1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 5 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 5 2015

የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ እና የዋንጫ ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት ይካሄዳሉ ።በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለፍጻሜ እየተቃረበች ድል የራቃት ክሮሺያ ከግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች መካከል ትገኛለች ። ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሜቻ ግርማ በ3000 ሜትር መሰናከል ሩጫ ክብረወሰን ሰብሮ አሸንፏል ።

UEFA Champions League | Finale | Manchester City vs Inter Mailand
ምስል JON OLAV NESVOLD/Bildbyran/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ እና የዋንጫ ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት ይካሄዳሉ ። በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለፍጻሜ እየተቃረበች ድል የራቃት ክሮሺያ ከግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች መካከል ትገናለች ። ኢትዮጵያዊው አትሌት ለሜቻ ግርማ በ3000 ሜትር መሰናከል ሩጫ ክብረወሰን ሰብሮ አሸንፏል ። በሜዳ ቴኒስ ግጥሚያ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች የዓለማችን ምርጥ መሆኑን አስመስክሯል ። ትናንት በፓሪስ ዳያመንድ ሊግ ለ23ኛ ጊዜ የዓመቱ ታላቅ ውድድርን በማሸነፍ ክብረወሰን ሰብሯል ። ሊዮኔል ሜሲ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አቅንቶ ለሚያሜ እንደሚጫወት ዐሳውቋል ። ቅዳሜ ዕለት ቻይና ሲደርስ እጅግ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል ።

አትሌቲክስ

የ3,000 ሜትር የመሰናከል ሩጫ ክብረወሰን እስከ ባለፈው ሳምንት ዐርብ ድረስ ላለፉት 19 ዓመታት ሳይደፈር ቆይቷል ። ያሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ግን በኢትዮጵያዊው ድንቅ አትሌት ክብረወሰኑ ተደፍሯል ። አትሌት ለሜቻ ግርማ ፈረንሳይ ውስጥ በፓሪስ ዳያመንድ ሊግ የ3,000 ሜትር የመሰናከል ሩጫ ፉክክር ክብረወሰን ሰብሮ ያሸነፈበት የ7 ደቂቃ ከ52.11 ሰከንድ ጊዜ የዓመቱ ሦስተኛ ድንቅ ተብሎ ተመዝግቧል ። ክብረወሰኑ በቃጠሩ አትሌት ሣይፍ ሣዒድ ሻሂን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2004 ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ የተያዘው 7:53.63 ጊዜ ነበር ። አሁን ክብረወሰኑ በ1.52 ሰከንድ ተሻሽሏል ። የአትሌት ለሜቻ ድል ኢትዮጵያ በመሰል የውድድር ዘርፍ ጠንክሮ ከተሠራ አመርቂ ውስጥ ሊገኝ እንደሚችልም አመላካች ነው ። 

በዚሁ የዳያመንድ ሊግ የሴቶች የ5000 ሜትር ውድድር ኬንያዊቷ ፌይዝ ኪፔይጎንም አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግባ ለድል በቅታለች ። ፌይዝ ኪፔይጎን በኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ ተይዞ የቆየውን  የርቀቱን ክብረ ወሰን በአንድ ሰከንድ አሻሽላ ነው ያሸነፈችው ። በውድድሩ ታሸንፋለች ተብሎ ቅድመ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው የርቀቱ የክብረ ወሰን ባለቤት ለተሰንበት ግደይ ሁለተኛ ወጥታለች። ፌይዝ ኪፔይጎን ክብረ ወሰን ስታሻሻል በሳምንት ጊዜ ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ። የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮናዋ የ29 ዓመቷ ፌይዝ ባለፈው ሳምንትም በ1500 ሜትር የሩጫ ውድድር በኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ጸጋይ ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ክብረ ወሰን ማሻሻሏ አይዘነጋም ።

የፓሪስ ዲያመንድ ውድድር የባለፈው ውድድርምስል Haimanot Tiruneh/DW

ከዚሁ ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ፦ ኤርትራ ውስጥ የአስመራ ማራቶን የሩጫ ፉክክር ትናንት ተከናውኗል ። ርቀቱን የኤርትራው አትሌት ናሆም ኤርሚያስ 2 ሰአት ከ14 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ በመሮጥ ሲያሸንፍ የዩጋንዳው ሯጭ ቤን ቼሊሞ 2ኛ ደረጃ አግኝቷል ። የሦስተኛ ደረጃውንም ኤርትራዊው ሯጭ ክብሮም ገብረእግዚአብሔር አግኝቷል ።

እግር ኳስ

በአፍሪቃ ሽምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ግጥሚያ ትናንት የግብጹ አል አህሊ በአጠቃላይ ውጤት አሸንፎ ዋንጫ ወስዷል ። በትናንቱ ግጥሚያ አል አህሊ እና የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ ጨዋታቸው የተጠናቀቀው አንድ እኩል በመውጣት ነበር ። በአጠቃላይ ውጤት ግን አል አህሊ 3 ለ2 አሸንፎ ዋንጫ ወስዷል። 

ዘንድሮ ከአውሮጳ የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል ማንቸስተር ሲቲ ወሳኝ የሚባሉ ሦስት ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ብቃቱን ዐሳይቷል ። ለዚህ ብቃቱ ታዲያ ዋነኛው ሞተር አሰልጣኙ ናቸው ። ማንቸስተር ሲቲን ለመጀመሪያ ጊዜ ለአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ማእረግ ያበቁት እኚሁ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ቡድናቸው የማሸነፍ መንፈሱን ይበልጥ ካጠነከረ የሚያቆመው የለም ብለዋል ። በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ሪያል ማድሪድ 14 ዋንጫዎችን በመውሰድ የያዘው ክብረወሰን ላልተወሰነ ጊዜ የማይደፈር ሊመስል ይችላል ።  ሆኖም ማንቸስተር ሲቲ ይህን የአውሮጳ ሻምፒዮን ውድድር በተደጋጋሚ የማያሸንፍበት ምክንያት የለምም ብለዋል ።

ቱርክ ኢስታንቡል ከተማ አታቱርክ ስታዲየም ውስጥ ቅዳሜ ዕለት ኢንተር ሚላንን 1 ለ0 በማሸነፍ ዋንጫውን ያነሳው ማንቸስተር ሲቲ በእርግጥም ገና ብዙ የመጓዝ እምቅ አቅም ያለው ቡድን ነው ። የአቡ ዳቢ ገዢ ቤተሰቦች ሐብት እና የአሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ልዩ ብቃት ብሎም የአብዛኞቹ ተጨዋቾች ችሎታ ተደምሮበት ቡድኑ ገና ብዙ ማድረግም የሚችል ነው ።

በዘንድሮ የጨዋታ ዘመን ብቻ ማንቸስተር ሲቲ የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፤ የኤፍ ኤ ካፕ እና ዋናውን የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል ። ፔፕ ጓርዲዮላ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ከዚህ ቀደም ያነሱት ከ12 ዓመታት በፊት የባርሴሎና አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት ነው ። ማሸነፋችን ገና ይቀጥላል ብለዋል ። ያን የማሸነፍ ስሜት ለማስቀጠል ደግሞ አዳዲስ ተጨዋቾችን ማስመጣትን ጨምሮ አንዳችም መሰናከል ወደ ኋላ እንዲጎትታቸው አይፈልጉም ።  ማንቸስተር ሲቲ ለዋንጫ ክብር ሲበቃ በቦታው ለተገኙት የቡድኑ ባለቤት ሼህ ማንሱር ቢን ዛይድ አል ናህያን ያን ሳይናገሩም አልቀሩም ።  

አፍሪቃውያን የእግር ኳስ ተጨዋቾች፦ ፎቶ ከማኅደርምስል Shaun Roy/Sports/empics/picture alliance

ማንቸስተር ሲቲ ባለፈው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ በቸልሲ ዋንጫውን ከማንሳት ቢገታም ፔፕ ጓርዲዮላ ጃክ ግሪሊሽን በእንግሊዝ ከፍተኛ በተባለለት ክፍያ በ139 ሚሊዮን ዶላር ወዲያው ነበር ያስመጡት ። ባለፈው የጨዋታ ዘመን ደግሞ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ምርጥ ቡድኖች በአጠቃላይ ዐይናቸውን ያሳረፉበት ኧርሊንግ ኦላንድን የቡድናቸው አባል በማድረግ የፊት መስመሩን ማጠናከሩ ተሳክቶላቸዋል ። አሁን ያልተሳካላቸው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ጁድ ቤሊንግሀምን ማስመጣቱ ነው ። ይህን ብቃት ያለው አማካይ የቡድኑ አባል በማድረጉ ፉክክር ሪያል ማድሪድ አሸንፏቸዋል ። ኢልካይ ጉንዶዋን እና ቤርናርዶ ሲልቫ እንዲሁም የኋላ ተመላላሹ ጆዋዎ ካንሴሎ ከማንቸስተር ሲቲ ሊሄዱ ይችላሉ መባሉ የአማካይ ክፍላቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል ።

በሦስት ተጨዋቾች የመከላከል አጨዋወትን በማንቸስተር ሲቲ ያስተዋወቁት አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የአማካይ ክፍላቸውን ዳግም ማዋቀሩ የሚሳካላቸው ከሆነ ቡድናቸውን በቀጣዩ የጨዋታ ዘመንም የሚያቆመው የሚኖር አይመስልም ።

ኔሽንስ ሊግ

የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜው ውድድር የፊታችን ረቡዕ እና ሐሙስ ኔዘርላንድ ውስጥ ይከናወናል ። ረቡዕ ወደ ፍጻሜው ለማለፍ አስተናጋጇ ኔዘርላንድ እና ክሮሺያ ይጫወታሉ ። ስፔን ከጣሊያን ደግሞ የሐሙስ ተፋላሚዎች ናቸው ። የአውሮጳ ኔሽንስ ሊግ ግጥሚያ የተዋቀረው ቀደም ሲል ይከናወኑ የነበሩ የወዳጅነት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ ነው ። 55ቱ የአውሮጳ ሃገራት የእግር ኳስ ቡድኖች በአውሮጳ እግር ኳስ ማኅበራት ኅብረት (UEFA) በሚሰጣቸው ደረጃ መሰረት በተለያዩ ሊጎች ይደለደላሉ ። በእየ ምድቡ 16 ቡድኖች እንደ ደረጃቸው በሊግ ሀ፣ ለ እና ሐ ውስጥ በማካተት ይጋጠማሉ ። ሊግ መ ውስጥ ሰባት ቡድኖች ይፋለማሉ ።

የኔሽንስ ሊግ ጨዋታዎች ፦ ፎቶ ከክምችት ማኅደርምስል imago images/Contrast

በዚህ ረዥም ጊዜ በወሰደ ሒደት ለግማሽ ፍጻሜ ከደረሱ አራት ቡድኖች ሁለቱ የፊታችን እሁድ ሮተርዳም ውስጥ ዋንጫውን ለማንሳት ይጋጠማሉ ። የደረጃ ጨዋታዎችም የሚደረጉት የፊታችን እሁድ ዛው ሮተርዳም ውስጥ ነው ። ባለፈው የዓለም ዋንጫ ኔዘርላንድ እና ስፔን በተሰናበቱበት ክሮሺያ አስደማሚ ጨዋታ ዐሳይታ እስከ ግማሽ ፍጻሜ ደርሳ ነበር ። በአርጀንቲና 3 ለ0 ብትሸነፍም በደረጃ ግጥሚያ ግን ሞሮኮን 2 ለ1 አሸንፋ የሦስተኛ ደረጃ ይጣ አጠናቃለች ። በሩስያው የዓለም ዋንጫም ክሮሺያ ለፍጻሜ ደርሳ ነበር ። በፈረንሳይ የ4 ለ 2 ሽንፈት ዋንጫውን ከማንሳት ተቆጠበች እንጂ ። እናስ ክሮሺያ ለረዥም ጊዜ ስትመኘው የነበረውን በዓለም አቀፍ ውድድር ከፍተኛ ማእረግ በዚህ ሳምንት በኔሽንስ ሊግ ታሳካ ይሆን?

የአርጀንቲናዊው የኳስ ጠቢብ ሊዮኔል ሜሲ የወደፊት ቡድን ኢንተር ሚያሚ ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን እያስተናገደ ነው ። በዩናይትድ ስቴትስ ዋናው ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢንተር ሚያሚ የመጨረሻው 15ኛ ላይ ይገኛል ። ቅዳሜ ዕለት በኒው ኢንግላንድ የእግር ኳስ ቡድንም የ3 ለ1 ሽንፈትን አስተናግዷል ።  ያም ብቻ አይደለም፤ ኢንተር ሚያሚ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎቹ በተከታታይ ሽንፈት አስተናግዷል።  እናም ከፈረንሳይ ሊግ ፓሪ ሳንጃርሞ ወደ ኢንተር ሚያሚ እንደሚያቀና ይፋ ካደረገው የ35 ዓመቱ አጥቂ በርካታቶች ብዙ ይጠብቃሉ ።

ሊዮኔል ሜሲ ወደ ኢንተር ሚያሚ ከማቅናቱ በፊትም ቅዳሜ ዕለት ወደ ቻይና ቤጂንግ መጓዙ ተገልጧል ። እዚያም አርጀንቲና ከአውስትራሊያ ጋር በሚቀጥለው ሳምንት ለወዳጅነት በሚኖራት ግጥሚያ ይሳተፋል ። ሊዮኔል ሜሲ ለ7ኛ ጊዜ ወደ ጎበኛት ቻይና ሲደርስም እጅግ በርካታ አድናቂዎቹ ስሙን እየጠሩ ሲያወድሱትም ታይተዋል። ሊዮኔል ሜሲ ወደ ኢንተር ሚላን ከማቅናቱ በፊት አርጀንቲና ጃካርታ ውስጥ የሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ከኢንዶኔዢያ ጋር በምታደርገው የወዳጅነት ጨዋታም ይሰለፋል ተብሏል ። ሊዮኔል ሜሲ ከፓሪ ሳንጃርሞ ጋር ያለው ውል ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሰኔ 23ይጠናቀቃል ።

ሠርቢያዊው የዓለማችን ዕውቅ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪችምስል LISI NIESNER/REUTERS

ወደ ጀርመን ስናቀና ደግሞ በቡንደስሊጋው የመጨረሻ 18ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የወረደው ሔርታ ቤርሊን የውድድር ፈቃዱ ከመሰረዝ ለጥቂት ተርፏል።  ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ያለበት ሔርታ ቤርሊን በቡንደስሊጋው ሁለተኛ ዲቪዚዮንም መጫወቱ ጥያቄ አጭሮ፤ ደጋፊዎቹንም እጅግ አስግቶ ነበር ። ሆኖም ሔርታ ቤርሊን በመጨረሻዎቹ ሰዓታት በጀርመን እግር ኳስ ሊጋ (DFL)የገንዘብ አቅሙን ጨምሮ የተጠየቀውን መስፈርቶች በማሟላቱ በሁለተኛ ዲቪዚዮን እንዲጫወት ዛሬ ፍቃድ ተሰጥቶታል ።  በስተመጨረሻ ዛሬ ውሳኔው ሌላ ቢሆን ኖሮ ሔርታ ቤርሊን ምናልባትም ከሊጋዎች እጅግ አሽቆልቁሎ በአካባቢያዊ ሊጎች ለመጫወት ይገደድ ነበር ። ሔርታ ቤርሊን የ60 ሚሊዮን ዩሮ ክፍተት ነበረበት ተብሏል ።

የሜዳ ቴኒስ

ሠርቢያዊው የዓለማችን ዕውቅ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች ለ23ኛ ጊዜ በወንዶች ፉክክር ታላቁን ድል በመቀዳጀት ክብረወሰን መስበር ችሏል ። ኖቫክ በአንድ የውድድር ዓመት አራት ታላላቅ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜዎች ላይ ድሎችን በመቀዳጀት ማለትም ዋና የሚባለውን «ግራንድ ስላም» ለ23ኛ ጊዜ በማሸነፉ በእርግጥም ብርቱ አትሌት መሆኑን አስመስክሯል ።  ይህም ብቻ አይደለም ለ94 ጊዜያት የቴኒስ ባለሞያዎች ማኅበር (ATP) ግጥሚያዎች ላይ አሸንፎ ዋንጫዎችን ሰብስቧል ። በዚሁ ተመሳሳይ ግን ደግሞ በጥንድ በተኪያሄዱ ግጥሚያዎች ላይ ደግሞ 38 ዋንጫዎችን ሰብስቧል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW