1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች ወደ ኢትዮ ሱዳን ድንበር መንቀሳቀሳቸው

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 11 2016

በዚህ አካባቢም “ያልታወቁ” ታጣቂዎች በሚያደርሱባቸው ጥቃት ምክንያት ሰሞኑን ከመንገድ ዳር ለቅቀው ወደ አገራቸው ለመመለስ ኢትዮጵያና ሱዳን ወደሚዋሰነቡት ድንበር ሄደዋል፡፡

Äthiopien | Flüchtlingscamp vertriebener aus dem Sudan
ምስል UNCHCR

ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ስደተኞች ስሞታ

This browser does not support the audio element.

 በየወሩ በአማካይ ከ1ሺህ 400 በላይ ስደተኞች ከሱዳን ደንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) አስታወቀ። ከሶስት ወራት በፊት የፀጥታና የምግብ አቅርቦት ጉድለት ደርሶብናል በሚል ከመጠለያ ጣቢያቸው ወጥተው መንገድ ዳር የነበሩ የሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮ ሱዳን ድንበር መንቀሳቀሳቸውን አስታወቁ፡፡
በሱዳን ያለውን የእርስበርስ ጦርነት በመሸሽ  ከ2023 ሚያዝያ ጀምሮ  በርካታስደተኞች ድንበር እያቋረጡ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ እስከአሁን  58,000 በላይ ሱዳናውያን፣ ኤርትራዊያን፣ ደቡብ ሱዳናዊያንና ኢትዮጵውያን ድንበር አቋርጠው መግባታቸውን ድርጅቱ ለዶይቼ ቬሌ ገልጿል፡፡ ስደተኞቹም በአማራ፣ በቤኒሻንጉልና በጋምቤላ ክልሎች በተዘጋጁላቸው መጠለያዎች እንደሚኖሩም ገልጧል፡፡
አሁንም ቢሆን ከሱዳን በአማካይ በየወሩ ከ1ሺህ 400 በላይ የተለያዩ አገር ዜግነት ያላቸው ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ በማከል፡፡
12ሺህ ያክል የሱዳን ስደተኞች በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን አውላላና ኩመር በተባሉ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖሩ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ከ1ሺህ 300 በላይ የሱዳን ስደተኞች ከሶስት ወራት በፊት የፀጥታ ችግር ገጥሞናል በሚልና የመሰረታዊ የፍጆታ ቁሳቁሶች በተሟላ ሁኔታ አልቀረበለንም በማለት ከመጠለያዎቹ ወጥተው መንገድ ዳር መቆየታቸው ይታወሳል። በዚህ አካባቢም “ያልታወቁ”  ታጣቂዎች በሚያደርሱባቸው ጥቃት ምክንያት ሰሞኑን ከመንገድ ዳር ለቅቀው ወደ አገራቸው ለመመለስ ኢትዮጵያና ሱዳን ወደሚዋሰነቡት ድንበር ሄደዋል፡፡ የመንግስት አካላትና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ስደተኞች የተሻለ የፀጥታ ሁኔታ ወደአለበት አዲሱ አፍጥጥ የስደተኞች መጠለያ እንዲገቡ ተከታታይ ጥረት ቢያደረግም ስደተኞች ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

የሱዳን ተሰዳጆች ጊዚያዊ መጠለያምስል UNCHCR


ሰሞኑን ወደ ድንበር ከተንቀሳቀሱት ስደተኞች  መካከል አንዱ የመድኃኒት፣ የምግብና የመጠለያ ድንኳን እጥረት እንዳጋጠማቸው ለዶይቼ ቬሌ አመልክቷል። ወደ ሱዳን ለመግባት አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ አስቸጋር በመሆኑም ወደ ሌላ ሶስተኛ አገር መሸኘት እንደሚፈልጉ ገልጧል።
ወደ ሁሉቱ አገሮች አዋሳኝ ድንበር ከደረሱ ስደተኞች መካከል ሌላው ስደተኛ በመንገድ ዳር በቆዩባቸው ሶስት ወራት ሰዎች በታጣቂዎች  እንደቆሰሉና እንደተገደሉ ጠቅሰው በዚህም ምክንያት አካባቢውን እንደለቀቁ ተናግረዋል። ሆኖም የአካባቢው ህብረተሰብ ከሚቀርብላቸው እርዳታ ውጪ ምንም የቀረበ ነገር የለም ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ወደ መጠለያ ለመግባት  ፈቃደኛ ያልሆኑ 800 ስደተኞች ወደ ኢትዮ ሱዳን ድንበር መሄዳቸውን አረጋግጧል።  ሱዳን አሁን ጦርነት በመኖሩ ስደተኞች ወደዚያ እንዲሄዱ ድርጅቱ አያበረታታም፣ ድጋፍና እገዛም አያደርግም ብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሐምሌ 2024 ሪፖርት እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ከ1 ሚሊዮን 64 ሺህ በላይ የተለያዩ አገር ስደተኞች በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች በሚገኙ 24 የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖራሉ። ከ4 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተመዝግበዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW