የሱዳኑን ውጊያ መሪ ጀነራሎች ደጋፊዎች ማን ናቸው?
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 28 2015
ከአፍሪቃ ሦስተኛዋን ትልቅ ሀገር ሱዳንን ለመቆጣጠር ፤የሱዳን ጦር ሠራዊት መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሀንና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ ሞሀመድ ሀማዳን ዳጋሎ በሌላ ስማቸው ሄመድቲ የሚያካሂዱት ውጊያ ተባብሶ ቀጥሏል ። ከአራት ዓመት በፊት በጎርጎሮሳዊው 2019 ለረዥም ዓመታት ሱዳንን የመሩትን ኦማር አልበሽርን ለመጣል ያበሩት ጀነራል አል ቡርሀንና ጀነራል ዳጋሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት በቅተው ነበር። በምዕራባውያን እይታ ያኔ ሱዳን እርምጃውያልተረጋገጠ የዴሞክራሲ ጎዳናን ተያያዘች ተብሎ ነበር። ሆኖም ቡርሀን ከአንድ ዓመት በፊት በጎርጎሮሳዊው 2021 የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤትን ሲበተኑ ተስፋው እንደ ጉም በነነ። ግጭቱ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአካባቢው ሀገራት ሚና ማነጋገሩ አልቀረም። የቀድሞ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የአሁኑ ጦርነት በሱዳን ጦር ሠራዊትና በአናሳ አማጽያን መካከል ብቻ የሚካሄድ አይደለም፤ይልቁንም በደንብ በሰለጠኑና በታጠቁ ሁለት ጦር ሠራዊቶች መካከል የሚካሄድ እንጂ ብለዋል የሄመደቲ ታማኝ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ወደ 100 ሺህ እንደሚጠጋ ይገመታል፤ ፈጥኖ ደራሹ በመላ ሱዳን ጦር ሰፈሮች አሉት።
የፈጥኖ ደራሹ ኃይል በእንግሊዘኛው ምህጻር RSF አጋሮች ማንነት ብዙም ግልጽ አይደለም። ሆኖም ሳዑዲ አረብያ፣የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ሊቢያ የሚገኙት የፊልድ ማርሻል ሃሊፋ ሀፍታር ኃይሎች እና ዋግነር የሚባለው የሩስያ የግል ወታደራዊ ኩባንያ የRSF አጋር ናቸው ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ሌላ RSF ከየመን ጋር ጥሩ ግንኙነት አለው ይባላል። ሄመድቲ ከሳዑዲ አረብያና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በመተባበር የመን የሚገኙ በኢራን የሚደገፉ ሁቲዎችን ለመውጋት በሺህዎች የሚቆጠሩ የRSF ቅጥር ተዋጊዎችን ልከው ነበር።RSF ከሱዳን ጦር ሠራዊት ጋር ሲነጻጸር የአየር ኃይል የለውም ።ይሁንና የቡድኑ ሚሊሽያዎች ፈጣን ተንቀሳቃሾች መሆናቸው ይነገራል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችም አሏቸው ።ከመካከላቸው ቶዮታ ላንድ ክሩዘር እና ሃይሉክስ አራት በአራት ማሽን ጋን፣ፀረ ታንክ መሣሪዎች፣ ጫኝ መኪናዎች፣ ሮኬት አስወንጫፊዎች እና አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች ይጠቀሳሉ። በርቀት በሚገኙ የበረሃ አካባቢዎች ላይ ቁጥጥር ለማድረግና ለከተማ ውጊያም በደንብ የተዘጋጀ ነው የሚባለው ቡድኑ የሱዳንን ጦር ኃይል መድፎች በአስተማማኝ ሁኔታ ለማውደምና የአየር የበላይነትን የመያዝ አቅም እንዳለው ነው የዶቼቬለው የካይ ኔበ ዘገባ የሚያስረዳው ። Global Witness investigation የተባለ ድርጅት እንደሚለው ቴክኒካዊ መሣሪያዎቹ የተገኙት ከዱባይ ነው። የብሪታንያው የቻተም ሀውስ የምርምርና ጥናት ተቋም ባልደረባ አህመድ ሶሊማን እንዳሉት ሀመድቲ ቻድ ውስጥ አጋሮች አሏቸው ። ዳርፉር የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ማዕከል ናት። ሀመድደቲ የቻድ ዘር ያላቸው የሬዚጋት ጎሳ አባል ናቸው። በጎተንበርግ ስዊድን School of Global Studies ስኩል ኦፍ ግሎባል ስተዲስ ተመራማሪና የሱዳን ጉዳዮች አዋቂ አሊ ቬርጄ በላላው የሱዳንና ቻድ ድንበር ላይ የሚገኘውን የሪዚጋት ማኅበረሰብን ኃይል ዝቅ አድርጎ መመልከት አይገባም ይላሉ።
«ሪዚጋቶች በሙሉ በአንድ ዓይነት መንገድ ነው የሚያስቡት ማለት ይቀላል። በአንዳንድ ዘገባዎች ላይ ሰዎች ይህ ሰው ከዚህ ቡድን ነው ሲሉ ይሰማሉ፤ስለዚህ ይደግፉታል። እንዲህ ቀላል ቀይደለም ።ሌሎች ንዑሳን ክፍፍሎችም አሉ። እንደሚመስለኝ ግን ሀምደቲ ከሌሎች በተለየ ቅርንጫፎችን በመዘርጋትና ኃይሎቹን ከመላ ሱዳን በመልመል ተዋጥቶለታል።»
ቬርጄ እንደሚሉት RSF ዳርፉር ውስጥ ለአሥር ዓመታት ይንቀሳቀስ ከነበረው ከጃንጃዊድ ሚሊሽያ የተገኘ ቡድን ነው። የአሁኖቹ ተዋጊዎች ወጣቶችና ምንጫቸውም የተለያየ ነው።በሱዳን ድንበር ላይ በተፈጠሩት አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ሰበብ ሁኔታዎች ተወሳስበዋል። ባለፉት አሥርት ዓመታት ብቻ ደቡብ ሱዳን፣ ሊቢያ ፣ቻድና ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች ተካሂደዋል።ኢትዮጵያና ሱዳን በአዋሳኛኛቸው የአልፋሻጋ ወረዳ ይወዛገባሉ።የአፍሪቃ ቀንድ ዓለም አቀፍ ስልታዊ ጥናት ተቋም ሃላፊ ሀሰን ካኔንጄ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የመዋጋት ሀሳብ የላትም ይላሉ ።ሆኖም ግን ቀውሱ ከቀጠለ ሊሆን የሚችለው አይታወቅም ባይ ናቸው።
«ኢትዮጵያ በርግጥም ከሱዳን ጋር ሌላ ጦርነት ውስጥ መግባት አትፈልግም። ቀውሱ ከቀጠለ ግን ወደፊት ሊካሄድ በሚችል ድርድር ላይ ጥቅምዋን ለማስጠበቅ ሊረዳት ይችላል። ከዚያ በኋላ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ይቃጣት ይሆናል። በአሁኑ ደረጃ ግን ይደግፋሉ ማለት አንችልም።»
በአሁኑ ደረጃ ከዚያ ይልቅ ኢትዮጵያ ከሲቪል አስተዳደሩ ጋር የመስራት ፍላጎት ይኖራታል ብለዋል ካናንጄ።በሌላ በኩል ተጠባባቂውን ኃይል ሳይጨምር 120ሺህ እንደሚደርስ የሚገመተው መደበኛው የሱዳንጦር ሠራዊት ከግብጽ ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው።ሆኖም የቡርሀን ኃይሎችን የምትደግፈው ግብጽ የRSF ደጋፊዋ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ብዙ መዋዕለ ንዋይ የምታፈስባት ሀገር ናት። ይሁንና ቬርጂ የሱዳንን ጉዳይ በሚመለከት ከውጭ የሚባለውን ሳይሆን የሀገር ውስጡን ድምጽ ማዳመጡ ይመረጣል ሲሉ ይመክራሉ።
«ውስጣዊው ስሌት በውጭ ከሚባለው ይልቅ በጣም ጠቃሚ ነው።
ካኔንጄ የሱዳን ጦር ኃይልና የRSF አጋሮች ሁለቱ ወገኖች ወደ ሰላም ንግግር እንዲመጡ ያግባባሉ ብለው ያምናሉ ። በርሳቸው አባባል ሆኖም በሚቀጥሉት አንድ ሁለት ወይም ሦስት ሳምንታት ውይይት ካልተካሄደ ግን የውጭ አጋሮች ገንዘብና የጦር መሳሪያዎች ወደ ሱዳን መላካቸው አልቀረም።
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር