1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
መቅሰፍትሰሜን አሜሪካ

የሰው ሕይወት ቀጥፎ በርካታ ዘመናዊ ሕንጻዎችን አመድ ያደረገው የካሊፎርኒያው እሳት

አበበ ፈለቀ
ማክሰኞ፣ ጥር 6 2017

በካሊፎርኒያ ግዛት በተከሰተው ብርቱ የሰደድ እሳት ሳቢያ ቢያንስ 24 ሰዎች መሞታቸው፤ ከ180,000 በላይ ሰዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ትተው መሰደዳቸው ተገለጠ ። ከ12,000 በላይ ሕንጻዎች፣ ት/ቤቶች፣ መኖርያ ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በእሳቱ ላንቃ ተለብልበው መውደማቸውም ተዘግቧል ።

USA Los Angeles 2025 | Zerstörung nach Palisades-Feuer in Pacific Palisades
ምስል፦ David Ryder/REUTERS

በፍጥነት የተዛመተው የካሊፎርኒያው ብርቱ የእሳት ሰደድ

This browser does not support the audio element.

በካሊፎርኒያ ግዛት በተከሰተው ብርቱ የሰደድ እሳት ሳቢያ ቢያንስ 24 ሰዎች መሞታቸው፤ ከ180,000 በላይ ሰዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ትተው መሰደዳቸው ተገለጠ ።  ከ12,000 በላይ ሕንጻዎች፣ ት/ቤቶች፣ መኖርያ ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በእሳቱ ላንቃ ተለብልበው መውደማቸውም ተዘግቧል ። እንደ ጉዳቱ ከፍተኝነት በርካታ ኢትዮጵያውያን የጥፋቱ ሰለባ ያልሆኑት ሰደድ እሳቱ ያጠቃው በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው ሰፈሮች ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች መሆኑም ተገልጿል ። በዚሁ አደጋ ሳቢያ ለተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚደረገው ድጋፍ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ትንሿ ኢትዮጵያ የሚባለው የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ተቋምና በአካባቢው የሚገኙ የንግድ ተቋማት እየተሳተፉ እንደሆነ ተገልጿል ። 

ኢትዮጵያውያን የጥፋቱ ሰለባ?

በካሊፎርኒያ ግዛት በተከሰተው ከፍተኛ የሰደድ እሳት  ሳቢያ ቤትና ንብረታቸውን ትተው የተሰደዱና ቤትና የንግድ ተቋማታቸውም የተቃጠለባቸው እንዳሉ ተገለጸ። እንደጉዳቱ ከፍተኝነት በርካታ ኢትዮጵያውያን የጥፋቱ ሰለባ ያልሆኑት ሰደድ እሳቱ ያጠቃው በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው ሰፈሮች ወጣ ብለው በሚገኙ አካባቢወች መሆኑም ተገልጿል። በዚሁ አደጋ ሳብያ ለተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚደረገውን ድጋፍ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣  ትንሿ ኢትዮጵያ የሚባለው የኢትዮጵያውያን ማበረሰብ ተቋምና  በአካባቢው የሚገኙ የንግድ ተቋማት እየተሳተፉ እንደሆነ ተገልጿል።

እስካሁን ከተከሰቱት የእሳት አደጋዎች ውስጥ ካባድና የጥፋት መጠኑ ከፍተኛ ከሆነው ጋ እንደተጋፈጠች ነው። በተለይ በሎስ አንጀለስ የተከሰተው ከፍተኛ የተባለው ሰደድ እሳት ቀናትን አስቆጥሮ፣ የጥፋት መጠኑን አስፍቶ ከ16,000 ሔክታር በላይ አካባቢን አቃጥሎ ዶጋአመድ አድርጓል።  ከ12,000 በላይ ህንጻዎች፣ ት/ቤቶች፣ መኖርያ ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች  ወድመዋል።

የሟቾች ቁጥርም ጨምሮ ቢያንስ 24 ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን 180,000 ነዋሪዎችም ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች   ለቀው ወጥተዋል። እንደ ፓሲፊክ ፓሊሴደስ፣ ፓሳዴና እና ማሊቡ ያሉ ከተሞችና ሌሎች በሎስ አንጀለስ ግዛት የሚገኙ የመኖርያ ሰፈሮች ለታሪክ የሚቀመጥ ምልክት ሳይተው  በእሳት ነበልባል  ተበልተው ሙሉ በሙሉ ጠፍተዋል።

በካሊፎርኒያ ግዛት የእሳት አደጋ ሠራተኞች ርብርብምስል፦ Ringo Chiu/REUTERS

በሆሊውድ አካባቢ ያሉ የንግድ ድርጅቶች

የካሊፎርኒያ ግዛት በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚኖርባት ግዛት ናት ። በሆሊውድ አካባቢ ያሉ የንግድ ድርጅቶች ባለቤት የሆኑት የሎሳንጀለስ ነዋሪዋ ወ/ሮ ትዕግስት ፈረደ አካላዊ ጉዳትም የቤትና የንግድ ቤት መውደምም ያጋጠማቸው ኢዮጵያውያንም እንዳሉ ገልጸዋል።

ቤታቸው ከተቃጠለባቸው ውስጥ የተወሰኑትን ያገኘኋቸው ቢሆንም አሁን ባሉበት ሁኔታ ቃለምልልስ ለማድረግ በማይችሉበት ስሜት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸውልኛል። ከነዚሁ ውስጥ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንዱ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ የወደመባቸው ኢትዮጵያዊ ክስተቱ የተለየ ውስጣዊ ህመም እንዳለው፣ በተለይ ከቤቱ ጋ ሙሉ ታሪካቸውን የያዙ፣ የትውስታቸው መገለጫ የሆኑ ዶክመንቶች አብረው መውደማቸው አንድ አካልን እንደማጣት እንደሚቆጠር ገልጸዋል። ሃብትም ንብረትም ተመልሶ ሊገኝ እንደሚችልና ከዚህ ሐዘን ማገገምና መልሶ መቋቋም ፈታኝና ረጅም ጊዜን የሚወስድ መሆኑን ያስታወሱት እኚሁ ኢትዮጵያዊ፣ ቤተሰቦቻቸው ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ ለመውጣታቸው አምላካቸውን አመስግነዋል።

ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ከወደመባቸው ሌላ ቅድመ ማስጠንቀቂያውን ተከትለው ሃብት ንብረቶቻቸውን ትተው የተሰደዱ እንዳሉ ታውቋል። እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ከሆቴልና ከመጠለያ ይልቅ በዘመድ አዝማድ ዘንድ መጠጋታቸውን ወ/ሮ ትግስት ገልጸዋል።

ካሊፎርኒያ፦ ከአውሮፕላን የእሳት ማጥፊያ ኬሚካል ርጭት ምስል፦ Daniel Dreifuss/REUTERS

የትንሿ ኢትዮጵያ ማኅበረሰብ

ሌላው የሎስ አንጀለስ ነዋሪ፣  የትንሿ  ኢትዮጵያ  ማኅበረሰብ አባልና የራሄል ኢትዮጵያ ቬጋን ኩዚን ስራ አስክያጅ አቶ ወንድወሰን ኃ/ማርያም በዚሁ ሰደድ እሳት ብዙ ኢትዮጵያውያን ያልተጎዱት እሳቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሚኖሩባቸው ሰፈሮች ራቅ ያለ ቦታ በመከሰቱ ነው ብለዋል። በዚህ ሁሉ መከራና ጭንቅ ውስጥ ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት የአካባቢው ማህበረሰብ በመረባረብ ላይ ነው። እንደ አቶ ወንድወሰን ገለጻ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ለመርዳት የሚያስፈልገውን የምግብ፣ የአልባሳት፣ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በማቅረብና በማሰባሰብ ረገድም ኢትዮጵያውያን የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ነው።

እሳቱ በሃይለኛው ሳንታ አውሎ ነፋስና በአካባቢው በተከሰተው ከባድ ድርቅ ምክንያት አሁንም እንደቀጠለ ነው ። በሰዓት 70 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ኃይለኛ ነፋስ እሳቱን እያባባሰ በመሆኑ ከ7500 በላይ የሆኑት የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት እልህ አስጨራሽ አድርጎባቸዋል።የአየር ንብረት ለውጥ ለችግሩ መባባስ አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑም እየተነገረ ሲሆን፣ የአካባቢው የአየር ንብረት መበከልም ሰወች ከቤት እንዳይወጡ አልያም ደረጃውን የጠበቀ ጭምብል እንዲለብሱ ማስጠንቀቅያ ተሰጥቷል። አካባቢውን የአደጋ ቦታ ብለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁት የካሊፎርኒያው አገረ ገዢ ጋቪን ኒውሰምበሰደድ እሳቱ የወደሙትን አካባቢወች በድጋሚ ለመገንባት ልክ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ አሜሪካ የመእራብ አውሮፓ ሃገራትን መልሶ ለማቋቋም የተገበረችውን ‘ማርሻል ፕላን' በመባል የሚታወቀውን አይነት ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።

አበበ ፈለቀ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW