1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 22 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 22 2012

በጀርመን ቡንደስሊጋ የዘንድሮ ውድድር ወራጅ ቃጣና ግርጌ የሚገኘው ቬርደር ብሬመን እና ከኹለተኛ ዲቪዚዮን ያደገው ሐደልሃይደን የደርሶ መልስ ግጥሚያ ብቻ ይቀራል። ሊቨርፑል ዋንጫውን አስቀድሞ በወሰደበት የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ራሱ ሊቨርፑል እና ዋነኛ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲ የሚያደርጉት ግጥሚያ በበርካቶች ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል።

Fußball Bundesliga Übergabe Meisterschale FC Bayern München
ምስል Reuters/K. Pfaffenbach

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ባየር ሙይንሽን አስቀድሞ ዋንጫውን በወሰደበት የቡንደስ ሊጋ የዘንድሮ ፉክክር የመጨረሻ ኹለት የደርሶ መልስ ግጥሚያዎች ብቻ ይቀራሉ። ወደ ኹለተኛ ዲቪዚዮን ከመውረድ በድንገት ተስፋው ለምልሞ ወራጅ ቃጣናው ግርጌ ላይ ለቆየው ቬርደር ብሬመን በቀጣይ ቀናት የሚከናወኑ ኹለት ግጥሚያዎች የሞት ሽረት ፍልሚያ ተደርገው ነው የሚወሰዱት። በተመሳሳይ ሊቨርፑል ዋንጫውን አስቀድሞ በወሰደበት የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ራሱ ሊቨርፑል እና ዋነኛ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲ የሚያደርጉት ግጥሚያ በበርካቶች ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። ምንም እንኳን ዋንጫው በሊቨርፑል የተወሰደ ቢኾንም ኹለቱ ተፎካካሪ ቡድኖች  የሐሙስ ጨዋታ በማሸነፍ ታሪክ ለመስራት መፋለማቸው አይቀርም። በስፔን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ የመሪነቱን ሥፍራ ተረክቧል። ከተጨማሪ ዘገባዎች ጋር አብራችሁን ቆዩ!

ቡንደስሊጋ

34ኛው ዙር ጨዋታ ተጠናቆ ቡንደስሊጋው ዘንድሮ ሲያበቃ ባየር ሙይንሽን ለሻምፒዮን ሊግ ካለፉት ከሌሎቹ ቡድኖች በአጠቃላይ በነጥብ ርቆ ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድን በ13 ነጥብ በልጦ ነው ያጠናቀቀው። ባየር ሙይንሽን 82 ነጥብ አለው። በአንፃሩ ላይፕሲሽ በዶርትሙንድ በ3 ነጥብ ብቻ ተበልጦ 66 ነጥብ ይዞ ነው የጨረሰው። ቦሩሽያ ሞይንሽንግላድባኅ በዘንድሮው የጨዋታ ዘመን 65 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል። ለአውሮጳ ሊግ ማጣሪያ ካለፉት ሦስት ቡድኖች ባየር ሌቨርኩሰንም ብዙ አልተበለጠም፤ 63 ነጥብ ይዞ ነው የጨረሰው። ሆፈንሃይም እና ቮልፍስቡርግ በ52 እና 49 ነጥባቸው የአውሮጳ ሊግ ማጣሪያን ተቀላቅለዋል።

ከኹለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ኾኖ በመጨረስ በቀጣይ ዓመት ወደ ቡንደስሊጋ ለመግባት ጫፍ የደረሰው ሐይደንሀይም ምስል Imago Images/Sportfoto Rudel

ፓዴርቦን እና ፎርቱና ዱይስልዶርፍ ከቡንደስሊጋው ተሰናባቾች ናቸው። ቬርደር ብሬመን ከወራጅነት ቃጣናው በአለቀ ሰአት ነው ነፍስ ዘርቶ ለጊዜውም ቢኾን ከመውረድ የተረፈው። ዱይስልዶርፍ ቅዳሜ ዕለት በዑኒዬን ቤርሊን 3 ለ0 መሸነፉ እና ቬርደር ብሬመን ኮሎኝን 6 ለ1 መረምረሙም ነበር በቀጥታ ወደ ኹለተኛ ዲቪዚዮን ከመውረድ ያዳነው።

16ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ቬርደር ብሬመን ከኹለተኛ ዲቪዚዮን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ከመጣው ሐይደንሃይም (55) ጋር ሐሙስ እና የሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ማታ በደርሶ መልስ ይጋጠማል። እናም ከኹለቱ ግጥሚያዎች በኋላ ወይ እዛው ቡንደስሊጋው ውስጥ ይቀራል አለያም ወደ ኹለተኛው የቡንደስሊጋ ይሰናበታል። ዘንድሮ ሐምቡርግ ወደ ቡንደስሊጋው ያድጋል ተብሎ ሲጠበቅ ሐይደንሃይም ነው ሦስተኛ መኾን የቻለው። ሐይደንሃይም በቢሌፌልድ 3 ለ0 ቢሸነፍም ሐምቡርግ በዛንድሐውሰን ባልተጠበቀ ኹኔታ 5 ለ1 መንኮታኮቱ ነበር ወደ ቡንደስሊጋ የመመለስ ዕድሉን በራሱ እንዲያመክን ያደረገው።

ሐምቡርግ እና ሐይደንሀይም በ1 ነጥብ ልዩነት ብቻ ነው የተለያዩት። ሐይደንሃይም እና ብሬመን ለጀርመን እግር ኳስ ዋንጫ (DFB) ጥቅምት 20 ተጋጥመው በወቅቱ ብሬመን ሳይቸገር 4 ለ 1 ነበር ያሸነፈው።  በቀጣይ የደርሶ መልስ ግጥሚያዎች ዳግም ያሸንፍ አለያም ቡንደስሊጋ ለመግባት ጫፍ የደረሰው ሐይደንሀይም በርትቶ ይምጣ ከሰሞኑ የሚታይ ይኾናል። ከኹለተኛው ዲቪዚዮን 68 ነጥብ ይዞ ያጠናቀቀው ቢሌፌልድ  እና ሽቱትጋርት ግን በ58 ነጥብ ወደ ቡንደስሊጋው አልፈዋል።

ባየር ሙይንሽን

የቡንደስሊጋ ዋንጫን በተከታታትይ ለ8ኛ ጊዜ ዘንድሮም የወሰደው ባየር ሙይንሽን፥ ከመሀል አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክምስል picture-alliance/dpa/Reuters/K. Pfaffenbach

57ኛው የቡንደስሊጋ ዋንጫን ዘንድሮም ባየር ሙይንሽን ሲወስድ ለ8ኛ ጊዜ በተከታታይ ነው። በዚህም ቡድኑ የአይበገሬነት መንፈሱ ዛሬም እንዳልተለየው ማስረገጥ ችሏል። የባየር ሙይንሽን ተደጋጋሚ ድል ቡድኑ ከተጨዋቾች አንስቶ እስከላይ አመራሩ ድረስ ማንም አያሸንፈንም የሚል መንፈስ ለረዥም ጊዜ በማዳበሩ ነው። የቡድኑ ተደጋጋሚ ድል የሚያስገኝለት ዳጎስ ያለ ገቢ እና የቡድኑ በአዲሱ ዋና አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክ በጥሩ ኹኔታ መናበብ መቻሉ በሚቀጥለው የጨዋታ ዘምንም ጠንካራ ተፎካካሪ ኾኖ ብቅ እንዲል ያስችለዋል።  

የባየር ሙይንሽኑ የ68 ዓመቱ የክብር ፕሬዚደንት ዑሊ ሆኔስ፦ «ቡድናችን ቅርጹን ጠብቆ የሚዘልቅ ከኾነ ከምር ኹሉንም ዋንጫዎች አሸንፎ የመውሰድ ዕድሉ አለን» ሲሉ ተናግረዋል።  ይኽንንም ትናንት ብሊክፑንክት ስፖርት (Blickpunkt Sport) ከተሰኘው የባይሪሽ ቴሌቪዥን ስርጭት ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ ነው የተናገሩት።

ባየር ሙይንሽን ለጀርመን እግር ኳስ ዋንጫ  ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር የፊታችን ቅዳሜ ቤርሊን ከተማ ውስጥ የዚህ ዓመት ኹለተኛ ዋንጫውን ያነሳል ተብሎ ይጠበቃል። እንዲሁም ነሐሴ 1 ቀን፤ 2012 ዓም  ፖርቹጋል ሊዛቦን ከተማ ውስጥ በሚደረጉት የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያዎች ላይም ዕድል ሊኖረው ይችላል። ለሻምፒዮንስ ሊግ በግማሽ ፍጻሜው የሚጋጠመው ከቸልሲ ጋር ነው።

በነገራችን ላይ ሪያል ማድሪድ ከማንቸስተር ሲቲ፤ ጁቬንቱስ ከኦሎምፒያኮስ ሊዮን፤ ባርሴሎና ከናፖሊ ጋር ነው በተመሳሳይ ቀን የሚጋጠሙት።  ባየር ሙይንሽን ሦስቱን ዋንጫዎች ማለትም፦ ቡንደስሊጋ፤ ጀርመን እግር ኳስ ዋንጫ (DFB) እና ሻምፒዮንስ ሊግ ያሸነፈው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 በዩፕ ሃይንከስ የአሰልጣኝነት ዘመን ነበር። ምናልባትም ዘንድሮ በሐንሲ ፍሊክ ዘመን ሦስቱን ባያሳካ እንኳን ኹለት ዋንጫዎችን ማግኘቱ የማይቀር እንደኾነ በርካቶች ይናገራሉ። በእርግጥ የኳስ ነገር የሚኾነው ስለማይታወቅ የፊታችን ቅዳሜ ቤርሊን ውስጥ የሚካኼደውን የጀርመን እግር ኳስ የፍጻሜ ግጥሚያው መከታተል ነው።

ሊቨርፑል

ከ30 ዓመታት በኋላ ዘንድሮ የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ የወሰደው ሊቨርፑል ቡድን ደጋፊዎች በአንፊልድ ምስል Reuters/P. Noble

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ አውሮጳ ሊግ ብሎም ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ ለመግባት መንገድ የሚጠርግለትን ግጥሚያ ነገ ማታ ከብራይተን ጋር ያከናውናል። 49 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ አምስተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ዎልቭስ የሚበለጠው በሦስት ነጥብ ብቻ ነው። በነገው ተስተካካይ ጨዋታው ማንቸስተር ዩናይትድ ማሸነፍ የሚችል ከኾነ ከዎልቭስ ጋር በነጥብ ተስተካክሎ በግብ ክፍያ ስለሚልቅ የአውሮጳ ሊግ ተሳታፊነት ዕድሉን ከዎልቭስ ይረከባል ማለት ነው። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ምድብ ውስጥ ከገባው ቸልሲም የሚበለጠው በ2 ነጥብ ይኾናል። ያ ግን ቸልሲ ረቡዕ ዕለት ከዌስትሐም ዩናይትድ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይወሰናል።

ወራጅ ቃጣናው ጠርዝ ላይ ለሚገኘው ዌስትሀምም ኾነ የሻምፒዮንስ ሊግ ቀጣይ ተሳታፊ ከሚኾኑ አራት ቡድኖች አራተኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ቸልሲ የረቡዕ ዕለቱ ግጥሚያ ለኹለቱም የሞት ሽረት ነው። 18ኛ እና 19ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት በርመስ እና አስቶን ቪላ ከዌስትሐም ዩናይትድ ጋር ተመሳሳይ 27 ነጥብ አላቸው። በርመስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ይቀረዋል።

የፕሬሚየር ሊጉ ግርጌ 20ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኖርዊች 21 ነጥብ ብቻ አለው። ቀጣይ ጨዋታው ረቡዕ ዕለት ከአርሰናል ጋር ነው። 9ኛ ደረጃ ላይ 43 ነጥብ ይዞ የሚገኘው አርሰናል የረቡዕ ግጥሚያን የማሸነፍ ዕድሉ የሰፋ ነው። አርሰናል ወደ አውሮጳ ሊግ ወይንም ሻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ ዕድሉ አኹንም አለው። ሐሙስ ማታ ቶትንሀም ከሼፊልድ ዩናይትድ ጋር ይጋጠማል። ኹለቱም ቡድኖች በአንድ ነጥብ ልዩነት 7ኛ እና 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመኾናቸው ግጥሚያቸው የሚጠበቅ ነው። እነዚህ ኹለት ቡድኖችም  ለአውሮጳ ሊግም ኾነ ሻምፒዮንስ ሊግ የማለፍ ዕድላቸው ገና አላከተመም።

ከኹለቱ ቡድኖች ፉክክር ኹለት ሰአት ቆይታ በኋላ ሐሙስ ማታ የዘንድሮ የፕሬሚየር ሊግ ባለድል ሊቨርፑል እና ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲ ይጋጠማሉ። የሐሙሱ ግጥሚያ ለሊቨርፑል የክብር ጉዳይ ቢኾንም ለማንቸስተር ሲቲ ግን የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱን ለማስረገጥ ብሎም ዋንጫውን የነጠቀውን ሊቨርፑል ለመበቀል የሚያደርገው ውድድር ነው።

ምስል Getty Images/A. Livesey

ኤፍ ኤ ካፕ

በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ማንቸስተር ዩናይትድ ቸልሲን ይገጥማል። አርሰናልን ካለፈው የዋንጫ ባለቤት ማንቸስተር ሲቲ ጋር ይፋለማል። አራቱም ቡድኖች የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን በተደጋጋሚ በመውሰድ ታሪክ ያላቸው ናቸው። ከአራቱም ግን አርሰናል ቀዳሚ ሲኾን፤ 13 ጊዜ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ማንሳት ችሏል። ኖርዊችን አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ማለፍ የቻለው ማንቸስተር ዩናይትድ 12 ጊዜ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን መጨበጥ ችሏል። በሩብ ፍጻሜው ላይስተርን ያሰናበተው ቸልሲ በአንጻሩ ለስምንት ጊዜያት ኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ማሸነፍ ችሏል።  ጨዋታዎቹ ከሦስት ሳምንት በኋላ ባሉት ቅዳሜ እና እሁድ ነው የሚከናወኑት። ፍጻሜው ሐምሌ 25 ቀን በተመሳሳይ የዌምብሌይ ስታዲየም ውስጥ ሊካኼድ ቀጠሮ ተይዞለታል።

ላሊጋ

ኤስፓኞላን በጨዋታ በልጦ ትናንት 1 ለ 0 ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ በላሊጋው የመሪነቱን ስፍራ ተቆናጧል። አትሌቲኮ ማድሪድ እና ሴቪላ 58 ነጥብ እባ 54 ይዘው የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ቦታቸውን አስጠብቀዋል። እሁድ ዕለት በተከናወኑ የስፔን ላሊጋ ሌሎች ግጥሚያዎች፤ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቪላሪያል ቫሌንሺያን 2 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 51 ማድረስ ችሏል። ለአውሮጳ ሊግ ማለፉን እንዳረጋገጠ መዝለቅ እንዳይችል ግን ጌታፌ በ2 ነጥብ ልዩነት ይከተለዋል። ጌታፌም ቢኾን በአውሮጳ ሊግ ማጣሪያ ለጊዜው የያዘውን ቦታ 47 ነጥብ ያለው ሪያል ሶሴዳድ ሊረከበው ይችል ይኾናል። በሌሎች የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች ሌቫንቴ ሪያል ቤቲስን 4 ለ2፤ እንዲሁም አይበር ግራናዳን 1 ለ0 ድል አድርገዋል።  ባርሴሎና የወራጅ ቃጣናው ጠርዝ ላይ ከሚገኘው ሴልታቪጎ ጋር ቅዳሜ ዕለት ባደረገው ግጥሚያ 2 እኩል በመውጣት ነጥብ በመጣሉ የመሪነቱን ስፍራ በ2 ነጥብ ተበልጦ ለሪያል ማድሪድ አስረክቧል። ሪያል ማድሪድ 71 ነጥብ አለው። ማዮካ፤ ሌጋኔስ እና ኤስፓኞላ ከ17ኛ እስከ 20ኛ በመደርደር ወራጅ ቃጣናው ውስጥ ይገኛሉ።

ፎርሙላ አንድ

ምስል picture-alliance/dpa/LAT Photographic

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም የዘንድሮ ቀጣይ ፉክክሮች መርሴዲስ በጥቊር ተሽከርካሪ እንደሚወከል ይፋ አድርጓል። ምንም እንኳን ሜርሴዲስ ላለፉት 90 ዓመታት ግድም በብርማ ቀለም ተወክሎ የቆየ ቢኾንም፤

 አኹን ቀለሙን የሚቀይረው ዘረኝነትን ለመቃወም ነው ተብሏል። በዛውም ለ«ጥቊር ሕይወት ግድ ይለኛል» ንቅናቄ ማለትም (Black Lives Matter)  ድጋፉን ለማሳየትም እንደኾነ ዐሳውቋል። የፎርሙላ አንድ ተደጋጋሚ ባለድሉ እና የማርሴዲስ ጥቁሩ አሸክርካሪ ብሪታኒያዊው ሌዊስ ሀሚልተን ቡድኑ ይኽን ማድረጉን «እንደ ቢዝነስ ለመለወጥ እና ለመሻሻል ፈቃደኛ መኾናችንን የሚያሳይ መግለጫ» ሲል አወድሶታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW