የሰዎች ደብዛ መጥፋትና የቤተሰብ ጭንቀት
ሰኞ፣ መጋቢት 16 2016የፌደሬሽን ምክር ቤት እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ሀብታሙ በላይነህ የተባሉ ሰው የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ. ም ከቤታቸው እንደውጡ እስካሁን ደብዛቸው መጥፋቱን ቤተሰቦቻቸው ለዶቼ ቬለ ገለፁ።አዲስ አበባ ውስጥ ለሚመለከተው የፀጥታ አካል በደብዳቤ እና በቃል ማመልከታቸውን የገለፁት ወንድማቸው "መረጃ የለንም" የሚል ምላሽ እንደሚሰጣቸው እና ወንድማቸው ሊታሰሩ የሚችሉበት የሚያውቁት ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለም ገልፀዋል።
በተመሳሳይ አርብ የካቲት 8 ቀን 2016ዓ.ም ከቤት እንደወጡ እስካሁን የት እንደገቡ ያልታወቁት ኢንጂነር አማኑኤል መንገሻ የተባሉ ሰው ባለቤት ባለቤታቸው የት እንዳሉ ማወቅ እንደተቸገሩ ገልፀው "እስካሁን መፍትሔ አላገኘንም" ብለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰዎች ከቤታቸው እንደወጡ ለሳምንታት ደብዛቸው ሲጠፋ፣ በኋላም በፀጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር መቆየቸው ሲገለጽ ፣ ከአዲስ አበባ ውጪም በታጣቂዎች ተይዘው ቤዛ ሲጠየቅባቸው ማየት ተደጋጋሚ ክስተት ሆኗል።
ተደጋጋሚው የሰዎች መጥፋት
እምጥ ይግቡ ስምጥ የማይታወቅ ደብዛቸው ለቀናት፣ ለሳምንታት ብሎም ለወራት የሚጠፋ ሰዎችን ዜና መስማት የተለመደ እየመሰለ ነው። ይህ ክስተት ባለፈው ወር ለሥራ ከቤታቸው የወጡ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል ላይ ጭምር መድረሱን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ወንድማቸው ነግረውናል። ለስብሰባ ብለው ወጥተው በዚያው የጠፉት አቶ ሀብታሙ ሊታሰሩ የሚችሉበት የሚያውቁት ምንም አይነት ምክንያት እንደሌለም ወንድማቸው ገልፀዋል።
በተመሳሳይ የካቲት 8 ቀን 2016ዓ.ም ከሚኖሩበት አዲስ አበባ የካ አባዶ ከቤት እንደወጡ ደብዛቸው የጠፋው ኢንጂነር አማኑኤል መንገሻ የተባሉ ሰው ከጠፉ ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ አጋፔ ግዮን ገልፀውልናል።
ይህንን በተመለከተ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪልን ጠይቀናቸዋል። በመሰል ክስተቶች ላይ ክትትል እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰዎች ከቤታቸው እንደወጡ ደብዛቸው ሲጠፋ፣ በኋላም በፀጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር መቆየቸው ሲገለጽ ፣ ከአዲስ አበባ ውጪም በታጣቂዎች ተይዘው ቤዛ ሲጠየቅባቸው ማየት ተደጋጋሚ ክስተት ሆኗል። ይህ በተለይ በፖለቲከኞች፣ በያገባናል ባዮች እና ጋዜጠኞች ላይ ተደጋግሟል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ