1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ተፈናቃዮች በምዕራብ ጎንደር

ሐሙስ፣ ሐምሌ 6 2015

አብዛኛዎቹ ስደተኞች በምዕራብ ጎንደር መተማ በኩል እንደሚገቡ የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የሱዳኑ ጦርነት በዞኑ ጫናዎችን እየፈጠረ ነው፡፡የኤርትራ ስደተኞች መጠለያውን ጥለው ለመውጣት ወደ መሐል አገር ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ታላቅ ፈተና እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡

Sudan EU richtet humanitäre Luftbrücke in den Sudan ein
ምስል Amanuel Sileshi/AFP

የሱዳን ተፈናቃዮች በምዕራብ ጎንደር

This browser does not support the audio element.

በሱዳን የቀጠለው ጦርነት በአጭር ጊዜ የማይቋጭ ከሆነ በአጎራባች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጫናው እንደሚበረታ የምዕራብ ጎንደር አስተዳደር አስታወቀ፡፡ ከ60ሺህ በላይ የ72 አገር ዜጎች ወደሚፈልጉበት ቦታ መሸኘታቸውን አስተዳደሩ አመልክቷል፣ ለሱዳንና ኤርትራውያን ስደተኞች አስፈላጊው እገዛ እየተደረገ እንደሆነ ተገልጧል፡፡በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል ሚያዝያ 2015 ዓም  አጋማሽ ላይ የተጀመረው ውጊያ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናዉያንንና በአገሪቱ ይኖሩ የነበሩ የሌሎች አገር ዜጎችን አፈናቅሏል።  ለሞትና ለአካል ጉዳት የተዳረጉም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።ጦርነቱን ሸሽተው ወደ ሱዳን ጎረቤት አገሮች የሚጓዙ ዜጎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ተፈናቃዮቹ ከሚጠለሉባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷናት። አብዛኛዎቹ ስደተኞች  በምዕራብ ጎንደር መተማ በኩል እንደሚገቡ የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄ በጎረቤት ሱዳን ያለው ጦርነት በዞኑ ጫናዎችን እየፈጠረ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ዞኑ በቂ የስደተኞች መጠለያ ያዘጋጀ ቢሆንም አንዳንድ በተለይም የኤርትራ ስደተኞች መጠለያውን ጥለው ለመውጣትና ወደ መሐል አገር ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት ታላቅ ፈተና እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ቢሆነኝ ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነና የሚሰደደው ሰው ቁጥር ከቀጠለ ዞኑ መደበኛ ተግባሩን ለማከናወን እንደሚከብደው ገልጠዋል፡፡“60 ሺህ 46 ተፈናቃይ በመተማ ዮሐንስ በኩል ገብተው አልፈዋል፣ የ72 አገር ዜጎች ናቸው፣ ህይዎታቸውን ለማዳን እየሸሹ ያሉት፣ በዞን ደረጃ ግብረኃል ተቋቁሞ ከሚመለከተው አካል ጋር እየሰተሰራ ነው፣ አሁን ላይ ቁጥሩ እየጨመረ ነው፣ ዞናችን ከሀገረ ሱዳን ጋር ሰፊ ወሰን ይጋራል፣ ዞኑ የሰላም፣ የፀጥታ፣ የመልካም አስተዳደር ስራዎች አሉበት፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ  ሥረዎች እየተከናወኑ ነው፣ ቁጥሩ (ተፈናቃዩ፣ስደተኛው) የሚጨምር ከሆነ የሎጂስቲክስ፣ የትራንስፖርትና የጤና ችግር ሊገጥም ይችላል፣ ከዚህ አኳያ ተጨማሪ ጫናዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ” ብለዋል፡፡ከ24ሺህ በላይ ኤርትራዊያንና ሱዳናውያን በአሁኑ ሰዓት በሁለት መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚኖሩ የተናገሩት አቶ ፋንታሁን፣አሁንም ደንበር እያቋረጡ የሚመጡ ስደተኞች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡“ 8ሺህ 328 የሚሆኑ ኤርትራውያንና 15 ሺህ 541 ሱዳናውያን በዞኑ በተዘጋጁ ሁለት የስደተኞች  ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ፣ አሁን ቁጥሩ ከመጨመር አንፃር የሚመለከተውን አካል አስፈላጊውን እርዳታና ድጋፍ የሚጠይቅ ነው፡፡”

ምስል Amanuel Sileshi/AFP

4ኛ ወሩን የያዘውን የሱዳኑን ግጭት ለማስቆም የተለያዩ ጥረቶች ቢካሄዱም እስካሁን ጦርነቱ ከመባባስ ውጪ ያመጣው ነገር የለም፣ በቅርቡ በኬንያ መሪነት ኢትዮጵያ፣ ፣ ደቡብ ሱዳንና ጂቡቲ በአዲስ አበባ ውስጥ የሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ግጭት ለማስቆም ምክክር አድረገዋል፣ በተመሳሳይ ግብፅ የሱዳን ጎረቤት ሀገራትን በማስተባበር ጦርነቱ እንዲቆም በካይሮ ሌላ ውይይት ለማድረግ ተዘጋጅታለች፣ በጉዳዩ ዙሪያ የግብፁ ፕሬዚደንት አብዱል ፈታህ አልሲሲና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  ትናንት ካይሮ ውስጥ መወያየታቸውን ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW