1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ቀዉስ ያስከተለዉ የታሪካዊ ቅርሶች ዘረፋ እና ዉድመት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 28 2017

ጎረቤት አገር ሱዳን በእርስ በርስ ጦርነት ዛሬም እየታበጠች ነዉ። በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናዉያን በጦርነቱ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸዉን አጥተዋል። የሃገሪቱ ነዋሪዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል። በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የሱዳን ጥንታዊ ታሪክን የሚገልፁ በርካታ ቅርሶች ወድመዋል አልያም ተዘርፈዋል።

በሱዳን ሚሊሽያ በናጋ ዓለም ቅርስ ፊት ለፊት የተነሳዉ ፎቶ
በሱዳን ሚሊሽያ በናጋ ዓለም ቅርስ ፊት ለፊት የተነሳዉ ፎቶምስል Naga-Projekt, Staatliches Museum Ägyptischer Kunst

የሱዳን ቀዉስ ያስከተለዉ የታሪካዊ ቅርሶች ዘረፋ እና ዉድመት

This browser does not support the audio element.

የሱዳን ቀዉስ ያስከተለዉ የታሪካዊ ቅርሶች ዘረፋ እና ዉድመት

 

«መርዌ ማለት አክሱም ማለት ነዉ። ይህ ማለት የአክሱም ስልጣኔ ወደመ እንደማለት ነዉ። አሁን ሱዳን ሜርዌ ላይ የሚታየዉ የእርስ በእርስ ጦርነት ብዙ ታሪካዊ ቅርስን ያወድማል እስካሁን ስለወቅታዊዉ ሁናቴ ለማወቅ ሰዎችን እንኳ መጠየቅ አልቻልንም» ስለ ጥንታዊዉ ሜርዌ ስልጣኔ አስተያየት የሰጡትን በኢትዮጵያ ታዋቂ የሆኑት የጥንታዊ ስነ ቅርስ ማለትም አርኪዮሎጂ ምሁር እና በአሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘዉ የሲምሶንያን ኢንስቲትውት የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ ዶክተር ዮሃንስ ዘለቀ ናቸዉ።

ጎረቤት አገር ሱዳን በእርስ በርስ ጦርነት ዛሬም እየታበጠች ነዉ። በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናዉያን በጦርነቱ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸዉን አጥተዋል። የሃገሪቱ ነዋሪዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል። በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የሱዳንን ብሎም የአካባቢዉን ጥንታዊ ታሪክን የሚገልፁ በርካታ ቅርሶች ወድመዋልአልያም ተዘርፈዋል። የአርኪዮሎጂ ምሁሩ ዶክተር ዮሃንስ ዘለቀ በሱዳን ጦርነት የሚወድመዉ ጥንታዊ ቅርስ፤ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅሪት ሱዳን  ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ሃገራትን ፤ አፍሪቃን ብሎም የዓለም   ታሪክ እንደሆነ ተናግረዋል።

«ይህ በቅርስ ጥናት እና ጥበቀ ሂደት፤ በዓለም ላይ ከታወቁት ቅርሶች መካከል፤ የናጋ ሱዳን አንዱ ነዉ። ይህ በናጋ የሚገኘዉ ቤተ መንግሥት እና ቤተመቅደስ የሚገኝበት ከተማ በከፍተኛ ቁፋሮ በአርኪዮሎጂ ምሁራን ነዉ ከ 1990 ዓም ጀምሮ የተገኘዉ።  የናጋ ጥንታዊ ቅርስ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በዩኔስኮ የተመዘገበ  የታሪቅ ቅሪቶች የሚገኙበት ቦታ ነዉ። እነዚህ በቅርቡ የተገኙት ጥንታዊ ቅሪቶችን የሚጠኑት ምሁራን በጦርነቱ ምክንያት ጥናታቸዉን አቋርጠዉ ቦታዉን እንዲለቁ ተገደዋል። በጦርነቱ ምክንያት ይህ ቅርስ በጦርነቱ ምክንያት ስለመጎዳት አለመጎዳቱ እስካሁን በእርግጥ ማወቅ አልተቻለም። ተንቀሳቃሽ የሆኑት እና በተለያዩ የሱዳን ቤተመዘክሮች የነበሩ ቅርሶች በታጣቂዎች መዘረፋቸዉ ይነገራል። ከፍተኛ ሃዘን ላይ ነዉ የምንገኘዉ።  እንዲህ አይነት ነገር ከዚህ ቀደም በኢራቅ ጦርነት ሲቀሰቀስ ከባግዳድ ቤተ መዘክሮች በከፍተና መጠን ቅርሶች መዘረፋቸዉ የምናስታዉሰዉ ነዉ። ግን ቀደም ሲል የኢራቅ መንግሥት ቅርሶቹን በስነ ስርዓት መዝግቦ ስለነበር ቅርሶቹ በዓለም ሃገራት ሽያጭ ላይ ሲቀርቡ በመንግሥታቱ ድርጅት በኩል እየተለቀሙ ወደ ሃገራቸዉ እንዲመለሱ መደረጋቸዉ ይታወቃል። በሱዳንም ሰላም እስካልመጣ ድረስ ብዙ ይዘረፋል ብዙ ይወድማል፤ ሁኔታዉ ለታሪካዊ ቅርሶች አስቸጋሪ ሁኔታ ነዉ ያለዉ። ይህን ለመታደግ እየተሞከረ ነዉ ያለዉ»

በሰሜናዊ ሜሮ የፒራሚዶች መቃብር ምስል Pawel Wolf

ከሱዳን ጦር ሰራዊት ጋር የሚዋጉት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ክላሽንኮፍ ተሸክመዉ በቁፋሮ በተገኘዉ በጥንታዊዉ ናጋ መንደር ፊት ለፊት ቆመዉ የድል ምልክት ጣቶቻቸዉን እያሳዩ ፎቶግራፍ እና ቪዲዮ ተቀርፀዉ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ከለቀቁ በኃላ ቅርሱን ይበልጥ እንዳያወድሙትምሁራንን አስግቷል። በሜርዌ ጥንታዊ ስልጣኔ በዛሬዋ ሱዳን ዉስጥ የተገነቡት እነዚህ ጥንታዊ ቤቶች እና የተለያዩ ቁሳቁሶች የሚገኙበት ናጋ ጥንታዊ መንደር ፤ ከሱዳን ዋና መዲና ከካርቱም በስተ-ሰሜን ምሥራቅ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ናት። በአንድ ወቅት የሥልጣኔ መገኛ ተደርጎ ይታይ የነበረዉ ይህ አካባቢ ከአባይ ወንዝ ተፋሰስ ብዙም እንደማይርቅ ተመልክቷል። በሜርዌ ስልጣኔ ዘመን የተገነባዉ ናጋ የተባለዉ እና በሱዳን በቁፋሮ የተገኘዉ ይህ ጥንታዊ ከተማ፤ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ 250 ዓመት አካባቢ የተገነባ እና የሜርዌ መንግሥት መኖሪያ የነበረ ፤ ብዙ ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥት ሕንፃዎች የሚገኙበት እንደነበር የታሪክ መዝገባት ያሳያሉ።

ዶክተር ዮሃንስ እንደሚሉት« የሜርዌ ስልጣኔ ይባላል፤ ይህ በከፊል የኢትዮጵያም ስልጣኔ ነዉ። ኢትዮጵያ ከከሰላ ጀምሮ እስከ ሱዳን ሜርዌ ድረስ ያለዉ፤ የኢትዮጵያ ግዛት ስለነበር ብዙ የኢትዮጵያ ቅርሶችም እዝያ ይገኛሉ። በናጋ የሳባዉያን ጽሑፍ የምንለዉ ሁሉ በቁፋሮ ተገኝቷል። በናጋ ይህን ተከትሎ ባለፉት 30 እና 35 ዓመታት በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። በቅርቡም የጀርመን የምርምር ቡድን እቦታዉ ላይ የምርምር ቆፋሮ ሁሉ እያካሄደ ነበር ይህ የምርምር ስራ ነዉ በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠዉ።»  

የካርቱም ብሔራዊ ሙዚየም በወታደሮች ተዘርፏልምስል Ashraf Shazly/AFP

 የሜርዌ ስልጣኔ የሰራቸው ፒራሚዶች ፍርስራሽ በዛሬዋ ሱዳን ይገኛሉ፡፡ የአክሱም ስልጣኔ ማበብ ለሜርዌ ስልጣኔ መውደቅ አንደኛው ምክንያት እንደሆነም ይነገራል። በጥንታዊዉ ናጋ መንደር ከጎርጎረሳዉያኑ 1990 ዎቹ ወዲህ በአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ሦስት ቤተ መቅደሶች በቁፋሮ ተገኝተዋል። በዚህ ምርምር ላይ ከተገኙት ምሁራን መካከል ከጀርመን ባቫርያ ግዛት ከሙኒክ የግብፅ የሥነ ጥበብ ሙዚየም የተላከ አንድ የጀርመን ቡድን በቁፋሮዉ እና በግኝቱ ላይ ተሳትፏል። ተመራማሪ አርኪዮሎጂዎቹ እንደሚናገሩት፤ በናጋ ጥንታዊ ፍርስራሽ ስር ዛሬም ድረስ በቁፋሮ ያልወጡ ሃምሳ ተጨማሪ ቤተ-መቅደሶች፣ ቤተ መንግሥቶችና የአስተዳደር ሕንፃዎች እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ መቃብሮች ይገኛሉ። የጥንታዊ ሥነ-ቅርስ ተመራማሪ ዶክተር ዮሃንስ ዘለቀ እንደሚሉት ሱዳን እጅግ ጥንታዊ ቅርሶች የሚገኙባት ሃገር ናት። በሱዳን ዛሬ እያየነዉ ያለዉ የእርስ በእርስጦርነት የአፍሪቃን ጥንታዊ የታሪክ ቅሪትን እያወደመ ነዉ።

በሱዳን ጦር ሰራዊት መሪ በጀነራል አብደል ፋታህ ቡርሃን እና በቀድሞ ምክትላቸዉ በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጭ ኃይል አዛዥ በጀነራል መሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ መካከል ከባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን 2023 ዓመት የጀመረዉ የእርስ በእርስ ጦርነት ማብቅያ ያለዉ አይመስልም። የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የዓለም መንግሥታት ጦርነት የገጠሙት የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ወደ ጠረቤዛ ዙርያ መጥተዉ ችግሮቻቸዉን በዉይይት እንዲፈቱ በተለያዩ ጊዜያት ጥሪ ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ አልተገኘም።  በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበዉ የሱዳኑ የናጋ ጥንታዊ መንደር፤ በሱዳን ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀዉ የእርስ በእርስ ጦርነት፤ ጨርሶ እንዳይወድምም ስጋት ቀስቅሷል። በአሁኑ ወቅት አካባቢዉን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የመሐመድ ሀምዳን ዳጋሎ ሚሊሻዎች  እንደተቆጣጠሩት ታዉቋል።  

አርኪዮሎጂስት አንጀሊካ ሎህዋሰር ከጎርጎረሳዉያኑ 2009 ጀምሮ በሰሜን ሱዳን ምርምር ሲያካሂዱ ቆይተዋልምስል privat

በጀርመን የሙኒክ የግብፅ የሥነ ጥበብ ሙዚየም ዳይሬክተር አርኑልፍ ሽሉተር የሱዳኑ ጦርነት ለጥንታዊ ቅርሶች ደህንነት "በጣም አስከፊ ሆንዋል" ብለዋል። በሜርዌ ስልጣኔ ዘመን የነበሩ ቅሪቶችን በመፈለግ ላይ የነበሩት «አብዛኛዎቹ የቁፋሮ ሰራተኞች ሱዳንን  ሸሽተዉ መዉጣታቸዉ ተናግረዋል። የመቆፈርያ ቁሳቁሶች እና ተሽከርካሪዎች ሆነ ተብሎ  ተሰባብረዋል። በሱዳን በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ቤተ-መዘክሮች እና ጥንታዊ ቅርሶች ተዘርፈዋል።

ለምሳሌ የሱዳን እጅግ ታሪካዊ የተባሉ ጥንታዊ፣ ሐውልቶችና የአርኪኦሎጂ ስብስቦች የሚገኙበት እና በቅርቡ በዩኔስኮ እና በጣሊያን መንግሥት የታደሰዉ በካርቱም የሚገኘዉ የሱዳን ብሔራዊ ሙዚየም ከተዘረፉ የሱዳን ጥንታዊ ቅርሶች መገኛ አንዱ ነበር። ይህን ተከትሎ የሥነ ጥበብ ገበያ ባለሀብቶች ከሱዳን የተዘረፉ ቅርሶችን እንዳይሸምቱ ዩኒስኮ ጥብቅ ማስጠንቀቅያ ማስተላለፉ ይታወቃል። ከዚህ ሌላ መቀመጫዉን ካርቱ ላይ አድርጎ የነበረዉ የጀርመን የባህል ተቋም የጎተ-ኢንስቲቱት ሰራተኞች የእርስ በእርስ ጦርነቱ እንደተቀሰቀሰ ሃገሪቱን ጥለዉ ወጥተዋል። በርሊን የሚገኘዉ የጎተ ተቋም ዋና መስርያቤት እንዳረጋገጠዉ፤ በሱዳን የነበሩ ሰራተኞች በግብፅ መዲና ካይሮ ላይ ሆነዉ ከሱዳን ጋር የሚዛመዱ ሥራዎችን ያከናዉናሉ። 

ዶክተር ዮሃንስ ዘለቀ ፤ ጥንታዊ ስነ ቅርስ ማለትም አርኪዮሎጂ ምሁር እና በዩናይትድ ስቴትስ የሲምሶንያን ኢንስቲትውት የተፈጥሮ ሳይንስ ሙዝየም ተመራማሪ ምስል Yohannes Zeleke

ጀርመናዊዉ ፍራንክ ግራፌንሽታይን መንግሥትን ወክለዉ ለጋዜጠኞች እና ለቱሪዝም ሥራ አስኪያጆች የሱዳንን ባህልን የሚያስተዋዉቅ ጉብኝቶችን የሚያደራጅ ድርጅት አስተዳዳሪ ናቸዉ።  ምንም እንኳ የድርጅቱ ድረ ገጽ አሁንም ኢንተርኔት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ግራፌንሽታይን በአሁኑ ወቅት በእርስ በርስ ጦርነት ከፈራረሰችው አገር ከሱዳን ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም። ግራፍ ሽታይን «ወደ ሱዳን እንዳትጓዙ ስል እመክራለሁ » ሲሉም ይናገራሉ።

ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀዉ የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ሳብያ በሃገሪቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀዉስ ተከስቷል። ከ 10 ሚሊዮን የሚበልጡ ሲዳናዉያን ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል። 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ደግሞ ለረሃብ ተጋልጠዋል። የሃገሪቱ ጥንታዊ ቅርሶች ተዘርፈዋል አልያም ወድመዋል።

አዜብ ታደሰ / ስቴፈን ደጌ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW