የሱዳን መፈንቅለ መንግስትና የስቪሎች ምላሽ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 2 2014
የ61 ዓመቱ የሱዳን ወታደራዊ ገዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ሰኞ ዕለት የሽግግር መንግሥቱ መፍረሱን በማወጅና በምትኩ ለሲቪልና ለዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ድጋፍ በመስጠት ከስቪሉ ሕዝብ አድናቆትና ቀልባቸውን ለመሳብ ጥረው ነበረ። ከዚህም በተጨማሪ አዲስ ከፍተኛ ወታደራዊ ምክር ቤት ለማቋቋም ያለቸውን ዕቅድ ገልጿል ።
በአንፃሩ ደግሞ አብዛኞቹ ሲቪል የፖለቲካ አቀንቃኞች ከመካከላቸው ታላቅ አንጃ የሆነው የነፃነትና የለውጥ ኃይሎች (ኤፍ.ኤፍ..ሲ) ያቀረበውን ሐሳብ ወዲያውኑ ውድቅ በማድረግ በካርቱም በየቀኑ በሚደረጉ ተቃውሞዎችና ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማዎችን የማድረግ ንቅናቄው እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል ።
"ትልቅ ውሸት ይመስለኛል" ሲል ሱዳናዊት የፖለቲካ አቀንቃኝ ራኒያ አብደልአዚዝ ለDW ተናግራለች። አክላም "አሁንም እየገደሉን ነው ፣ አሁንም ተቃውሞውን ለማስቆም እየሞከሩ ነው ፣ አሁንም አብዮታዊ መንፈሱን ለማጥፋት እየጣሩ ነው" ብላለች ።
„ ወታደሩሮቹ እኔ እንደሚመስለኝ ትልቅ ውሸት እየዋሹ ነው። በሲቪሎች መካከል መሰነጣጠቅ እንዳለ፣ ውግያውም በስቪሎች መካከል እንደሆነ አድርገው እያቀረቡ ነው። ልክ እንደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቱ እነሱ እንዳልጀመሩት፣ ለአንድ ዓመት ተኩል የዘለቀውን የሽግግር ጊዜ በነሱ ተንኮል እንዳልተሰናከለ አስመስለው እተየናገሩ ነው። በተጨማሪም ስቪል ማሕበረሰቡ አብሮ መሥራት እንደማይችልና በአንድ ግንባር መሰባሰብ እንደማይችል አድርገው ያስባሉ፣ ነገሩ ግን እሱ አደለም። ``
ቡርሃን በጥቅምት 2021 በወታደራዊ መር መፈንቅለ መንግሥት ርምጃ ሥልጣን ላይ ከወጡ ቦኋላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች የጦር ሠራዊቱ "ወደ ጦር ሰፈሮቹ እንዲመለስ" እና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ በማቅረብ አደባባይ ላይ ናቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ 114 ተቃዋሚዎች መገደላቸውንና ከ5,000 በላይ ተቃዋሚዎች መቁሰላቸውን የሱዳን ዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ ገልጿል። ሱዳናዊትዋ የፖለቲካ አቀንቃኝ ራንያ አብደል አዚዝ አክላ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተቆናጠጡት ወታደሮች ስቪል ዜጎችን እየገደሉ እንደሆነ ትገልጻለች
`` አሁንም ድረስ በየጎደናው እየገደሉን ነው። በየቀኑ እየገደሉን ነው። ይህን የሚያደርጉት ተቃውሞውን ለማስቆምና የአብዮቱን መንፈስ ለመግታት ነው። እነሱ ስልጣን ለስቪል ማህበረሰቡ ለማስረከብ ምንም አይነት ቅን ፍላጎት የላቸውም። የራሳቸው ኢኮኖሚምም እያበለጸጉ ነው። ስልጣን ለስቪል ማሕበረሰቡ አስረከቡ ማለት እነዚህን እንዳየደርጉ ይከላከላቸዋል። ስለዚህ ለፈጸሙት መፈንቅለ መንግስት ከደሙ ንጹህ ነን የማለት ጨዋታ ነው።``
ታህሪር በተባለ የመካከለኛው ምስራቅ ፖሊሲ ተቋም ባልደረባ ሱዳናዊው ሃሚድ ካላፋላህ "ወታደራዊ ኃይሉ ከፖለቲካው ሂደት ለመራቅ እውነተኛ ፍላጎት የለውም ። ሲቪሎች ከመንግሥቱጋ በሚደረጉ ንግግሮች እንዳይሳተፉ ስልታዊ ጨዋታ እየተጫወቱ ነው "ሲሉ ለDW ተናግረዋል ።
`` ጥያቄያችን ገና አልተመለሰም። ወታደሮቹ በቅርቡ ካወጡት መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው ከፖለቲካዊ ንግግር እየሸሹ ነው። በፖለቲካ ሂደቱ ቅንነት ይጎድላቸዋል። ስቪሎችን አሳትፎ ፖለቲካዊ ንግግር ከማድረግ ይልቅ ከፍተኛ ወታደራዊ ምክርቤት መመስረትን መርጧል። ከፖለቲካዊ ውይይት ለመራቅ የሚጠቅሙበት ስልታዊ ጨዋታ ነው። ይህደግሞ በወታደራዊ ምክርቤቱና በሱ ውስጥ ባሉ መዋቅሮች ስልጣንን ለመቆጣጠር እንዲያስችላቸው ነው። ለዚሁ ነው ሕዝቡ በተቃዎሞው የገፋበት። ከ114 ተቃወሚ ሰልፈኞች ተገድሏል፣ ላለፉት 8 ወራት ተቃውሞው ቢቀጥልምና መስዋዕት ቢከፈልም የሕዝቡ ጥያቄዎች ግን አልተመለሱም``
ቡርሃን ቀደም ሲል አገሪቱን ከጥቃት የመጠብቅ እንጂ ሌላ ፍላጎት እንደሌላቸው መግለጻቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ ከወታደራዊ ኃይልና ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች ጋር በመተባበር "ከፍተኛ ወታደራዊ ምክር ቤት" ለማቋቋም ማቀዳቸው የሱዳን ባንክን ኢኮኖሚን ጦሩን እንዲቆጣጠሩ ያስገድዳል" ሲል ተንታኝ ካላፋላህ ለዶቸቨለ ገልጿል ። በወታደሮቹ የእስካሁን ቆይታ ኢኮኖሚው መንኮታኮቱንና አገሪቱን ማስተዳደር እንዳልቻሉ በማከል።
``ወታደሮቹ የቅርቡ መግለጫ እንዲያወጡ የገፋፋቸው ከመፈንቅለ መንግስት በዘለለ መቀጠል እንደማይችሉ የተገነዘቡ ይመስለኛል። ባለፉት 8 ወራት ሁሉንም ተግባሮቻቸው አልተሳኩም። ሕጋዊ ቅቡልነት ያለው መንግስት ለማቋቋምና መንግታዊ ሥራ ለማከናወን አልቻሉም። የጸጥታ ሁኔታው ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ ነው፣ ኢኮኖሚው እየወደቀ ነው፣ በመፈንቅለ መንግስቱ ምክንያት ሁሉም ዓይነት የሕይወት ተግባራት ተጎድቷል፣ አገሪቱን ለማስተዳደርም አልቻሉም። ይህን መገንዘብ አለባቸው። በመሆኑም ስልጣናቸውን እስኪያስረክቡ ድረስ ሕዝቡ ጥያቄውን ይገፋበታል።``
በሱዳን 45 ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርበት ሁኔታ እጅግ አስከፊ ሆኗል ። የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) እንደገለፀት 18 ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናውያን እ.ኤ.አ በመስከረም 2021 አጣዳፊ ረሃብ አጋጥሟቸው ነበር ።ይሁንና መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ የነበረው አለመረጋጋት ፣ እንዲሁም ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ ከውጭ የሚገባው የስንዴ እጥረት ፣ የዋጋ ግሽበት ፣ ዓለም አቀፍ ማዕቀብና አሁን በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታን አባብሶታል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ማንተጋፍቶት ስለሺ