የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በኤልፋሺር ይፈጽማል የሚባለው ግፍ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 6 2018
የሱዳንን መንግሥት የሚወጋው ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በምህጻሩ RSF ምዕራብ ሱዳን የሚገኘውን የኤልፋሺር ከተማን ከተቆጣጠረ ከሁለት ሳምንት በላይ ሆኗል። ከዚያን ወዲህ በከተማይቱ የጅምላ ግድያ፣ ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ እገታ እና ወሲባዊ ጥቃት መባባሳቸው እየተዘገበ ነው። በዶቼቬለው ኬርስተን ክኒፕ ዘገባ መሠረት ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን የዓይን ምስክሮች ለመገናኛ ብዙሀን እየተናገሩ ነው።
RSF የሱዳንን ጦር መውጋት ከጀመረ ሦስት ዓመት አልፏል። ግጭቱ የተቀሰቀሰውም የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ዋና አዣዥ ሞሀመድ ሀምዳን ዳግሎ ወይም በአጭሩ መጠሪያቸው ሄሜቲ የሚመሩት ኃይል ከሱዳን ጦር ጋር እንዲቀላቀል ለቀረበላቸው ጥያቄ እምቢተኛ መሆናቸው ነው። RSF ፣ በጎርጎሮሳዊው 2019 ዓ.ም. ፣በቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር፣ ከተቋቋመው ጃንጃዊድ ከተባለው ቡድን ነው የወጣው። ጃንጃዊድ በጎርጎሮሳዊው 2000 ዓ.ም. አካባቢ በተካሄደው የዳርፉር ግጭት በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በመፈጸም ተጠያቂ የሚባል ቡድን ነው።
ሀገር አሊ በጀርመኑ ዓለም አቀፋዊና እና አካባቢያዊ ጥናቶች ተቋም የሱዳን ጉዳዮች አዋቂ ናቸው። ሀገር አሊ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ህዝቡ አሁን በአልፋሺር የሚካሄደውን ጭፍጨፋ ሲያይ የመጀመሪያው አይደለም። ኖም አሁን ከበፊቱ በጣም ተባብሷል። « የጭካኔው መጠን በጣም አስደንጋጭ ወደሆነ አዲስ ደረጃ ላይ ደርሷል። የRSF ጥቃትና ጭካኔ ወደዚህ ደረጃ አድጓል። በመሠረቱ የRSF ዓመፅና ጭካኔ እስከዚህ ደረጃ ድረስ በመስፋፋቱ በበቂ ሁኔታ በጋለ ስሜት የማይደግፋቸው፣ ከእነሱ ጋር መቀላቀል የማይፈልግ ወይም ማንኛውንም ተዋጊ የሚያደናቅፍ ማንኛውም ሰው አደጋ ላይ ይወድቃል። ጥቃት ለማስጀመር ትዕዛዝ ወይም የዕዝ ሰንሰለት አያስፈልግም።»
ከአልፋሺር የሸሹት ሰዎች ቁጥር 90ሺ ይደርሳል
የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ምክትል ከፍተኛ ኮሚሽነር ኬሊ ክሌሜንትስ በቅርብ ቀናት ከአልፋሺር የሸሹት ሰዎች 90ሺ እንደሚደርስ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። እነዚህ ሰዎችም እርሳቸው እንዳሉት አንድም ነገር ሳይዙ ነው ከቀያቸው ሸሽተው ሌላ አካባቢ የሄዱት። « ብዙዎች ታዊላ ወደሚባል ከተማ ወይም መንደር (አሁን ትንሽ ከተማ ሆናለች) ነው የመጡት። ከተማይቱ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለሟሟላት የሚሞክሩ በርካታ ተፈናቃዮች ይገኙባታል። ሰዎች ምንም ሳይዙ ነው ወደታዊላ የሚመጡት ። ከባድ ስነ ልቦናዊ ጉዳት ደርሶባቸው፤ ቆስለውም ይመጣሉ። እጅግ አንገብጋቢ የሆነውን ምግብን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰብዓዊ ፍላጎቶችም አሏቸው። ወደ ቻድ የሚመጡት ሴቶችና ህጻናት ናቸው። ወደ 87 በመቶ ይሆናሉ ከአማካዩ በላይ ነው። አብዛኛዎቹ ሴቶችና ልጃገረዶች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል ወይም የወሲብ ጥቃት ደርሶባቸዋል።»
ሀገር አሊ እንደሚሉት ደግሞ ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ድሎቹን ከእውነታው እጅግ አጋኖ የማሳየት አዝማሚያ አለው አሁን ደግሞዳርፉርንበስፋት የመቆጣጠር ፍላጎት እንዳላቸው ለጦሩ መልዕክት እያስተላለፉ ነው። ከዚህም በላይ እንደ ሀገር አሊ በጦርነቱ የሱዳን የተፈጥሮ ሀብቶችም አደጋ ላይ ናቸው። ይህም ወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕደናትን ያካትታል። በአሊ አባባል የሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብቶች ወርቅና እጣን አደጋ ላይ ናቸው። RSF እነዚህን ሀብቶች በሀገሪቱ ድንበሮች በኩል አሻግሮ የመሸጥ ሙከራ ላይ መሆኑን የሚጠቁሙ ዘገባዎች ቁጥር ጨምሯል። ይህ ደግሞ RSF አሁን ሊያቋቁም ለሚሞክረው የራሱ መንግሥት ገንዘብ የሚያገኝበት መንገድ ነው ።
የጅምላ እስርና ጭፍጨፋ ይጠረጠራል
በአሁኑ ጊዜ በአልፋሺርም ሆነ በአካባቢው የጅምላ እስር እና ግድያ መድረሱን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች በብዛት እየወጡ ነው። የየል የኅብረተሰብ ጤና ትምሕርት ቤት፣ የሰብዓዊነት ምርምር ላቦራቶሪ በአንዳንድ አካባቢዎች አስከሬኖች የሚመስሉ ቁሶችን ለይቶ ማወቁን በቅርቡ ዘግቧል። እነዚህ ምልከታዎችም ከተማይቱን ለቀው ለመውጣት የሚሞከሩ ሰዎች ላይ ርሸናና ግድያዎችን እረጋግጠዋል።
የመረጃ ማቋቋሚያ ማዕከል በምህጻሩ CIR የተባለው ድርጅትም ከአል ፋሺር ሰሜን ምዕራብ አካባቢ የጅምላ እስሮችንና ግድያዎችን የሚያሳዩ የተረጋገጡ ምስሎችን አቅርቧል። ይህ የደረሰው በሰላማዊ ሰዎች በሚዘወተረው ከአል ፋሺር ፣ጉርኔ ወደተባለው ቦታ በሚወስደው መስመር ላይ ነው።
የህዝብ ቁጥርን ለመቀነስ ይወሰዳል የሚባል የዘር ማጥፋት ክስ
የሱዳንን ጦርነት የሚከታተለው ዋር ሞኒተር የተባለው ድርጅት በመስከረም አጋማሽ ላይ በዳርፉር ግጭቱ መባባሱን አስጠንቅቆ ነበር። በወቅቱ ዳርፉር በሚገኘው በአልሳፋያ መስጊድ ላይ ያነጣጠረ የድሮን ጥቃት የአርብ ጸሎት በሚካሄድበት ወቅት መፈጸሙን ዘግቦ ነበር። በዘገባው በሳፊያ የደረሰው ግድያ የRSF ዘመቻ ዓላማ ወታደራዊ ድል ብቻ ሳይሆን የህዝብ ቁጥር ለማሳነስ የሚካሄድ (ዘር )ማጥፋትም ነው ብሎም ዘግቧል። ስልታዊ ማስራብም እንዲሁ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።
አስቸጋሪ የሰላም ጥረቶች
በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ከሱዳን ጦር አዛዥ ጀነራል አብዱልፈታህ ቡርሀን ጋር ፖርት ሱዳን ውስጥ የተነጋገሩት የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ባለፈው መስከረም አራት መንግሥታት ማለትም ዩናይትድ ስቴትስ ፣ግብጽ ፣ሳዑዲ አረብያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ያቀረቡትን የሰላም እቅድ ዳግም ለቡርሀን አቅርበውላቸዋል። እቅዱ የሦስት ወራት ሰብዓዊ የተኩስ አቁምና ከዚያም የ9 ወራት ፖለቲካዊ ሂደት እንዲከተል የሚጠይቅ ነው።
RSF ባለፈው ሳምንት በሰብዓዊ የተኩስ አቁሙ እስማማለሁ ብሏል። ጦሩ ደግሞ የቀረበውን ሃሳብ መልካም ብሎ የሚቀበለው ግን RSF ሲቭሎች ከሚኖሩበት አካባቢ ለቆ ሲወጣና ትጥቁንም ሲፈታ ብቻ ነው ሲል መልሷል። ከዚህ በመነሳት የጊጋው ሀገር አሊ በሱዳን ሰላም ለማውረድ የሚካሄደው ዓለም አቀፉ ጥረት ጦርነቱን ማስቆሙም መቻል አለመቻሉ ያጠራጥራል ይላሉ።
«እንዳለመታደል ሆኖ ለህዝቡ አስቸኳይ ጥበቃ ሊያደርግ የሚያስችለ ወታደራዊ የመከላከያ እርምጃ ብቻ ነው። ለምሳሌ ሰላማዊ ሰዎችን ለማስወጣት ከጦርነት ነፃ አካባቢዎች ፣የታጠቁ አጃቢዊች ፣ማዕቀቦችና ክልከላዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው። ሆኖም እነዚህን ተግባራዊ ሆነው ውጤት እስኪያመጡ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። »
በአሊ አስተያየት ጊዜው እየረዘመ በሄደ ቁጥር ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል የጦር መሣሪያ አቅርቦት መስመሮች እየበዙ ሄደዋል። አሁን ባለበት ደረጃም በቀላሉ በማዕቀቦች ሊወገድ የማይችልበት ደረጃ ላይ አይደለም።
ኬርስተን ክኒፕ /ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ