1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የሰውሰራሽ አስተውሎትን አጠቃቀም የሚቆጣጠሩ ህግ እና መመሪያዎች

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 2 2016

የሰውሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆችን የአኗኗር ዘይቬ በእጅጉ እየለወጠ ያለ እና በግለሰብም ይሁን በማህበረሰብ ደረጃ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው ቴክኖሎጅ ነው። ተፅዕኖው አወንታዊ ወይም አሉታዊ ሊሆን ይችላል።ከዚህ አኳያ በቴክኖሎጂው አጠቃቀም ላይ የህግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎች ያስፈልጉታል የሚለው ግፊት እየተጠናከረ ነው።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ህይወት በአወንታዊም ይሁን በአሉታዊ  መልኩ እየለወጠ ነው።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ህይወት በአወንታዊም ይሁን በአሉታዊ መልኩ እየለወጠ ነው። ምስል DW

የዲጅታል መብት ተሟጋቾች በቴክኖሎጂው ላይ ህግ እንዲወጣ ግፊት እያደረጉ ነው

This browser does not support the audio element.


ሰው ሰራሽ አስተውሎት በሰው ልጆች ተፈጥሮአዊ ክህሎት የሚሰሩ ስራዎችን በተለያዩ ማሽኖች በመተካት የሚሰራ ቴክኖሎጅ ነው።ይህ ቴክኖሎጅ በአሁኑ ወቅት የሰው ልጆችን የአኗኗር ዘይቬ በእጅጉ እየለወጠ በመሆኑ በግለሰብም ይሁን በማህበረሰብ ደረጃ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል አይለም።
በዚህ ቴክኖሎጅ  ሰው አልቫ ተሽከርካሪዎችን ፣ድምጽን ወደ ጽሁፍ የሚቀይሩ መተግበሪያዎችን ፣ ቁንቁን ለመተርጎም የሚያገለግሉ ዲጅታል መድረኮች ፣ የምናውቃቸውን ሰዎች በፌስቦክ  ለማገናኘት፣ ዩቲዩብ ላይ ከተመለከትነው  ቪዲዮ ጋር ተያያዥነት ያለውን ሌላ ቪዲዪ ለመጠቆም ያገለግላል። በአጠቃላይ ቴክኖሎጂውአገልግሎቱ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች  ላይ የምናየውን ይዘት  ከሚወስኑት ስልተ ቀመሮች ጀምሮ  ሀኪሞች በራጅ ካንሰርን ለመለየት የሚረዱ ጽሑፎችን ወይም ምስሎችን ለማመንጨት እስከሚረዱት ሶፍትዌሮች ድረስ  ይዘልቃል።

የአዲስ ዌይ የቴክኖሎጅ ኩባንያ መስራች እና የሰውሰራሽ አስተውሎት ባለሙያ የሆኑት አቶ መሀመድ ኑር ኢብራሂም እንደሚሉት ይህ ቴክኖሎጂ ባደጉ ሀገራት ብቻ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በአዳጊ ሀገራትም ጠቀሜታው  እየተለመደ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ቴክኖሎጂው በጨርቃጨርቅ እና በፋሽን ኢንደስትሪው ሞዴል ሆነው የሚገለግሉ፣በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታይ ያላቸው  ነገር ግን ትክክለኛ ሰዎች ያልሆኑ ይዘት ፈጣሪዎችን መመልከትም እየተለመደ መጥቷል።
በተለይ ዲፕፌክ /deepfake/ የሚባለውን የሰውሰራሽ አስተውሎትን መተግበሪያ የእውነት የሚመስሉ ነገር ግን ሐሰተኛ የሆኑ ምሥሎችን እና ቪዲዮዎችም እየተሰሩ ነው።በዚህ ቴክኖሎጂ የአንድን ሰው ፎቶ እና ቪዲዮ በሌላ በመተካት እውነት  በሚመስል መልኩም ተቀናብሮ ይሰራል።

ዲፕፌክ የሚባለውን የሰውሰራሽ አስተውሎትን መተግበሪያ በመጠቀም የእውነት የሚመስሉ ነገር ግን ሐሰተኛ የሆኑ ምሥሎችን እና ቪዲዮዎችም እየተሰሩ ነው።በዚህ ቴክኖሎጂ የአንድን ሰው ፎቶ እና ቪዲዮ በሌላ በመተካት እውነት በሚመስል መልኩም ተቀናብሮ ይሰራል።ምስል DW

የሰውሰራሽ አስተውሎት አሉታዊ ጎኖች

ከዚህ አንፃር ሰውሰራሽ አስተውሎት በርካታ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም ሐሰተኛ መረጃ እና  ዜናን ማሰራጨትን፣ በከፍተኛ ደረጃ በሰዎች ላይ ክትትል ማድረግን፣ ከዚህ ቀደም በዓለማችን የሚታዩ  የፍትሃዊነት እና የእኩልነት ችግሮችን እንዲባባስ ማድረግን እንዲሁም  የሰዎችን ሚና በመተካት ከስራ ገበታ ማፈናቀልን የመሳሰሉ ችግሮችን ሊያጎላ ይችላል።ሰውሰራሽ አስተውሎትና ሐሰተኛ ወሬዎች

አክሰስ ናው የተባለው የዲግታል መብት ተሟጋች ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ፋኒ ሂድቬጊ በበኩላቸው ይህ ቴክኖሎጅ የሰው ልጆችን ስተት ሊደግም ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። «ሰው ሰራሽ አስተውሎት ፣ የማሽን መማር /ማሽን ለርኒንግ / እነዚህ ሁሉ፣ ውስብስብ ስልተ ቀመሮች እና የውሂብ ስብስቦች እኛ የሰው ልጆች ያለብንን አድሏዊነት እነሱ ይደግሙታል ማለት እንችላለን።»
አቶ መሀመድ ኑርም ስጋቱን ይጋሩታል።«አንዳንዴ እነዚህ «ሲስተሞች» መሬት ላይ ያለውን ወደ ኤ አይ «ሲስተም» የሚወስደው ማለት ነው።ለምሳሌ ለሴቶች ለአካል ጉዳተኞች ለመሳሰሉት ድጋፍ የማያደርግ «ሲስተም» ካለ፤ ወደ AI በሚሄድበት ጊዜ መሬት ላይ ያለው ነፀብራቅ ነው።ወደ ሲስተሙ የሚሄደው።እና እንደዚህ እንደዚያህ ያሉ ችግሮች AI ላይ  በሀገራችንም በሉሎች ሀገራትም እየተስተዋለ ይገኛል።»በማለት ገልፀዋል።

የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን ለመቆጣጠር የህግ ማዕቀፍ

እነዚህ  ችግሮች ያሰሰቧቸው እንደ ሄድቪኒ ያሉ የዲጅታል መብት ተሟጋቾች ፣ ፖለቲከኞች እና የቴክኖሎጂ ተቋማት መሪዎች ታዲያ  የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን ለመቆጣጠር የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል የሚል ግፊት እየተጠናከረ መጥቷል።

የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ በጎርጎሪያኑ ሰኔ 2023 ዓ/ም ሕግ ለማውጣት የሚያስችለውን ሰነድ ያፀደቀ ሲሆን፤ ያለፈው መጋቢት አጋማሽ 2024 ዓ/ም ደግሞ ሰውሰራሽ አስተውሎትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ አፅድቋል።ምስል Christian Ohde/CHROMORANGE/picture alliance

እንደ ፣አሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና ቻይና ያሉ ሀገራት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍን የሚቆጣጠር ሕግ ለማውጣት እየተዘጋጁ ነው።የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ  በጎርጎሪያኑ ሰኔ 2023 ዓ/ም ሕግ ለማውጣት የሚያስችለውን  ሰነድ ያፀደቀ ሲሆን፤ ያለፈው መጋቢት አጋማሽ 2024 ዓ/ም ደግሞ ቴክኖሎጂውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ አፅድቋል። አቶ መሀመድ ኑር ም መሰል ህጎች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በአዳጊ ሀገራትም ያስፈልጋሉ የሚል እምነት አላቸው።ሰው ሰራሽ አስተውሎት የመጭው ዘመን ፈተና

«ብዙ ጊዜ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሲባል ለኢትዮጵያ ቅንጦት ነው ።ያደጉ ሀገራት ይጠቀሙበት እንጅ እኛን አይመለከተንም ተብሎ ይታሰባል።በተለይ በፖሊስ እና ህግ አውጭዎች ትልቅ ትኩረት እየሰጡት ነው የሚል እምነት የለኝም።»ካሉ በኋላ፤ 
ነገር ግን ቴክኖሎጅውን ይነስም ይብዛም በኢትዮጵያም በተለያዩ ዘርፎች ጥቅም ላይ እየዋለ በመሆኑ የሚያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ ህግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል። ቴክኖሎጂውን ለመቆጣጠር የሚወጡት  ህጎችም እንደየ አስፈላጊነታቸው በየዘርፉ ቢዘጋጁ የተሻለ መሆኑን ያስረዳሉ።

« በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በየዘርፉ ለምሳሌ ጤና ዘርፍ ካለ ጤናን የሚመለከት እንዴት ነው ሰውሰራሽ አስተውሎትን ለጤና የምንጠቀመው፤በትምህርት ዘርፍም እንዴት ነው የምንጠቀመው፤እያልን ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎቻችን፤ህግ ቢኖሩት መልካም ነው።» ብለዋል። 

በዲጅታል መብት ተሟጋቾች ፣ ፖለቲከኞች እና የቴክኖሎጂ ተቋማት መሪዎች ዘንድ  የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀምን ለመቆጣጠር የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል የሚል ግፊት እየተጠናከረ መጥቷል።ምስል Michael Bihlmayer/CHROMORANGE/picture alliance

 ቁጥጥር ማድረግ ፈጠራን ያቀጭጫል የሚል ስጋት

አንዳንድ ባለሙያዎች ግን  በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ  ከልክ በላይ ቁጥጥር ማድረግ ለፈጠራ እንቅፋት ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው።
ከነዚህም መካከል 400 የሚያህሉ ኩባንያዎችን የሚወክለውን የጀርመን የሰውሰራሽ አስተውሎት ማኅበር እንዲመሰረት ያደረጉት ራስመስ ሮቴ አንዱ ናቸው።እሳቸው እንደሚሉት በዚህ ቴክኖሎጅ ላይ የቁጥጥር ህጎችን ማውጣት ፈጠራን ያቀጭጫል። 

«ሰው ሰራሽ አስተውሎት በጭራሽ ጥሩ ወይም መጥፎ አይለም። ተመሳሳይ ስልተቀመር/አልጎሪዝም/ የሳይበር ጥቃትን  ለማድረግ እንዲሁም ካንሰርን ለይቶ ለማወቅ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ። ስለዚህ  ሰው ሰራሽ አስተውሎት  ጥቅም ላይ እንደሚውልበት ምክንያት ይወሰናል። ስለዚህ  ዋናው ነገር ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ማን ለምን ጉዳይ እየተጠቀመበት ነው።የሚለው ነው።ከትናንሽ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ብዙ ፈጠራዎችን ይሰራሉ። እና ብዙ ደንቦችን ባስቀመጥን ቁጥር ከትንንሽ ኩባንያዎች የምናየው ፈጠራ ይቀንሳል።»ብለዋል።ሰው ሰራሽ አስተውሎት የመጭው ዘመን ፈተና

አደጋዎቹን በመቀነስ የሰው ሰራሽ አስተውሎት  ለመጠቀም

በዚህ የተነሳ የአውሮፓ ህብረት ህግ አውጪዎች የሁለቱንም ወገኖች ስጋት ሚዛናዊ ለማድረግ በሚመስል መልኩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት  ስርዓቶችን እንደ ስጋት ደረጃቸው ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ህጎችን ማውጣት ላይ አተኩሯል።

እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ የዚህ ቴክኖሎጅ ውጤቶች ከመጡ ወዲህ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰው ልጆች የወደፊት ህይወት ያለው ተፅዕኖ አነጋጋሪ እየሆነ መጥቷልምስል Andreas Franke/picture alliance

ማለትም ቁጥጥሩ እንደ ስጋት ደረጃቸው ይለያያል።የሚያደርሱት አደጋ መጠነኛ ሲሆን፤ለምሳሌ ለጥቃት የሚያጋልጡ የኢሜይል  መልዕክቶችን ለማጣራት ጥቅም ላይ በየሚውል የሰውሰራሽ አስተውሎት ላይ ጥቂት ደንቦች ብቻ ተፈጻሚ ይሆናሉ። ነገር ግን ህይወትን ሊቀይሩ የሚችሉ  መተግበሪያዎች፣ ለምሳሌ የትኞቹ ተማሪዎች ለከፍተኛ ትምህርት ብቁ እንደሆኑ ለመወሰን፣ ጥቅም ላይ የሚውሉ እና መሰል የሰውሰራሽ አስተውሎት የሚሰሩ መተግበሪያዎች ላይ  ህጎቹ የበለጠ ጥብቅ ይሆናሉ። አንዳንድ መተግበሪያዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ይታገዳሉ።
የዚህ ዓላማም አደጋዎቹን በመቀነስ የሰው ሰራሽ አስተውሎት  ለመጠቀም ያስችላል። ባለሙያው አቶ መሀመድ ኑር ይህንን አሰራር በመደገፍ  ምሳሌዎችን ያቀርባሉ።
ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም የሰውሰራሽ አስተውሎትን አጠቃቀም የሚቆጣጠሩ ፖሊሲዎች የማውጣት ጅምሮች መኖራቸውን ገልፀው፤ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ባለሙያው አቶ መሀመድኑር ኢብራሂም አሳስበዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW