1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሱዳን መንግስት እና አማጽያን የሰላም ስምምነቱን ፊርማ አኖሩ

ቅዳሜ፣ መስከረም 23 2013

የሱዳን የሽግግር መንግስት እና ተቃዋሚዎች አስርት አመታት ላስቆጠረው የእርስ በእርስ ደም አፋሳሽ ግጭት መቋጫ ያስገኝለታል የተባለለትን የሰላም ስምምነት ዛሬ ደቡብ ሱዳን ጁባ ውስጥ ተፈራረሙ። የሁለቱ ወገኖች የሰላም ስምምነቱን የተፈራረሙት ውይይቱን  ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው።

Südsudan Juba Unterzeichnung Friedensvertrag mit Rebellen
ምስል፦ Reuters/S. Bol

የሱዳን የሽግግር መንግስት እና አማጽያን አስርት አመታት ላስቆጠረው የእርስ በእርስ ደም አፋሳሽ ግጭት መቋጫ ያስገኝለታል የተባለለትን የሰላም ስምምነት ዛሬ ደቡብ ሱዳን ጁባ ውስጥ ተፈራረሙ። የሱዳን የሽግግር መንግሥት እና የተቃዋሚ ቡድኖች ታሪካዊ የተባለለትን ይህንኑ የሰላም ስምምነት የተፈራረሙት የሰላም ውይይቱን  ከጀመሩ ከአንድ ዓመት በኋላ መሆኑ ተመልክቷል። የቀድሞው አምባገነን ሀሰን ኦማር አልበሽር በህዝባዊ አብዮት ከስልጣናቸው ከተገረሰሱ ወዲህ  በሀገሪቱ የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት የሀገሪቱን የውስጥ ግጭት እልባት እንዲያገኝ ቅድሚያ ሰጥቶ ሲሰራ ነበር ተብሏል። የሽግግር መንግስቱን ከአማጽያኑ  የማሸማገሉን ሂደት ሲያስተባብሩ የነበሩት የደቡብ ሱዳኑ ቱት ጋትሉክ  «የሰላም ስምምነቱ በስኬት ተጠናቋል፤ ደስ ተሰኝተናልም» ብለዋል።የሰላም ስምምነቱን የሱዳን መንግስትን በመወከል የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀ መንበር ሉቴናንት ጄኔራል ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ  ሲፈርሙ ከአማጽያኑ ወገንም በሰላም ሂደቱ ላይ  ተሳታፊ የነበሩ የምዕራብ ዳርፉር ግዛት አማጽያን ፣ የደቡባዊ ብሉ ናይል እና የደቡባዊ ኮርዶፋን አንጃዎች በየፊናቸው ፊርማቸውን አኑረዋል። በፊርማ ስነስረዓቱ ላይ  የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፣ የአውሮጳ ህብረት ፣ ግብጽ ፣ቻድ  እና እና ኳታር ተወካዮች ተገኝተዋል።በሰላም ስምምነቱ የመሬት ባለቤትነት የሃብት እና የስልጣን ክፍፍልን ጨምሮ በጦርነቱ ለተጎዱት ካሳ በሚከፈልበት እና በዚሁ ምክንያት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ተሰደው የቆዩ ሱዳናውያን ወደ መኖርያቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ እልባት እንደሚያገኙ ተጠቁሟል። ።

ታምራት ዲንሳ 

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW