1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰኔ 6 ቀን፣ 2014 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሰኔ 6 2014

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በማላዊ ሜዳ ቆይታው ከወጪ ቀሪ አስልቶ «ትርፍ» ማስመዝገቡን ገልጧል። በርካቶች በሜዳችን እና በደጋፊያችን ፊት የበለጠ ድል ለመቀዳጀት ከደረጃ በታች ናቸው የተባሉ ስታዲየሞቻችን በአፋጣኝ መፍትኄ ይበጅላቸው ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

Fußball | Nations League | Deutschland - Ungarn
ምስል Attila Kisbenedek/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

ዋሊያዎቹ ከሜዳቸው ውጪ እንዲጫወቱ በተገደዱበት ግጥሚያ ያልተጠበቀ ድል ማስመዝገባቸው የእግር ኳስ አፍቃሪውን ከጥግ እስከ ጥግ አስፈንድቋል። ድሉ ደግሞ ለሦስት ዐሥርተ ዓመታት በአሸናፊነት የበላይ በነበረው የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ላይ መኾኑ ልዩ ትርጉም ተሰጥቶታል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በማላዊ ሜዳ ቆይታው ከወጪ ቀሪ አስልቶ «ትርፍ» ማስመዝገቡን ገልጧል። በርካቶች በሜዳችን እና በደጋፊያችን ፊት የበለጠ ድል ለመቀዳጀት ከደረጃ በታች ናቸው የተባሉ ስታዲየሞቻችን በአፋጣኝ መፍትኄ ይበጅላቸው ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል።  ናይጄሪያ በአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ ሳዎቶሜ እና ፕሪንሲፔን ዛሬ ከሰአት ገጥማ እንዳልነበረች አድርጋ ጉድ ሠርታታለች። 

የዋሊያዎቹ ድል

ያለፈው ሳምንት ኢትዮጵያውያን ከጥግ እስከ ጥግ ጮቤ የረገጡበት ድል የተመዘገበበት ታሪካዊ ሳምንት ነው። የአፍሪቃ ዋንጫን ለ7 ጊዜያት ማንሳት የቻለውን ከአፍሪቃ ጠንካራውን የግብጽ ቡድን ዋሊያዎቹ 2 ለ0 ድል ማድረጋቸው በብዙዎች ዘንድ እጅግ አስደማሚ ኹኔታ ፈጥሯል። ከግብ ጠባቂ እስከ ተከላካይ፤ ከአማካይ እስከ አጥቂ ክፍል እጅግ ልዩ ውበት በታየበት ጨዋታ ዋሊያዎቹ ፈርኦኖቹን በታሪካዊው ድል ከ33 ዓመት በኋላ በማሸነፋቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለቡድኑ ሁለት ሚሊዮን ብር የማበረታቻ ገንዘብ እንደሚሰጥ ዐስታውቋል።

በተያያዘ ዜና፦ ደረጃውን የጠበቀ የመጫወቺያ ሜዳ የለውም በሚል ውድድሩን በማላዊ ሜዳ ለማድረግ የተገደደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን «በማላዊ ቆይታ ከወጪው በላይ ትርፍ አስመዝግቧል» ሲል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዘግቧል። በስታዲየሙ 20 ሺህ ተመልካች እንዲታደም ተፈቅዶ የነበረ ሲሆን፤ 30 የቴሌቪዥን እና 120 የሬዲዮ ማስታወቂያዎች ተነግረው ገቢ መገኘቱም ተገልጧል። ከቲኬት ሽያጭ እና በሜዳ ዙሪያ ከነበሩ 22 የማስታወቂያ ሰሌዳዎች የተገኘው ገቢ ለማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚሰጠው ተቀንሶ እና ተደምሮ ትርፍ መገኘቱ ተገልጧል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፦ «የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከግብፅ ጋር ባደረገው ጨዋታ 68,000 ዶላር የተጣራ ገቢ ማገኘት ችሏል» ሲልም በድረ ገጹ ጽፏል።

በርካታ አስተያየት ሰጪዎች ቀጣይ ውድድሮችን ዋሊያዎቹ በደጋፊያቸው ፊት ሀገር ውስጥ እንዲያደርጉ በፍጥነት ስታዲየሞች እደሳ ላይ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ሲሉ ተማጽነዋል። ፌፌሬሽኑ ማላዊ ውስጥ ባደረገው ጨዋታ ትርፍ ማግኘቱ መልካም ዜና ኾኖ በሀገር ውስጥ ጥራቱን የጠበቀ ስታዲየም ባለመኖሩ ግን በሜዳው ሊያካኺድ የሚገባቸውን ግጥሚያዎች ከሀገር ውስጥ እንዲያደርግ መገደዱ እጅግ የሚያሳዝንም የሚያስቆጭም ነው።

ሴካፋ

ምስል Charly Triballeau/Getty Images/AFP

በሌላ ዜና ደግሞ፦ በሴካፋ ውድድር ውጤት ላስመዘገቡት የሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ5,000,000.00 (አምስት ሚልየን ብር) ሽልማት ማበረክሩን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጠቅሷል።  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በሴካፋ ውድድር የታንዛኒያን ቡድን 1 ለ0 በማሸነፍ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው የነሐስ ተሸላሚ ኾነዋል።

የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪቃ እግር ኳስ ማኅበራት ምክር ቤት (CECAFA) የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን የወሰደችው ኡጋንዳ ለአፍሪቃ ዋንጫ ፉክክር ከአዘጋጇ አገር ሞሮኮ ጋር ተመድባለች።  የሴካፋ ተወካይ መሆን የቻሉት ግን በግማሽ ፍጻሜው ከኢትዮጵያ ጋር ብርቱ ፉክክር አድርጋ 1 ለ0 በማሸነፍ በፍጻሜው ዋንጫውን የወሰደችው ኡጋንዳና ሁለተኛ የወጣችው ቡሩንዲ ናቸው። ኡጋንዳ በሴካፋ ፍጻሜ ቡሩንዲን 3 ለ1 ነው ያሸነፈችው። የአፍሪቃ የሴቶች ዋንጫ ውድድር ከሰኔ 25 እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2014 ዓ.ም በሞሮኮ አዘጋጅነት ይከናወናል። በሦስት ምድብ በተከፈለው ፉክክር፦ ከሴካፋ አንደኛ የወጣችው ኡጋንዳ ከአዘጋጇ ሞሮኮ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ሴንጋል ጋር ተመድባለች። ሁለተኛ የወጣችው ቡሩንዲ ደግሞ ከናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪቃ እና ቦትስዋና ጋር ትጋጠማለች። በሦስተኛው ምድብ ካሜሩን፣ ዛምቢያ፣ ቱኒዝያ እና ቶጎ ይገኛሉ።   

አትሌቲክስ

ሞሪሽየስ ውስጥ ሰኔ 1 ጀምሮ ትናንት በተጠናቀቀው 22ኛው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያ 4 የወርቅ፣ 6 የብር እና 4 የነሐስ በድምሩ 14 ሜዳሊያዎችን በማግኘት የ5ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።  ኢትዮጵያ ከሰበሰበቻቸው 14 ሜዳሊያዎች አንድ ተጨማሪ ወርቅ ቢኖር ኖሮ ያለተቀናቃኝ የሦስተኛ ደረጃን ትይዝ ነበር። በውድድሩ ኬንያ በ23 ሜዳሊያ የበላይነትን ይዛ አንደኛ ወጥታለች። ኬንያ ያገኘችው 10 የወርቅ፣ 5 የብር እና 8 የነሐስ ሜዳሊያዎችን ነው። ከኬንያ በመቀጠል ደቡብ አፍሪቃ በ9 የወርቅ፣ 13 የብር እና 14 የነሐስ ሜዳሊያዎች የሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች። ናይጀሪያ እና አልጀሪያ ተመሳሳይ 5 የወርቅ እና 3 የብር ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል። 3 የነሐስ ሜዳሊያዎች ያገኘችው ናይጀሪያ አልጄሪያን በ2 ነሐስ በልጣ በድምሩ 11 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የሦስተኛ ደረጃን መያዝ ችላለች።  

ምስል picture-alliance/Rolf Kosecki

የማርሴሎ ስንብት

ብራዚሊያዊው የሪያል ማድሪድ ተከላካይ ማርሴሎ ዛሬ ከቡድኑ በእንባ እንደተዋጠ የስንብት አሸኛኘት ተደረገለት። ማርሴሎ የዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ከወሰደው ሪያል ማድሪድ ጋር ለ15 ዓመታት ከአምስት ወራት አብሮ ቆይቷል። ሪያል ማድሪድ በማሽምፒዮንስ ሊግ ሊቨርፑልን 1 ለ0 ባሸነፈበት ወቅት የ34 ዓመቱ ብራዚሊያዊው የግራ ተከላካይ የተቀያሪ ወንበር ላይ ነበር። ማርሴሎ በሪያል ማድሪድ ቆይታው ከላሊጋው አንስቶ በርካታ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል። ለሁሉም ጊዜ አለውና በታዳጊነቱ ወደ ቤርናቤዎ ያቀናው ብራዚሊያዊ ተጨዋች በ34 ዓመቱ ከሪያል ማድሪድ መሰናበቱ ግድ ኾኗል።

ሪያል ማድሪድ ለብራዚሊያዊው ወሳኝ ተጨዋቹ ኤስታዲዮ ሣንቲያጎ ቤርናቤዎ ውስጥ ካደረገለት ስንብት ባሻገር ዛሬ ቤተሰቦቹ፣ የቡድኑ ወዳጆች እና ጋዜጠኞች በተገኙበት ንግግር አድርጎ እንዲሰናበት ኹኔታዎችን አመቻችቶለታል። በእንባ የተዋጠው ማርሴሎ በሪያል ማድሪድ ቆይታው ከጎኑ ለነበሩ ኹሉ ምስጋናውን አቅርቧል። ወደፊት ምን እንደሚያደርግ ተጠይቆም ቅድሚያ ለቤተሰቡ ሰጥቶ ደስታውን ማጣጣም ከዚያም በቅርቡ መልሱን ይዞ ብቅ እንደሚል ተናግሯል።

ምስል Lee Smith/REUTERS

የዝውውር ዜና

የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙን አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድ ወደ እንግሊዝ ማንቸስተር ሲቲ የመዘዋወሩ ዜና እርግጠኝነት ዛሬ ይፋ ኾኗል። ኖርዌያዊው አጥቂ ወደ ማንቸስተር ሲቲ መምጣቱ እውን መኾኑን ማንቸስተር ሲቲ በይፋዊ የትዊተር ገጹ፦ «እዚህ ነው ያለው» ሲል የኧርሊንግ ኦላንድን ፎቶ በቪዲዮ አጅቦ ለተከታዮቹ አቅርቧል። በአጭር ቪዲዮውም፦ «እንኳን ደህና መጣህ» የሚል ተጽፏል።

የእግር ኳስ የማጣሪያ ውድድሮች

የአውሮጳ የኔሽን ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ዛሬ ማታም ቀጥሎ ይከናወናል። በምሽቱ ፉክክር፦ ዴንማርክ ከአውስትሪያ፤ ፈረንሳይ ከክሮሺያ፤ አይስላንድ ከእስራኤል፤ ካዛክስታን ከስሎቬኒያ እንዲሁም አዘርባጃን ከቤላሩስ ጋር ይጋጠማሉ። ነገ ማታ ደግሞ ጀርመን ከጣሊያን እንዲሁም እንግሊዝ ከሐንጋሪ ጋር በተመሳሳይ ሰአት ይጫወታሉ። ጀርመን በሦስቱ ጨዋታዎቿ አቻ በመውጣት ባገኘችው 3 ነጥብ በምድቡ 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ጣሊያን በ3 ጨዋታዎች 5 ነጥብ ሰብስባ ከምድቡ አንደኛ ናት። ሐንጋሪ በ4 ነጥብ 2ኛ፤ እንግሊዝ በ2 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ነገ የፖላንድና ቤልጂየም እንዲሁም ኔዘርላንድ እና ዌልስን ጨምሮ ሌሎች የኔሽን ሊግ ጨዋታዎችም አሉ።

ለአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ደግሞ ዛሬ ማታ ሞሮኮ ከላይቤሪያ ጋር ይጋጠማሉ። ሴራሊዮን እና ጊኒ ቢሳዎ እየተጫወቱ ሲሆን፤ ናይጄሪያ ሳዖቶሜ እና ፕሪንሲፔን ከሰአታት በፊት በሰፋ የግብ ልዩነት 10 ለ0 አንኮታኩታታለች። የ23 ዓመቱ አጥቂ ቪክቶር ኦሲምሄን ከሔርትሪክም በላይ ለብቻው 4 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። 

ከአፍሪቃ እና አውሮጳ አኅጉራት ባሸገር አውስትራሊያ እና ፔሩ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የፍጻሜ ግጥሚያቸውን በዛሬው ምሽት ያከናውናሉ። ኮናክፋን ወክሎ በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ኳታር ውስጥ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ ነገ ማታ ኮስታ ሪካ እና ኒውዚላንድ በፍጻሜው ይጋጠማሉ። ባለፈው ግጥሚያ ኮስታሪካ ኒውዚላንድን 4 ለ0 አሸንፋለች።

የሜዳ ቴኒስ

ሩስያዊው የሜዳ ቴኒስ ዕውቅ ተጨዋች ዳኒል ሜድቬዴቭ ከዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋቾች በነጥብ ልቆ አንደኛ ኾነ። ካለፉት 19 ዓመታት ወዲህ ከኖቫክ ጄኮቪች፣ ራፋኤል ናዳል፣ ሮጄር ፌዴሬር አለያም አንዲ ሙራይ ውጪ እንዲህ ላለው ድል ሌላ ሰው ሲበቃ ይህ የመጀመሪያው ነው። ሩስያዊው የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚከናወነው የዌምብልደን ፍጻሜ ግን እንዲጫወት አይፈቀድለትም። ዊምብልደን የሩስያ እና የቤላሩስ ተጨዋቾች እንዳይሳተፉ እገዳ በመጣሉ ዳኒል መሳተፍ ባይችልም ተጨማሪ ውድድሮችን አሸንፎ ነጥቡን ያስጠብቃል የሚል ግምት ተሰጥቷል።

ምስል John Walton/empics/picture alliance

ሩስያዊው ዳኒል ሜድቬዴቭ እስካሁን 7.950 ነጥብ በመሰብሰብ ነው አንደኛ የኾነው። ጀርመናዊው አሌክዛንደር ዜቬሬቭ በ7.075 ነጥብ በሁለተኛነት ይከተላል። ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች በ 6.700 እንዲሁም ስፔናዊው ራፋኤል ናዳል በ6.525 ነጥብ የሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።  እስካለፈው ሳምንት ድረስ በአጠቃላይ ነጥብ መሪው ኖቫክ ጄኮቪች ነበር።

የመኪና ሽቅድምድም

በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት ጀርባው ላይ መጠነኛ ጉዳት የደረሰበት ሌዊስ ሐሚልተን የካናዳ ፍጻሜ ላይ እንደሚሳተፍ ዐስታወቀ። ሌዊስ ሐሚልተን በውድድሩ ወቅት በደረሰበት ጉዳት ጀርባው ላይ አነስተኛ መበለዝ እና መጠነኛ የእንቅልፍ ማጣት እንዳጋጠመው ቢገልጥም አሁን በጥሩ መነቃቃት ላይ እንደሚገኝ ገልጧል። ካናዳ ሞንትሪያል ውስጥ የሚካኼደው ቀጣዩ ውድድርም በሕይወት ዘመኑ «ፈታኙ» እንደሚሆን በመጥቀስ ለዚያ ዝግጁ መኾኑን ዐሳውቋል። በትናንንቱ የአዘርባጃን ፉክክር ብሪታንያዊው ሌዊስ ሐሚልተን በ4ኛ ደረጃ ነው ያጠናቀቀው። በትናንቱ ውድድር የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን አንደኛ መውጣት ችሏል። ሌላኛው የቡድን አጋሩ ሠርጂዮ ፔሬዝ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል። የሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀው ደግሞ የመርሴዲስ አሽከርካሪው ጆርጅ ሩሴል ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW