1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ዕድል እና ፈተና በአፍሪቃ

ረቡዕ፣ ኅዳር 10 2018

ሰውሰራሽ አስተውሎት በዓለም ላይ በፍጥነት እያደገ ያለ ቴክኖሎጂ ነው።ቴክኖሎጂው ትምህርትን ግላዊነት በማላበስ፣ በቂ አገልግሎት ለሌላቸው ተማሪዎች ተደራሽነትን በማሻሻል በአፍሪካ በትምህርት ላይ በጎ ተጽእኖ እያሳደረ ነው።ያም ሆኖ ቴክኖሎጂውፈተናዎችም አሉት።ባለሙያዎች ፈተናዎቹን ለመሻገር ቴክኖሎጂው የሚገዛበት ፖሊሲዎች ማውጣትን ይመክራሉ።

የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ
የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ በአፍሪቃ እያደገ ያለ ቴክኖሎጂ ነው።ምስል፦ DW

የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ዕድል እና ፈተና በአፍሪቃ

This browser does not support the audio element.

የሰውሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሊጂ ልክ እንደሌላው ዓለም ባይሆንም በአፍሪቃም  በማደግ ላይ ያለ ቴክኖሎጂ ነው።ቴክኖሎጂው በአፍሪቃ የለውጥ አጋዥ ሆኖ በማገልገል  ኢኮኖሚያዊ እድገትን ፣ የጤና እና ሌሎች አገልግሎት አሰጣጥንም ለማሳደግ ሊውል ይችላል።ሰው ሰራሽ አስተውሎት  (AI) ትምህርትን ግላዊነት በማላበስ፣ በቂ አገልግሎት ለሌላቸው ተማሪዎች ተደራሽነትን በማሻሻል በአፍሪቃ በትምህርት ላይ በጎ ተጽእኖ እያሳደረ  ነው። ይህም የመማር ማስተማር ሥራን በማሻሻል ለአፍሪቃ ወጣቶች አዲስ እድል ሊፈጥር ይችላል። ቴክኖሎጂው በተለይ በገጠር ለሚገኙ ተማሪዎች አካታች  የትምህርት አካባቢን ለመፍጠር እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሊገኙ የማይችሉ ልዩ መሣሪያዎችን እና ግብዓቶችን በማቅረብ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች መደገፍ ይችላል።

የሶፍትዌር ባለሙያው እና መጻሕፍትን በበይነመረብ ለማንበብ የሚረዳው «የአፍሮ ሪድ» መተግበሪያ ተባባሪ መስራች አቶ ዳዊት ዓለሙ የሰውሰራሽ አስተውሎት የትምህርት ይዘትን ለተማሪዎች ፍላጎቶች በሚስማማ መልኩ በማዘጋጀት፣ የመምህራንን የሥራ ጫናዎችን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ይገልፃሉ።በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በርካታ ተማሪዎች በአንድ ክፍል ለሚታጨቁበት ሀገር ጥሩ መፍትሄ መሆኑንም ያስረዳሉ።
ተማሪዎች መምህራንን ሳይጠብቁ በራሳቸው ፍላጎት ዕውቀት እንዲቀስሙም ቴክኖሎጅው ያግዛል።በውጭ በሀገር የሚገኙ የትምህርት ሀብቶች በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ለማቅረብም ይረዳል።
በጎርጎሪያኑ ኅዳር መጀመሪያ  ከ1,500 በላይ የትምህርት እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በጋና መዲና አክራ  የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ  በትምህርት ላይ ስላለው ተጽእኖ መክረዋል። ዋናው መሪ ሀሳብ ፡ ለወጣቶች ፈጠራ እና የዘላቂ ልማት እድሎችን ለመክፈት ሰውሰራሽ አስተውሎትን (AI)ን ከትምህርታዊ ስርዓቶች ጋር ማዋሃድ የሚል ነበር።የጋና-ህንድ ኮፊ አናን የአይሲቲ የልህቀት ማዕከል ባልደረባ የሆኑት ጌዲዮን ኦውሱ አግዬማንግ እንደሚሉት ስለትምህርት እና ሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ሲነሳ፤  በትምህርት አካባቢ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተጠቀምንባቸው ያሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ወይም ደግሞ በትምህርት ስርአቶች ውስጥ መማር እና ማስተርን ለማሳደግ የምንጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂዎች ያካትታል። በዚህም ሰውሰራሽ አዲፕሲክ፤የቴክኖሎጂ አብዮት ያስነሳው አዲሱ የቻይና መተግበሪያ ስተውሎት ቴክኖሎጂ የመማር ማስተማር ሂደትን ያሻሽላል።

በትምህርት ውስጥ የቴክኖሎጂው  ስጋቶች እና እድሎች

ያም ሆኖ ቴክኖሎጂው በተለያዩ ዘርፎች ጠቃሚ የመሆኑን ያህል ፈተናዎችም አሉት።ባለሙያዎች ፈተናዎቹን ለመሻገር ቴክኖሎጂው የሚገዛበት ፖሊሲዎች እና መመሪያዎችን ማውጣትን ይመክራሉ።
ምንም እንኳ ቴክኖሎጂው ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም ፣ በአፍሪቃ አንዳንድ መምህራን በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች ከቴክኖሎጂው ባህሪ  እና አሉታዊ ጎኖች አንፃር ስጋት አላቸው።አፍሪካውያንን በሰውሰራሽ  ቴክኖሎጂዎች የሚያሠለጥነው  የኤአይ አፍሪቃ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ዴቪድ ኪንግ ግን አይስማሙም። «የዩንቨርስቲ ፕሮፌሰሮች የሰው ሠራሽ አስተውሎትን የመፍራት ሐሳብ፤ ከታላቅ አክብሮት ጋር ለመናገር በአብዛኛው ካለማወቅ የተነሳ ነው።» ብለዋል።
ቴክኖሎጂው ከእኛ ጋር ከመቶ አመት በላይ የቆየ እንጅ፤ትናንት የመጣ አይለም የሚሉት ዶክተር ዲቪድ ከስጋት ይልቅ ስፋት ያለው ስልጠና እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።«የኛ ድርጅት 11 ሚሊዮን አፍሪቃውያንን በሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ለማሰልጠን እንፈልጋለን።እስካሁን 2 ነጥብ 3  ሚሊዮን አሰልጥነናል።  ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበርም ሰውሰራሽ አስተውሎትን AIን በኃላፊነት ለመጠቀም እየሞከርን ነው።ጥያቄው ለምን እንፈራለን? ምንድነው የምንፈራውሥ? ነው። ተመልከቱ  ቻይና ልማትን ለማሳደግ በተለይ ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ቴክኖሎጂውን ትጠቀማለች። እና ሰዎች ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ የሚጠቀሙባቸውን መሳሪያዎች እንፈራለን። ተማሪዎች ከሌሎች  ይቀዳሉ ብለን እንሰጋለን።እዚህ ላይ ጥያቄ አነሳለሁ። ቻይና በምን ተማረች?  በመቅዳት እና በማባዛት ነው። ይቀዳሉ ። የሆነ ነገር ይመርጡ እና ያሳድጉታል። ታዲያ መቅዳት ለምን መጥፎ ነገር ይሆናል።?» በማለት ገልፀዋል።

የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ጠቃሚ የመሆኑን ያህል ፈተናዎችም አሉት።ባለሙያዎች ፈተናዎቹን ለመሻገር ቴክኖሎጂው የሚገዛበት ፖሊሲዎች ማውጣትን ይመክራሉ።ምስል፦ Andreas Franke/picture alliance

የጋና የትምህርት ትረስት ፈንድ መስራች እና የቀድሞ የጋና የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኤክዎው ስፒዮ-ጋርብራህ ለDW እንደተናገሩት ቴክኖሎጂው ብዙ አወንታዊ ፋይዳዎች ቢኖሩም አፍሪካ እና የትምህርት ተቋሞቿ አሁንም ጉዳዩ የገባቸው አይመስልም ይላሉ። እናም ሊፈጠሩ የሚችሉትን እና አደጋዎችን በንቃት መከታተል እንዳለባቸው ያስጠነቅቃሉ። 
አያይዘውም «ብዙዎቻችን ተኝተናል።ብዙ የትምህርት ተቋማት ተኝተዋል።» ነገር ግን ፣ «ማሽን የሚገነቡ ሰዎች አለምን ለመቆጣጠር በሚዘጋጁበት ደፋር እና አዲስ አለም ላይ ነን።» ሲሉም አክለዋል።
ስፒዮ-ጋርብራህ እንዳሉት የአፍሪካ የትምህርት ተቋማት አህጉሪቱ የራሷን የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች ባለቤት እንድትሆን በማሰልጠን  ላይ በንቃት መሳተፍም አለባት።

የሰውሰራሽ አስተውሎትን የሚቀርጹ ፖሊሲዎች

በተጨማሪም ስጋቶችን ለመፍታት እና አፈፃፀሙን ለመከታተል እንደ ንፖንቱ ቴክኖሎጅ የተባለ ድርጅት  ዋና ስራ አስፈፃሚ ዲቦራ አስማህ ያሉ ባለሙያዎች ግልጽ ፖሊሲዎች እንዲኖሩ ይጠይቃሉ።
«በትምህርት ውስጥ በሰውሰራሽ አስተውሎት AI ላይ ፖሊሲ ያስፈልገናል። ስለዚህ ያ ውይይት በአንድ ከፍተኛ ትምህርት ቤት ውሳኔ ላይ ብቻ የተተወ አይደለም። ነገር ግን በሰውሰራሽ አስተውሎት እና   በትምህርት ዙሪያ የታሰበበት እና የተለየ ፖሊሲ ካለ ውይይቱን  ይመራል። እኛንም ከውይይት ወደ ተግባር እንድንሄድ ያደርገናል።»ጋና የቴክኖሎጅውን እና ትምህርትን ለመምራት እና ለወጣቶች አዳዲስ እድሎችን ለመፍጠር ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት ረገድ ጋና እርምጃዎችን እየወሰደች መሆኗንም ገልፀዋል።አቶ ዳዊት በበኩላቸው በኢትዮጵያም ጥሩ ጅምር መኖሩን ይገልፃሉ።

ቴክኖሎጂው ከአፍሪቃ እሴቶች ጋር

የጋና ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ሳም ጆርጅ በበኩላቸው ከአፍሪቃዊ እሴት እና ባህል ጋር ተዛማጅነት ያለው የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ  አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል።
«ሰውሰራሽ አስተውሎት ህዝባችንን ያገለግላል፣ እሴቶቻችንን ያንፀባርቃል እና የእድገት ግቦቻችንን ያፋጥናል፣ ትብብርን፣ የመዋዕለንዋይ ፍሰትን  እና ፈጠራዎችን እንቀበላለን። ነገርግን ለዲጂታል ሉዓላዊነታችን ፍትሃዊነት፣አካታችነት እና መከባበርን አጥብቀን እንጠይቃለን።» በማለት ገልፀዋል።ሚኒስትሩ አያይዘውም የውጭ የበላይነት እንዳይኖርም አስጠንቅቀዋል፡ «አህጉሪቱ እንደገና በዲጂታል ቅኝ ግዛት እንዳትያዝም  በቴክኖሎጂው ለአፍሪቃ  የሚቀርቡ መፍትሄዎች  አፍሪካውያን ባልሆኑ ሰዎች መገንባት የለባትም።»ባይ ናቸው።

አንዳንድ አፍሪቃውያን ባለሙያዎች ሰሰውሰራሽ አስተውሎት በቴክኖሎጂ ለአፍሪቃ  የሚቀርቡ መፍትሄዎች  አፍሪካውያን ባልሆኑ ሰዎች መገንባት የለባትም ይላሉ።ምስል፦ Samir Jana/Hindustan Times/Sipa USA/picture alliance

ሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ለዘላቂ ልማት

የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ፎይበ ኩንዱሪ ቴክኖሎጂውን ለዘላቂ ልማትማበረታቻ አድርገው ይመለከቱታል።«ሰው ሰራሽ አስተውሎት  በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አሰጣጥ እንዲኖር በማድረግ የዘላቂ ልማት ግቦች እድገትን ለማፋጠን ከፍተኛ አቅም አለው።የሀብት አጠቃቀምን በማመቻቸትም ለተቀናጁ ስርዓቶች ሽግግር ለዘላቂ ፋይናንስ፣ ለትምህርት እና ለአቅም ግንባታ የፈጠራ መፍትሄዎችን በመንደፍ   የዘላቂ ልማት ግቦችን ትግበራ ለማፋጠን እና ለማሳደግ ሁሉም አስፈላጊ ናቸው።»ነገር ግን ጥንቃቄን መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።እሳቸው እንደሚሉት "ቁልፉ ነገር ኃላፊነት ያለው እና በስነምግባር ፣በሰው ልጆች እሴት እና  በፍትሃዊ ተደራሽነት የሚመራ ሁሉን አቀፍ የሰውሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጅን ማረጋገጥ ነው"ባለሙያዎቹ እንደገለፁት በአፍሪካ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት አሁን የሰውሰራሽ አስተውሎት  AI ትምህርቶችን እየሰጡ ነው፣ እና የትምህርት ስርዓቶች ቴክኖሎጂውን ለመቀበል እየተሻሻሉ ነው። ያ ከሆነ አፍሪካ የቴክኖሎጂው ተመልካች ሳይሆን መሪ መሆን ትችለለች ብለው ያምናሉ።የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባልደረባ ዋና ጸሃፊ አሚር ዶሳል። «በዚህ ዓለም አቀፋዊ ውድድር ውስጥ አፍሪካ ተመልካች አይደለችም። አናንተ ተሳታፊዎች ናችሁ።  ነበዓለም አቀፍ ደረጃ በአብዛኛው ወጣት በሆነው ህዝቧ እና  በጣም ተለዋዋጭ በሆኑ ቡድኖች ፣ በፍጥነት እየተስፋፉ ባሉ ዲጂታል መሠረተ ልማቶች አካባቢያዊ መፍትሄ የመፈለግ  ረሃብ አለ።አፍሪካ እነዚህን ጊዜ ያለፈባቸው ሞጁሎች በመሻገር ይህንን ተለዋዋጭነት  የመለወጥ ኃይል አላት።እና የአለም አቀፍ የሰውሰራሽ አስተውሎት  ህጎችን እንደገና መፃፍ ትችላለች።» ብለዋል።

ባለሙያው አያይዘውም በሰውሰራሽ አስተውሎት የተደገፈ የተሻሻለ ግብርና እስከ የጤና ነክ መፍትሄዎች እና እያንዳንዱ ልጅ  የ21ኛው ክፍለ ዘመን ክህሎት የሚያገኝበትን ግላዊ የመማሪያ ስልቶች ድረስ አፍሪቃ በቴክኖሎጂው መጠቀም እንደምትችል ገልፀዋል።እነዚህ ሁሉ ህልሞች ሳይሆኑ  የአፍሪካ ቀጣይ እጣ ፋንታ መሆኑንም አስምረውበታል።በአጠቃላይ በአፍሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) አጠቃቀም ተስፋ እና ፈተናዎች አሉት። በአህጉሪቱ  አንዳንድ ሀገሮች  ቴክኖሎጂውን ለማላመድ ባሳዩት ቁርጠኝነት  እድገቱ የተሻለ ቢሆንም፤ ሌሎች ደግሞ  እንቅፋቶች ያጋጥሟቸዋል።የአፍሪካ ሀገራት ከሌሎች የአለም ክፍሎች ጋር ያለውን ልዩነት በማጥበብ ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባለሙያዎች እንደሚሉት ሁሉን አቀፍ አካሄድ ያስፈልጋል። እነዚህን ተግዳሮቶች ለማሸነፍ እና በአፍሪካ ቴክኖሎጂውን በሙሉ  አቅም  ለመጠቀም የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ ነው። ይህም በዲጂታል መሠረተ ልማት  ልዩ ስልጠና፣ ምርምር እና ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስን ይጨምራል። ከዚህም በላይ ለፈጠራና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ለሚመራ የኢኮኖሚ ዕድገት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በመንግስት ፣ በግሉ ዘርፍ እና በሲቪል ማህበረሰብ መካከል አጋርነቶች አስፈላጊ ናቸው።
የአፍሪቃ ሀገራት በጋራ በመስራትም አሁን ያሉ ችግሮችን ወደ እድል በመቀየር እና  ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለዘላቂ ልማት በማዋል፤ የአፍሪካውያንን ህይወት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅዖ የሚያደርግበትን የወደፊት መንገድ ማመቻቸት እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW