1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ስደተኞች አዲስ ወደ ተገነባዉ መጠለያ ጣቢያ መግባት

ሰኞ፣ ነሐሴ 27 2016

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በኩመርና አውላላ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ የሱዳን ስደተኞች አዲስ ወደተገነባው «አፍጥጥ» የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ መግባታቸውን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት (RRS) አስታውቋል፣ ስደተኞች በበኩላቸው «አዲሱ መጠለያ ጣቢያ የተሻለ አገልግሎትቶች አሉት» ብለዋል፡፡

የሱዳን ስደተኞች መጠለያ በኢትዮጵያ
የሱዳን ስደተኞች መጠለያ በኢትዮጵያ ምስል UNCHCR

የሱዳን ስደተኞች ወደ አፍጥጥ መተለያ ጣቢያ መግባት

This browser does not support the audio element.

የሱዳን ስደተኞች ወደ አፍጥጥ መተለያ ጣቢያ መግባት

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በኩመርና አውላላ መጠለያ ጣቢያ የነበሩ የሱዳን ስደተኞች አዲስ ወደተገነባው “አፍጥጥ” የስደተኞች መጠለያ ጣቢያመግባታቸውን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት (RRS) አስታውቋል፣ ስደተኞች በበኩላቸው “አዲሱ መጠለያ ጣቢያ የተሻለ አገልግሎትቶች አሉት” ብለዋል፡፡

ሱዳን ጦርነት የተሰደዱ ሱዳናውያን

በሚዝያ 2015 ዓ ም በሱዳን የተቀሰቀሰውን የእርስበርስ ጦርነት ተከትሎ በርካታ የተለያዩ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ከሱዳን ተሰድደው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፤ ከሱዳን ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ዜጎች መካከል የሱዳን ዜግነት ያላቸው ስደተኞች አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙ ሲሆን  ስደተኞቹ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ አውላላና ኩመር በተባሉ የመጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡

የስደተኞቹ ቅሬታ

በሁለቱ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖሩ የነበሩ የሱዳን ስደተኞች ቀደም ሲል “በመጠለያዎቹ የግብዓት አቅርቦትና የፀጥታ ችግሮች አጋጥሞናል” በማለት የተወሰኑት ከመጠለያዎቹ ወጥተው በመንገድ ዳር የቆዩ ናቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ “ደህንታችን ወደሚጠበቅበትና በቂ አቅርቦት ወደአለበት አካባቢ እንዛወር” በሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ያን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስትና የስደተኞች ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሌላ አዲስ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በዚሁ ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ “አፍጥጥ” በሚባል አካባቢ ተገንብቷል፡፡

አዲስ የተገነባው አፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ

ስደተኞቹ አሁን አዲስ ወደተገነባው አፍጥጥ መጠለያ ጣቢያ ጠቅልለው መግባታቸውንና ቀደም ሲል አገልግሎት ይሰጡ የነበሩት አውላላና ኩመር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መዘጋታቸውን በመተማ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት (RRS) የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ብስራት ደጉ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችም በጣቢያው እየተካሄዱ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የሱዳን ስደተኞች መጠለያ በኢትዮጵያ ምስል UNCHCR

ስደተኞች ወደ አዲሱ መጠለያ ስለመግባታቸው

ኃላፊው አክለውም እስከ 9 ሺህ ስደተኛ በመጠለያ ጣቢያው እንደሚኖር አመልክተው ሁሉም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሆነና ከስደተኞች በኩል የቀረበ ቅሬታ አእስካሁን እንዳልቀረበ ገልጠዋል፡፡ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ እየተካሄደ እንደሆነም አቶ ብስራት አብራርተዋል፣ የመተጥ ውሀ ዝርጋታም ተከናውኖ ስደተኞቹ እየተጠቀሙ ነው ብለዋል፡፡፡፡

ባለፈው ግንቦት 2016 ዓ ም መሰረታዊ ፍላጎታችን አልተሟላም በማለት ከመጠለያ ጣቢያቸው ወጥተው ከነበሩ 1ሺህ 300 ያክል ስደተኞች መካከል ተወሰኑት ወደ አዲሱ መጠለያ መመለሳቸውንና ሌሎቸ ደግሞ ወደ ሀገራቸው መሄዳቸውንም ኃላፊው አመልክተዋል፡

ከመጠለያ የወጡ ስደተኞች ሁኔታ

ግንቦት 2015 ከስደተኞች ከመጠለያ ስለወጡ ስደተኞች የተጠየቁት አቶ ብስራት፣ “ በፍላጎታቸው ከስደተኛ መጠለያዎች የወጡ አንዳንዶቹ ተመልሰዋል ሌሎች ደግሞ በፍላጎታቸው ወደ አጋችን እንሄዳለን ስላሉ ሄደዋል” ሲሉ መልሰዋል፡፡

የስደተኞች አስተያየት

በአፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ ከሚገኙ ስደተኞች መካከል ጆሴፍ ዊሊያምስ “አውላላና ኩመር የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ተዘግተዋል” ብሏል፡ሁሉም ስደተኞች ወደ አዲሱ አፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ መግባታቸውን በመግለፅ፡፡ አህመድ ናስር የተባለ ስደተኛ በበኩሉ አዲሱ መጠለያ የተሻለ ፀጥታ መኖሩንና ያሉ አቅርቦቶችም መልካም ሚባሉ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

የሱዳን ስደተኞች መጠለያ በኢትዮጵያ ምስል UNCHCR

“ሁሉም ስደተኞችከቀድሞዎቹ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ወጥተዋል” ያለው አህመድ በአዲሱ የስደተኞች መጠለያም አስፈላጊውን አገልግሎት እያገኙ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ከነሐሴ 19 ጀምሮ አብዛኛው ስደተኛ ወደ መጠለያው ገብቷል ነው ያለው፣ በመጠለያ ጣቢያው የተሸለ የፀትታ ሁኔታ፣ የመሰረታዊ አገልጎቶች አቅርቦትና የመንገድና የትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጧል፡፡ 

በኢትዮጵያ የስደተኞች ቁጥር

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሐምሌ 2024 ሪፖርት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ 1 ሚሊዮን 64 ሺህ 412 የተለያዩ አገር ስደተኞች በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በሚገኙ 24 የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖራሉ፣ ከ4 ሚሊዮን በላይ ደግሞ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሆነው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተመዝግበዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW