የሱዳናውያን የጅዳው የሰላም ንግግር እና ደብዛዛው ተስፋ
ሰኞ፣ ግንቦት 7 2015
ልዕለ ኃያሏ ዩናይትድስቴትስ እና ሌላኛዋ የቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪ ሳዑዲ አረቢያ ገፋፍተው የጠሩት የሰላም ንግግር የሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ተወካዮች ጂዳ ውስጥ ፊት ለፊት ካስቀመጠ እነሆ ሳምንት ተሻገረ። ከሁለቱም ወገን ከአንዳች የተኩስ አቁም ስምምነት የመድረስ ፍላጎት በእርግጥ እስካሁን አለመታየቱ የሱዳናውያንን ሰቆቃ ከሳምንታት ወደ ወራት ያሻግር ይሆን ተብሎም አስግቷል። ተፋላሚዎቹ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ወታደራዊ ኃይሎቻቸውን ከሲቪላውያን መኖሪያ አካባቢ ማራቅን ጨምሮ ለሰብአዊ እርዳታ መተላለፊያ ለመክፈት ከሰሞኑ መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል። ነገር ግን አራት ሳምንታት ያስቆጠረው የሱዳን እና ሱዳናውያን ቀውስ ተባብሶ ቀጥሏል። ጤና ይስጥልን አድማጮች ከመነጋገር ይልቅ ጉዳያቸውን በኃይል ለመጨረስ የጀመሩ ለሚመሰለው የሁለቱ ሱዳናውያን ወታደራዊ ኃይላት ግጭት ዕልባት ጂዳ መልስ ይኖራት ይሆን? ይህ ማህደረ ዜና ነው ።
ቀን ቀንን እየተካ ፣ሳምንታት ብሎም ከወር ተሻገረ። አንዳች ተስፋ የማይታይበት ፤ ይልቁኑ መሽቶ ሲነጋ የሟቾች ቁጥር የሚጨምርበት፣ ሺዎች ከማለት ባለፈ ምን ያህል ሰው እንደተጎዳ እንኳ በእርግጥ መናገር አስቸጋሪ ሆኗል ። ነብሱን ለማትረፍ ሀገር ትቶ ከሸሸው ጋር ተዳምሮ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለው ሰው ቁጥር አንድ ሚሊዮን ሊደርስ ነው። ስረዓተ አልበኝነት የፈጠረው ዝርፍያ እና ንጥቂያው ሲጨመርበት ደግሞ በእርግጥ የዚያች ሀገር ነገር ከሆነው ይልቅ ሊሆን ያለው ያስፈራል።
በሁለቱ ጄነራሎች የሚመሩት የወታደራዊ ኃይሎች ተወካዮች በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ንግግር ከጀመሩ ሳምንት አስቆጠሩ ። ሀገር ቤት ግን ሰላም የለም። የዳርፉሯን ጄኔይናን ጨምሮ መንትዮቹ ከተሞች ካርቱም እና ኦምዱርማን ግጭቶች አይለው የተስተዋሉባቸው ከተሞች ናቸው። በአንድ በኩል ሄሜቲ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የሲቪላውያንን የመኖሪያ አካባቢዎች በመውረር ሲከሰሱ፤ የአልቡርሃኑ ብሔራዊ ጦር ደግሞ እነዚህኑ የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ አካባቢዎች የአየር ጥቃትን ጨምሮ በከባድ መሳሪያ መደብደባቸው እየተነገረ ነው። ሁለቱ ኃያሎች ትናንት እሁድ ጅዳ ውስጥ የተኩስ አቁም ለማድረግ ንግግር መጀመራቸው ተገልጿል። ንግግር የመጀመራቸው ነገር ተስፋ ይኖረው ይሆን ወይስ ልክ አ,ስቀድመው እንዳደረጉት የፈረሙበት ቀለም ሳይደርቅ ውግያቸውን ይቀጥሉ ይሆን እንጠይቃለን። ተፋላሚዎቹ ጦርነት ከጀመሩበት ዕለት አንስቶ የተኩስ አቁም ለማድረግ በርካታ ጊዜያት ተስማምተው የስምምነታቸው ገቢራዊነት የውሃ ሽታ መቅረት እና ውግያው መቀጠሉን ለተመለከተ አሁንስ እንዴት ተስፋ ያሳድርቡን ይሆን ብሎ መጠየቁም ተገቢ ሳይሆን አይቀርም ። ነገር ግን በአንድ በኩል ዋነኞቹ አጋሮች ዩናይትድስቴትስ እና ሳዑዲ አረቢያ ምናልባት ጫናቸው አይሎ ገቢራዊ ሊደረግ ወደ ሚችል አንዳች የስምምነት ማዕቀፍ ተገፍተው ይመጡ ይሆን ፤ ይህም ላይሆን የሚችልበት ዕድሉ አይኖርም ። የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት መረጋገጥ ብሎም የተኩስ አቁም ተደርጎ ወደ ዘላቂ የሰላም መፍትሄ እንዲመጣ የሚጠበቀው የሱዳናውያኑ የሰላም ንግግር ተስፋ እና ስጋት ይዞ ቀጥሏል።
ነዋሪነታቸውን በቤልጅየም ያደረጉት ፕሮፌሰር መሀመድ ሀሰን ጸሀፊ ፣መምህር እና የታሪክ ተመራማሪ ናቸው። የምስራቅ አፍሪቃ ቀጣናዊ ጉዳዮችን ደግሞ በቅርበት ይከታተላሉ ። የሱዳናውያኑን ወታደራዊ ኃይሎች ግጭት በቶሎ መፍትሄ እንደሚያገኝ ተስፋ እንዳላቸው ይናገራሉ ። ምክንያት የሚሉት ደግሞ የወታደሮቹ ግጭት ለእርሳቸው ታሪክ ወይም ትርክት ወለድ ሳይሆን የወደፊት ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ በመሆኑ ነው ባይ ናቸው ።
«ዕድሉ አለ። ምክንያቱም እነሱ በታሪካቸው ላይ ግጭት የላቸውም ። ንባባቸው በሱዳን ታሪክ ላይ ግጭት የላቸውም። በዚያ ላይ ትርክት የላቸውም። ያላቸው ግጭት እንደሁ በአራዳቋንቋ ልግለጸውና ከሚጣፍጠው ባቅላባ ላይ አብረን እንካፈል ከሚል የመነጨ ነው።»
የሱዳናውያኑ ኃይላት ወደ ስምምነት የመምጣት አንድምታው ከሱዳን ባሻገር ነው። ለወትሮም ቢሆን የርስ በእርስ ግጭት እና ጦርነት ለማያጣው ቀጣናው ሌላ የራስ ምታት እንዳይሆንም ያሰጋል። የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ሸሽተው ሱዳን የተጠለሉትን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን በእዚያ ይመራሉ ። የሌሎች ሀገራት ዜጎችም እንዲሁ ቀላል ቁጥር የሚሰጠው አይደለም ። ከዚህ በላይ ግን ሱዳናውያኑን ኃይላት ወደ ስምምነት ሊያመጣቸው የሚችል አቅም አላቸው የሚሉት ፕሮፌሰር መሐመድ ሲቪሉን ያካተተ አስተዳደር ለማቋቋም እና መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከመግባባት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።
«የሱዳን ችግር ሊፈታ ይችላል ። ሊፈታ የሚችለው ግን ከሁለቱም ወገን በዝቅተኛ መረዳት መምጣት ከቻሉ እና በአዲስ መዋቅር ሲቪሉንም ጨምሮ አ,ዲስ ሱዳን ለመገንባት ያላቸውን ችሎታ ሲጠቀሙ ነው።»
በሳዑዲ አረቢያ ጂዳም ሆነ ከሀገር ቤት የሚታየው እና የሚሰማው ግን በእርግጥ የደበዘዘ ተስፋ ነው። በጅዳ የሰላም ንግግሩን በቅርበት የሚከታተሉ አንድ የአሜሪካ ዲፕሎማት ሁለቱ ኃይላት ለመስማማት ከሚያስችል መቀራረብ ላይ አለመድረሳቸውን ይልቁንም የተራራቀ አቋም መያዛቸውን ገልጸዋል።
የሱዳኑ ወታደራዊ ግጭት በቀላሉ ሊቆም እንደማይችል በስጋት ከሚመለከቱት አንዱ በአሜሪካ አዮና ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ደረሰ ጌታቸው ናቸው። እንደ ዶ/ር ደረሰ የሱዳን ግጭት በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጠናቀቅ አዝማሚያ እንደሌለው ነው።
« የምጠብቀው እኔ ከማየው ነገር ምንድነው ፤ ምናልባት ወደ ተራዘመ እና የሶማልያን አይነት ማዕከላዊ መንግስቱ የተዳከመ በጦር አበጋዞች እና በክልል ጉልበተኞች ኃይል መጠናከር ሱዳን ወደ ሀገር መፍረስ አደጋ ልታዘቀዝቅ ትችላለች»
ሱዳን ከወታደራዊ ኃያላቱ ግጭት አስቀድሞ በሌሎች መልከ ብዙ ግጭቶች ውስጥ አልፋለች ። ግጭቶቹ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ አሁንም ድረስ አሉ። ለግጭቶቹ መንስኤ የሆኑ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጥያቄዎች አሁንም ድረስ መልስ አላገኙም ። አሁን በሀገሪቱ ውስጥ ተገዳዳሪ በሌላቸው ሁለቱ ኃያላን ወታደራዊ ኃያሎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ከቀደሙት መሰረታዊ ምክንያቲች ጋር ሲዳመሩ ሱዳን ለተራዘመ ጦርነት የመጋለጥ ዕድል እንዳላት ዶ/ር ደረሰ ይናገራሉ።
« ሀገሩ በጣም ትልቅ ነው። ደቡብ ሱዳን ሳይወጣ በፊት ሱዳን በአፍሪቃ ውስጥ በቆዳ ስፋቷትልቅ ሀገር ነበረች። እና ያ ትልቅነት ያመጣው ነገር በምዕራቡ የተለያዩ የመገንጠል ጥያቄ የሚያራምዱ የ,ዳርፉር አማጽያን አሉ። ጦርነትም እየተደረገ ነው። በምስራቁም እንዲሁ የመገንጠል ጥያቄ ፣ የፖለቲካ ዕኩልነት ጥያቄ የሚያነሱ ብሄረሰቦች አሉ።የብሄረሰብ እና የጎሳ ፖለቲካ ዳራው ሱዳን ከገባችበት ምስቅልቅ ውስጥ በቀላሉ የመውጣት አቅም አላት ብዬ አላስብም »
የጂዳው የሰላም ንግግር ለሱዳን እና ሱዳናውያን መጻኢ ዕጣ ፈንታ ወሳኞች ናቸው። ሱዳን እንደ ሀገር ለመቀጠል ጭምር መጻኢ ጊዜዋ የሚወሰነው በእነዚሁ ኃያሎች ከስምምነት መድረስ ነው። ችግሩ ያ ሳይሆን ቢቀርስ ነው፤ እንጠይቅ ፤ የታርክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር መሐመድ ሀሰን እንደሚሉት ያ ሳይሆን ቢቀር መጭው የሱዳን ጊዜ በጦር አበጋዞች እጅ መውደቅ ነው ይላሉ ። እንደእርሳቸው ምንም እንኳ ሀገር እንደ ሀገር የመከፋፈል አደጋ ባያጋጥማትም ።
« የምለው እዚያ ደረጃ የማይደርሱ ከሆነ ሱዳን ተበተነች ማለት ነው። ሱዳን በጦር አበጋዞች ልትገዛ ነው ማለት ነው። ምክንያቱም ማዕከላዊ መንግስቱ ካርቱም ላይ ያለው ሁሉንም ሲቆጣጠር የነበረው ማዕከላዊ መንግስት ሆኖ መቆጣጠር ካልቻለ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው»
»የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲቋጭ ዩናይድስቴትስን ጨምሮ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጫና ከፍተኛ እንደነበር ይታወሳል። ኢትዮጵያውያኑ ተፋላሚዎች ከስምምነት ለመድረስ እጅግ አዳጋች ነበሩ የተባሉ የስምምነት ማዕቀፎችን ጭምር ተቀብለው ወደ ተግባራዊነቱ ለመግባታቸውም ይኸው ዓለማቀፍ ጫና በዋነኛነት ይጠቀሳል። በሱዳን ያለው የሃይል አሰላለፍ እና ልዕለኃያሏን ሀገር አሜሪካንን ጨምሮ የሌሎች ኃያላን ሃገራት ከሱዳን አንጻር ያላቸው አሰላለፍ እና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚያራምዱት አቋም ሱዳናውያኑ ላይ ጫና ፈጥረው ወደ ሰላም እንዲመለሱ አያስችላቸውም ይላሉ ዶ/ር ደረሰ፤
«የግብጽ መንግስት በሱዳን ህዝብ ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው። እና ግብጽን እንደ በጥባጭ እንጂ እንደ መፍትሄ አምጪ የሚያይ ኃይል የለም። የባህረሰላጤው ሀገ,ራት ደግሞ ሄሜቲን ይደ,ግፋሉ። ምዕራባውያን ደግሞ ምን እንደሚፈልጉ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። »
ይህ በእርግጥ ጥሩ ዜና አይደለም ። ሱዳናውያኑ ወደ ሰላም እንዲመለሱ በተስፋ መጠበቁ እንዳለ ሆኖ ፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ እና አሁንም ድረስ በራሳቸው ካሉበት የውስጥ ችግር ያልተላቀቁ ፤ አሁንም በግጭት ውስጥ ባሉ የሱዳን አጎራባቾች ራሳቸውን የማዘጋጀት ተገቢነትን ምሁራኑ ይመክራሉ። ሱዳን ውስጥ ግጭትም ሆነ ጦርነት በተራዘመ ቁጥር በተለይ እንደኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ከማሸጋገር አንጻር አሳሳቢ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር መሐመድ።
«የሚያሳድረው አንደኛው ተጽዕኖ ብዜ መሳሪያ ሱዳን ውስጥ አለ፤ እና በተለይ ትናንሽ መሳሪያዎች ምናምን በ,ቀላሉ ተገዝተው ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ይችላሉ። ኢትዮፕያ ውስጥ ጠብ እፈልጋለሁ የሚlle ኃይል ካለ ወርቃማ እድል ይሆንለታል ማለት ነው።»
ዶ/ር ደረሰ ደግሞ የችግሩን አሳሳቢነት በቀጣናው ሃገራት ከሚያስከትለው የስደተኞች ቀውስ ጋር አስተሳስረው ይመለከታሉ።
« በየሀገሩ ግጭት በተነሳ ቁጥር በጣም ብዙ ስደተኞች ይፈልሳሉ በየሀገሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ቁጥሩ ይጨምራል። የሰው ሞት አለ፤ መቁሰል አለ፤ አደጋ አለ፤ የቤት እና የቤተሰብ መፍረስ አለ፤ ከባድ ፍልሰ,ት አለ፤ ይሄ ራሱ ትልቅ ችግር ነው።»
የሆነ ሆኖ በጅዳ ትናንት የተጀመረው የተኩስ ማቆም ንግግር ውጤት ገና አልታወቀም ። ንግግሩ ከስምምነት ቢደረስ እንኳ የሁለቱ ኃይላት ወታደሮች በምን ያህል ፍጥነት ዉግያ አቁመው ወደ ሰላም እንደሚመለሱ ማረጋገጫ ማግኘቱም አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም። ቀኑ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር የሚቀጥፈው የሰው ልጅ ህይወት ፤ የሚያደርሰው አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ቀውስ ፤ አገራዊ ኤኮኖሚያዊ እና ሌሎች ማህበራዊ ምስቅልቅሎችን ለመተንበይም እንዲሁ ማስቸገሩ አይቀርም። ለሰላም የተጣራችው ጂዳ ሰምሮላት ቸር ታሰማን ይሆን ? ታምራት ዲንሳ ነኝ።ሰላም!
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ