የሰዎችን ችግር በማዳመጥ ማማከር ሌላው ህክምና
ማክሰኞ፣ ሰኔ 28 2014
ማኅበራዊ ችግሮች በበረከቱበት በዚህ ወቅት ሰዎች ለቁጣ ቅርብ እየሆነ መምጣታቸውን የዕለቱ የጤና እና አካባቢ ዝግጅታችን እንግዳ ይናገራሉ። ዘመኑ ያመጣው ቴክኒዎሎጂ ታክሎበት የወላጅ ልጅ ግንኙነት ወትሮ ከተለመደው ዛሬ በመለወጡም የቤተሰብ ትኩረት እና ፍቅር ያጡ ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው ለተለያዩ ሱሶች እና ልማዶች በመዳረጋቸው ሕይወትን በገዛ እጅ ወደማጥፋቱ እያዘነበሉም እንደሆነ እንዲሁ።
ወይዘሮ ወይንሸት አባተ ለ25 ዓመታት በበጎ ፈቃደኝነት በራሳቸው መንገድ ለ250 ሰዎች የምክር አገልግሎት እንደሰጡ ይናገራሉ። እሳቸው እንደገለጹልን በሰው በሰው እየሰሙ ምክር ከጠየቋቸው እና እሳቸውም ጊዜያቸውንም ገንዘባቸውንም አውለው ካማከሯቸው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከገቡበት የተለያዩ ችግሮች ወጥተው ወደ ተረጋጋ እና ጤናማ ሕይወት ለመመለስ በቅተዋል። ከልጅነታቸው ጀምሮ ሰዎችን ለመርዳት የነበራቸው ዝንባሌ ውሎ ሲያድር በግላቸው ወደ ማማከር አገልግሎት እንዳሳደጉት የገለጹልን ወይዘሮ ወይንሸት ምክር ፈላጊዎቹ እንዴት ባለ ችግር ውስጥ እንደሆኑ ሲናገሩ፤ «ራሳቸውን ለማጥፋት የፈለጉ፤ ያረገዙ ወጣት ሴቶች፣ በትዳር ሕይወት ችግር የገጠማቸው፣ ግብረሰዶማዊ ልምምድ ውስጥ የገቡ እንዲሁም በሀዘን ልባቸው የተሰበረ» ወገኖች እንዳሉበት ይዘረዝራሉ።
ወይዘሮ ወይንሸት ይኽን የማማከር አገልግሎት የሚሰጡት ያለምንም ክፍያ ነው። ለኑሯቸው የሚሆናቸው የግላቸውን ሥራ እየሠሩ ከቤተሰብም ሆነ ከሥራ የሚተርፋቸውን ጊዜ የሌሎችን ችግር ለማዳመጫ ያውሉታል። እናም ሰዎች የተጨነቁበትን እና የግል ምስጢራቸውን ጠጋ ብለው ይተነፍሱላቸዋል።
ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች የሚጋለጡት ያጡ የነጡ የማኅበረሰቡ ክፍሎች አይደሉም የሚሉት ወይዘሮ ወይንሸት የተሻለ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ወገኖችም የግሌ የሚሉትን ምስጢር የሚያማክሩት የሚሹበት አጋጣሚ በርካታ መሆኑን በ25 ዓመታት ውስጥ ከገጠመኛቸው ተረድተዋል። የስነልቡና ምክር አገልግሎት ሲታሰብ በስነልቡናም ሆነ በማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት የዘለቀ ዕውቀት መኖሩ የግድ እንደሚል ይታሰባል። ሆኖም ወይዘሮ ወይንሸት ለረዥም ጊዜያት በንባብ ባዳበሩት ግንዛቤ ላይ ተመርኩዘው ለብዙዎች የሕይወት እንቆቅልሽ መፍትሄ ማግኘት መቻላቸውን አጫውተውናል።
ወይዘሮ ወይንሸት ለረዥም ጊዜያት በበጎ ፈቃደኝነት በተለያዩ ምክንያቶች የተጨነቁ ሰዎችን አግኝነተው በሚያነጋግሩበት ጊዜ ያሉበትን ሁኔታ ካደመጡ በኋላ በሰዎቹ ላይ ለመፍረድ አልቸኩልም ነው የሚሉት። ይልቁንም ወደዚህ የገቡበትን መነሻ ምክንያት መረዳት ላይ ያተኩራሉ። እንዲያም ሆኖ ሰዎች ለዘመናት የቀበሩትን ምስጢር ልባቸውን ከፍተው ያለ ምክንያት አይናገሩምም ባይ ናቸው።
በዘመነ ቴክኒዎሎጂ ይላሉ ወይዘሮ ወይንሸት ልጆች ወላጆቻቸው ወደማያውቁት ጥልቅ ዓለም የመግባት ዕድሉ ተመቻችቶላቸዋል። ዓለምን ያስተሳሰረው መረብ ዕድሜያቸውን የማይመጥን መረጃ ስለሚያቀብላቸው ዛሬ ዘመናዊ ስልክ በእጁ ያለ በየትኛውም ዓለም የሚኖር ልጅ የሚጋራቸው በርካታ ነገሮችም እንዳሉ አጽንኦት ይሰጣሉ።
ለልጆች የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ከማቅረብ በተጨማሪ ዋነኛው የወላጅ ትኩረት እና አቀራረብ መሆኑን ያመለከቱት በጎ ፈቃደኛዋ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ የገንዘብ አቅም ይኽን ሊገድብ አይገባም ባይ ናቸው። አሁን ባለው የተወሳሰበ ችግር ምክንያት ማኅበረሰቡ ለቁጣ ቅርብ ሆኗል የሚሉት ወይዘሮ ወይንሸት እንዲህ ያለው የምክር አገልግሎት ቢስፋፋ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ። በምዕራቡ ዓለም የማማከር አገልግሎት ሰፊ ትኩረት የሚሰጠው የህክምና ዘርፍ ነው። ማኅበራዊ ችግሮች በበረከቱበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥም እንዲህ ያለው አገልግሎት በባለሙያዎች ቢስፋፋ የብዙዎችን ሕይወት አትርፎ ወደ ቀና መንገድ ለመምራት እንደሚያስችል ይታመናል። ለ25 ዓመታት በበጎ ፈቃደኝነት ወይዘሮ ወይንሸት ያበረከቱትም በቀላሉ አይታይም።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ