1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሱዳንን ጦርነት ያባባሰው የአረብ ኤሜሬት ጦር መሣሪያ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ሐሙስ፣ ኅዳር 18 2018

ሱዳን የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ለፈጥኖ ደረሽ ኃይሉ የምትሰጠውን ድጋፍ እንድታቆም ጠየቀች። የአውሮጳ ሕብረት ምክር ቤት አባላትም ይህን ለማስቆም ያለመ ውይይት እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል።

የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የጠየቀ ሰላማዊ ሰልፍ
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ለንደን ላይ የተካሄደው ሱዳን ውስጥ በሚካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት እጇ እንዳለበት የሚነገረው የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የጠየቀ ሰላማዊ ሰልፍ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Zak Irfan/Avalon/picture alliance

የሱዳንን ጦርነት ያባባሰው የአረብ ኤሜሬት ጦር መሣሪያ

This browser does not support the audio element.

 

ሱዳን የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ለፈጥኖ ደረሽ ኃይሉ የምትሰጠውን ድጋፍ እንድታቆም ጠየቀች። ወታደራዊው የሱዳን መንግሥት አረብ ኤሜሬት በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን እና ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል የጦር መሣሪያ ማቅረቧን እንድታቆም ተማጽኗል። በአረብ ኤሜሬት አማካኝነት የተላኩ አውሮጳ ሠራሽ የጦር መሣሪያዎች ሱዳን ውስጥ ጦርነቱን እያባባሱ ነው የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው። የአውሮጳ ሕብረት ምክር ቤት አባላት ይህን ለማስቆም ያለመ ውይይት እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል። ሸዋዬ ለገሠ ዘገባ አጠናቅራለች።

የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ወደ ሰላም እና ተኩስ አቁም እንዲመጡ ተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገዋል አሁንም ቀጥሏል። ሁለቱም ወገኖች ግን አንዳቸው ሌላቸውን የግጭቱ አባባሽ አድርገው ከመክሰስ ባለፈ ተግባራዊ እርምጃ ሲወስዱ አልታዩም። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የሱዳን እና የአረብ ጉዳዮች አማካሪ ማሳድ ቡሎስ ሰሞኑን ለሁለቱ ተፋላሚ ኃይላት ለላኩት የሰላም እቅድ አዎንታዊ ምላሽ እንዳላገኙም ተናግረዋል።

«ለተኩስ አቁሙ ጠንካራ መልእክት ቢላክም፤ እስካሁን የሱዳን ታጣቂ ኃይም ሆነ ፈጥኖ ደራሹ ኃይል በይፋ አልተቀበሉትም። ትናንት የፈጥኖ ደራሹን የብቻ የተኩስ አቁም ወይም ከአጥፊ ድርጊቶች መቆጠብን የተመለከተ መግለጫ ተመልክተናል። ያን ተግባራዊ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ወገኖችይፋዊ ቁርጠኝነትና ትብብር፤ ተጨማሪ ሕይወት የሚያሳጣ ቅድመ ሁኔታ፤ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ አቋም ያልገባበት ሰብአዊነትን ማዕከል ያደረገ አስቸኳይ የተኩስ አቁም፤ ሲያደርጉ እናያለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።» እኛና ዓለም አቀፍ ተባባሪዎቻችን የተኩስ አቁሙን ለመደገፍና ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ዝግጁ ነን።»

የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ፤ ለጦርነቱ መባባስ ለፈጥኖ ደራሹ ኃይል ድጋፍ በመስጠት የሚከሳት አረብ ኤሜሬትስ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ብትጠይቅም፣ ከዚህ ድርጊቷ ሳትታቀብ የምትለው ተዓማኒነት የለውም ብሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙዋያ ኦትማን ካሊድ፤ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት አሸባሪ ያሉትን ሚሊሺያ መደገፏን ካላቆመች ለታሰበው የሰላም ግንባታም ሆነ መረጋጋት ተዓማኒ አጋር መሆን አትችልም ነው ያሉት።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የአውሮጳ ሕብረት ፓርላማ ለአረብ ኤሜሬት የጦር መሣሪያ መሸጥ እንዲቆም በሚለው ሃሳብ ላይ እየተከራከረ መሆኑ ተሰምቷል። ሽትራስቡርግ ፈረንሳይ ላይ የተሰባሰቡት የሕብረቱ ፓርላማ አባላት ለተባበሩት አረብ ኤሜሬት የሚሸጠው የጦር መሣሪያ ወደ ሱዳንእየተላከ ጦርነቱን አባብሷል የሚለውን መነሻ በማድረግ ይነጋገራሉ። የምክር ቤት አባላቱ የአውሮጳ ሕብረት ከአረብ ኤሜሬት ጋር ያለውን የነጻ ንግድ ውል ሙሉ በሙሉ እንዲያቆም ነው የጠየቁት።

አረብ ኤሜሬት ለፈጥኖ ደራሹ የሱዳን ኃይል አውሮጳ ሠራሽ የጦር መሳሪያ እያቀረበች ነው የሚል ክስ ቀርቦባታል፤ የተባለውን ብታስተባብልም። ጉዳዩን የመረመሩ የተመድ ባለሙያዎችና ዓለም አቀፉ የመብት ተቆርቋሪ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግን በየበኩላቸው ባወጧቸው ዘገባዎች ፈጥኖ ደራሹ ኃይል አውሮጳ ሠራሽ የጦር መሣሪያዎችን በአረብ ኤሜሬት በኩል እያገኘ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል።

በምሥራቅ አፍሪቃ ተጽዕኖ ማሳደር እንደቻሉ ከሚነገርላቸው ሃገራት አንዷ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትን ከሱዳን ጋር የሚያሳይ ካርታ

ወደ ሱዳን የጦር መሣሪያ እንዳይገባ የተጣለውን ማዕቀብ ጥሷል የተባለውን እርምጃ የተቃወሙት የአውሮጳ ሕብረት ምክር ቤት አባላት ታዲይ መሣሪያው አምራችን ሀገር ጨምሮ ከአውሮጳ ወደ አረብ ኤሜሬት የጦር መሣሪያ እንዳይላክ መመሪያ እንዲወጣ ጠይቀዋል። ኔዘርላንዳዊቷ የአውሮጳ ፓርላማ አባል ሜሪት ማይ፤

«የጦር መሣሪያዎች በተባበሩት አረብ ኤሜሬት አማካኝነት ወደ ፈጥኖ ደራሹ ኃይል እየሄደ እስከሆነ ድረስ የአውሮጳ ምክር ቤት ከአረብ ኤሜሬት ጋር የሚያደርገውን የንግድ ድርድር እንዲያቆም ጥሪ እናቀርባለን።»

የአውሮጳ ሕብረት በትራምፕ መመሪያ ምክንያት ከአሜሪካ ጋር የንግድ ግንኙነቱን ለመቀጠል በመቸገሩ ከሌላ ሦስተኛ ወገን ጋር የንግድ ውል ለማድረግ እየሞከረ ነው። ከተባበሩት አረብ ኤሜሬት ጋር የሚያደርገው የንግድ ድርድርም በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2025 ማለቂያ ላይ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል። ከሕብረቱ ምክር ቤት አባላት ግን ይህ እንዲቋረጥ የሚጠይቁ ጥቂት አይደሉም። በሌላው በኩል የንግድ ትስስሩ እንዲሰፋ የሚፈልጉ የምክር ቤት አባላት ደግሞ የንግድ ድርድሩን በአረብ ኤሜሬት ላይ ጫና ለማሳደር መጠቀም ይቻላል ባይ ናቸው። 

ፈጥኖ ደራሹ ኃይል ሱዳን ውስጥ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመፈጸም እየተከሰሰ ነው፤ ቡድኑ ሰሞኑን ኤልፋሸር ውስጥ መጠነ ሰፊ አስገድዶ የመድፈር ጥቃት እና ረሀብን እንደየጦር መሳሪያ በመጠቀም ተከሷል። ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ICC ድርጊቱ የጦር ወንጀል መሆኑን ለማጣራት ምርመራ እያደረገ ነው። ሱዳን ውስጥ በተባባሰው ውጊያ ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩት ወደ ሊቢያ መሰደዳቸው ውሎ አድሮ ወደ አውሮጳ የሚፈልሱትን ቁጥር ሊያበረክተው ይችላል የሚለውን ስጋትም የሚያነሱ የምክር ቤቱ አባላት አሉ።

ሱዳን ውስጥ በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃትና መፈናቀል ለማስቆም የሚሻለው ወደ ሀገሪቱ የሚገባውን የጦር መሣሪያ ማስቆም ነው የሚለው ሃሳብ የአውሮጳ ምክር ቤት አባላት ብቻ ሳይሆን የመብት ተሟጋች ተቋማትም ሆኗል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW