1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሱዳኑ ዐብደላ ሐምዶክ የኅዳሴ ግድብን ሊጎበኙ ይችላሉ-ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 19 2012

የሱዳኑ መሪ በሚቀጥለው ወር ወደ ኢትዮጵያ ሲያመሩ የኅዳሴ ግድብን ሊጎበኙ እንደሚችሉ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቆማ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይና ጠቅላይ ምኒስትር ሐምዶክ ካደረጉት ውይይት በኋላ "በሶስትዮሽ ድርድሩ ስኬታማ ማጠቃለያ ላይ ለመድረስ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ሁለቱ ወገኖች አጽንዖት ሰጥተዋል" የሚል መግለጫ አውጥተዋል

Äthiopien Grand Renaissance Damm
ምስል፦ picture-alliance/AP Photo/Maxar Technologies

የሱዳን ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ በመጪው ወር  ወደ ኢትዮጵያ ሲያመሩ ታላቁ የኅዳሴ ግድብን ሊጎበኙ እንደሚችሉ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ የሱዳኑ አቻቸው በሚቀጥለው ወር ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ያረጋገጡት በኻርቱም ባደረጉት የአንድ ቀን የሥራ ጉብኝት ከጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ዐቢይ "በሚቀጥለው ወር ጠቅላይ ምኒስትር ሐምዶክ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የጋራ ፕሮጀክታችን የታላቁ የኅዳሴ ግድብን እንጎበኝ ይሆናል" ብለዋል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ ዐቢይ ይፋ ስላደረጉት የአዲስ አበባ እና በምን አልባት የተጠቀሰው የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉብኝት ያሉት ነገር የለም።

"ታሪካዊ" ያሉትን የኢትዮጵያ እና የሱዳን ግንኙነት ያወደሱት ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክ "በጋራ ልንሰራ የምንችለው ነገር ለቀጣናው ውሕደት እንደ ባቡር ሞተር ሊያገለግል ይችላል" ሲሉ ተደምጠዋል።

"በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ምኒስትር ሐምዶክ እና ከምኒስትሮቻቸው ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጊያለሁ" ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ከአጀንዳዎቹ መካከል እንደሚገኝበት ገልጸዋል። ጠቅላይ ምኒስትር ዐብደላ ሐምዶክም ለኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ "ትልቅ ተስፋ" ባሉት እና እስካሁን 120 ቢሊዮን ብር በወጣበት የጉባው ግድብ ላይ ውይይት መደረጉን አረጋግጠዋል።   

ጠቅላይ ምኒስትሮቹን ጨምሮ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ካደረጉት ውይይት በኋላ ያወጡት የጋራ መግለጫ "በሶስትዮሽ ድርድሩ ስኬታማ ማጠቃለያ ላይ ለመድረስ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ሁለቱ ወገኖች አጽንዖት ሰጥተዋል" ብሏል።

የአፍሪካ ኅብረትን የአሸማጋይነት ሚና ያደነቀው ይኸው የኢትዮጵያ እና የሱዳን የጋራ መግለጫ እንደሚለው በሶስቱ አገሮች መካከል የሚደረገው ድርድር ግድቡን የቀጠናው የውሕደት መሳሪያ ወደሚያደርግ ቀመር ሊመራ ይገባል።  

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ እንዳሉት ከግድቡ በተጨማሪ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች የመነጋገሪያ ርዕሶች ነበሩ። "በቀጣናው ሰላም እና ጸጥታ ላይ ተወያይተናል። ከዚህ ጉብኝት ሁለቱ የለውጥ መንግሥታት ለቀጣናችን ብርሀን እንደሚፈነጥቁ ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።

ከጠቅላይ ምኒስትሩ ጋር ወደ ኻርቱም ካቀኑት መካከል የመከላከያ ምኒስትሩ ቀንዓ ያደታ፣ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው እና የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ምኒስትር ስለሺ በቀለ ይገኙበታል።

ጉብኝታቸው የቀድሞው የሱዳን መሪ ከሥልጣን ወርደው የሽግግር መንግሥት የተመሠረትበትን አንደኛ አመት በማስመልከት የተደረገ ነው። ዐቢይ በኻርቱም ጉብኝታቸው ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታሕ አል ቡርሐን ጭምር ተገናኝተዋል።

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW