በአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (CAF)ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቡድኖች መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ፋሲል ከነማ ዛሬ ባህር ዳር ስታዲየም ውስጥ በተከናወነው የቤትኪንግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታ አዳማ ከነማን 2 ለ0 በማሸነፍ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የ3 ነጥብ ልዩነት ማስጠበቅ ችሏል። ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ወልቂጤ ከተማን 2ለ0 አሸንፈው ነጥባቸውን 58 አድርሰዋል። ሊጉ ሲጠናቀቅ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን በካፍ ውድድር ኢትዮጵያን በመወከል የሻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናል። ሁለተኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን በበኩሉ ካፍ በሚያዘጋጀው የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተወዳዳሪ ይሆናል። የካፍ የሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የዘንድሮ ውድድሮች ዐርብ ነሐሴ 6 ቀን፣ 2014 ዓ.ም እንደሚጀምሩ የአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ይፋ አድርጓል። በሁለቱም የውድድር ዘርፎች የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች መስከረም ወር ላይ ጀምሮ የካታር የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ 3 ቀን በፊት በኅዳር 9 ቀን እንደሚጠናቀቅ ተገልጧል። የኳታሩ የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ሊጀመር 153 ቀናት ይቀሩታል።

የዝውውር ዜና

ምስል Anke Waelischmiller/SVEN SIMON/picture alliance

የሊቨርፑል ወሳኝ አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ወደ ጀርመኑ ኃያል ቡድን ባየርን ሙይንሽን የመዘዋወር ዜና በቡንደስሊጋው ታሪክ አዲስ ምእራፍ ከፍቷል። ለወትሮው የጀርመን ቡንደስሊጋ ቡድን ምርጥ ተጨዋቾች ነበሩ ወደ እንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሲያቀኑ የሚስተዋለው። በቅርቡ እንኳን የቦሩስያ ዶርትሙንድ አጥቂ ኖርዌያዊው ኧርሊንግ ኦላንድ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ማቅናቱን፤ መጥቀስ ይቻላል። የባየርን ሙይንሽን የረዥም ዘመን አጥቂ የ33 ዓመቱ ፖላንዳዊ ሮቤርትር ሌቫንዶቭስኪም ወደ ባርሴሎና ሊዛወር እንደሆነ መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል። የ30 ዓመቱ ሴኔጋላዊ አጥቂ ሳዲዮ ማኔ ግን ከእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ወደ ጀርመን ቡንደስሊጋ ሊዛወር ሒደቱ ጫፍ ደርሷል። እንደ ጀርመን ጋዜጦች መረጃ ከኾነ ባየርን ሙይንሽን ሳዲዮ ማኔን የ3 ዓመት ውል ለማስፈረም ለሊቨርፑል 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ከፍሎታል።  ሌሎች ጥቅማ ጥቆሞች ሲደማመሩ ደግሞ ገንዘቡ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሊሆን እንደሚችልም ተገልጧል።

ሳዲዮ ማኔ የሕክምና ጉዳዮችን ለመጨራረስ ነገ ወደ ጀርመን ሙይንሽን ከተማ እንደሚያቀና ታውቋል። ባየርን ሙይንሽን በአውሮጳ ንፍቀ ክበብ የበጋ ወራት ሳዲዮ ማኔን ሲያስፈርም ሦስተኛ ተጨዋቹ ነው። ከሱ ቀደም ብሎ ከአያክስ አምስተርዳም ሪያን ግራቬንቤርች እና ኖሳይር ማዝሮይ ፈርመዋል። በአንጻሩ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ሻንጣውን ከሸካከፈ ሰነባብቷል። በእርግጥ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ከባየርን ሙይንሽን ጋር የገባው ውል ሊገባደድ የ1 ዓመት ጊዜ ስለሚቀረው ባየርን ሙይንሽን ተጨዋቹን ለመሸጥ አይገደድም። ኾኖም ባርሴሎና ፖላንዳዊውን አጥቂ በ32 ሚሊዮን ዩሮ ለመግዛት ጠይቆ ባየርን ሙይንሽን ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉን ስፖርት የተሰኘው የስፔን ጋዜጣ ዘግቧል።

ለሊቨርፑል 269 ጊዜ ተሰልፎ 120 ግቦችን ያስቆጠረው ሳዲዮ ማኔ ወደ ባየርን ሙይንሽን ሲያቀና የ22 ዓመቱ ዑራጋያዊ ብርቱ አጥቂ ዳርዊን ኑኔዝ ለሊቨርፑል መፈረሙ ታውቋል። ዳርዊን ከቤኔፌካ ወደ ሊቨርፑል ለስድስት ዓመት ውል የፈረመው ለመነሻ 78 ሚሊዮን ዶላር ተከፋይ በመሆን ነው። ዳርዊን ኑኔዝ ከማስታወቂያ የሚያገኘው ተጨማምሮ በሊቨርፑል ከፍተኛ ክፍያ ታሪክ 104 ሚሊዮን ዶላር ያገኛል ተብሏል። ዑራጋያዊ አጥቂ ለፖርቹጋሉ ቤኔፊካ 41 ጊዜ ተሰልፎ 34 ኳሶችን ከመረብ ማሳረፍ የቻለ የግብ ቀበኛ ነው።  

የመኪና ሽቅድምድም

ምስል HOCH ZWEI/picture alliance

በካናዳ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን ትናንት ድል ተቀዳጅቷል። ማክስ ፈርሽታፐን በውድድር ዘመኑ የትናንቱ 150 ተሳትፎው ሲሆን፤ 24ኛ ድሉ ኾኖም ተመዝግቦለታል። ለጥቂት በ0.9 ሰከንድ ልዩነት ያሸነፈው የ24 ዓመቱ ሆላንዳዊ አሽከርካሪ በፌራሪ አሽከርካሪ ካርሎስ ሳይንስ ብርቱ ፉክክር ገጥሞት ነበር። የማርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን የሦስተኛ ደረጃን አግኝቶ ወደ አሸናፊነት መድረኩ ዳግም ብቅ ማለቱ መነቃቃትን እንደፈጠረለት ተናግሯል።  

እስካሁን በተደረጉ ውድድሮች በአጠቃላይ ሆላንዳዊው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ማክስ ፈርሽታፐን በ175 ነጥቦች ይመራል። ሌላኛው የቡድን አጋሩ ሜክሲኮያዊው ሠርጂዮ ፔሬዝ በ129 ነጥብ ይከተላል። የሞናኮው የፌራሪ አሽከርካሪ ሻርል ሌክሌር የሬድ ቡል አሽከርካሪዎችን ተከትሎ በ126 ነጥቡ የሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ሌዊስ ሐሚልተን ከቡድን አጋሩ ጆርጅ ሩሴል እና የፌራሪው አሽከርካሪ ካርሎስ ሳይንስ ቀጥሎ በ6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እስካሁን የሰበሰበው ነጥብም ከመሪው ማክስ ፈርሽታፐን በ98 ነጥብ ተበልጦ 77 ነው። በአንድ ዙር ውድድር ያሸነፈ አሽከርካሪ የሚያገኘው 25 ነጥብ ነው። እንዲያም ኾኖ የ7 ጊዜያት የዓለማችን የፎርሙላ አንድ ዋንጫ ባለቤት ሌዊስ ሐሚልተን ዳግም ወደ ድል ለመመለስ የትናንት 3ኛ ደረጃው አዲስ ጅማሬ ኾኖለታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW