1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ተፋላሚዎች እንዲነጋገሩ ኢጋድ የጀመረው ጥረት

ሰኞ፣ ሐምሌ 3 2015

ኢጋድ በኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ በአዲስ አበባ በተመራው ውይይት ላይ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች እንደሚገኙ ማረጋገጫ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም እንዳልተገኙ አስታውቋል። በውይይቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ የጅቡቲ እና የደቡብ ሱዳን የዩናይትድ ስቴትስ፣ሳዑዲ አረብያና የአውሮጳ ሕብረትና ሌሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።

IGAD Treffen / Sudan in Addis Abeba
ምስል Office of the PM Ethiopia

የሱዳን ተፋላሚዎች እንዲነጋገሩ ኢጋድ የጀመረው ጥረት

This browser does not support the audio element.


በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የተመራውና የአባል ሀገራቱ መሪዎች የተሳተፉበት የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎችን ወደ ሰላም ስምምነት ማምጣት ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሄደ።  ኢጋድ ዛሬ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ  በኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ አዲስ አበባ ላይ የተመራው ውይይት ላይ ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች በውይይቱ እንደሚገኙ ማረጋገጫ ሰጥተው የነበረ ቢሆንም እንዳልተገኙ አስታውቆ ጥልቀት ያለው ውይይት መደረጉን አስታውቋል። በውይይቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ፣ የጅቡቲ እና የደቡብ ሱዳን ፣ የዩናይትድ ስቴትስ፣ የግብጽ፣ የሳውዲ አረቢያ ፣ የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ፣ የዩናይትድ ኪንግደም ፣ የአውሮጳ ሕብረት እና ሌሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል ተብሏል።ኢጋድ ዛሬ ተደርጓል ያለውን "ገንቢ ውይይት" ተከትሎ በውይይቱ ተሳታፊ አባል ጎረቤት ሀገራት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሱዳን "የጠመንጃ ላንቃዎችን ለመዝጋት" እና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት አመስግኗል። ችግሩን ለመፍታት የፊታችን ሀሙስ በግብፅ ሊደረግ የታቀደውን ውይይት ይህ ቡድን በደስታ እንደሚቀበለውም ተገልጿል። 

ሱዳን ውስጥ መረጋጋት እንዲኖር የዩናይትድ ስቴትስ እና የሳውዲ አረቢያ መንግሥት እያደረጉት ነው ያለውን ጥረትም ኢጋድ በመግለጫው እንደሚያደንቅም አስታውቋል። በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነቱ መባባስ ፣ የተለያዩ የተኩስ አቁም ስምምነቶች በተደጋጋሚ መጣስ እና ከካርቱም ውጭ ያለው ሁከት ወደ ሌሎች የሱዳን ክፍሎች በተለይም በዳርፉር እንዲሁም በኮርዶፋን መስፋፋቱ የጎሳ እና የሃይማኖት መልክ መያዙ እንደሚያሳስበው በውይይቱ ማብቂያ የወጣው በመግለጫ ተገልጿል። 

ምስል Yohannes G/Eziabhare

ተፋላሚ ወገኖች ሁከቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ያለ ቅድመ ሁኔታ እና ላልተወሰነ ጊዜ የተኩስ አቁም እንዲፈርሙ በውጤታማ የማስፈጸሚያ እና የክትትል ዘዴ የሚደገፍ የጦርነት ስምምነት እንዲፈርሙ በጥብቅ ያሳሰበው ይህ አደራዳሪ ቡድን በግጭቱ ለተጎዱ ሱዳናውያን ሁሉ አፋጣኝ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማመቻቸት ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ወስኗል። ሁሉም የሱዳን ጉዳይ ተዋናዮች ግጭቱን ወደ ዘላቂ ሰላም መፍትሔ ለማምጣት በራሳቸው በሱዳኖች የሚመራ ውይይት እንዲያደረግ ተጠይቋል።
የሱዳን ብሔራዊ ጦር መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሀን እና ፈጥኖ ደራሽ የሚባለው ኃይል መሪ ጄኔራል ሞሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ የለኮሱት እና ሦስት ወራት እየሞላው የሚገኘው የእርስ በርስ ጦርነት በተኩስ አቁም እንዲገታ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ( ኢጋድ ) የኢትዮጵያ፣ የጂቡቲ፣ የኬንያ እና የደቡብ ሱዳን መሪዎችን በአደራዳሪነት መሰየሙ ከተነገረ ቆይቷል።ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ እንዳሉት ኢጋድ የአባል ሀገራቱ ተጽዕኖ ያለበት መሆኑ እና በራሱ ምንጭ የሚንቀሳቀስበት ሀብት የሌለው ድርጅት መሆኑ በቀጣናው የሰላም ማደራደር ተግባር ላይ የጎላ ሚና እንዳይኖረው አድርጎታል።
"የአባላት የፖለቲካ ጥገኛ ነው። ሁለተኛው ደግሞ እንደ አብዛኞዎቹ የአፍሪካ ተቋማት የገንዘብ ነፃነት ያለው ተቋም አይደለም።በፕሮጀክት ላይ የተመሰረተ ማንነት ነው ያለው"
የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጭምር በውይይቱ እንደሚሳተፉ መረጃዎች ያሳያሉ። በውይይቱ ላይ የግጭቱ መሪ ተዋናይ ጀነራሎች አለመገኘታቸውን ኢጋድ አረጋግጧል። ያነጋገርናቸው ተንታኝ እንደሚሉት የተፋላሚዎቹ ወቅታዊ ኃይል ለመደራደር ዝግጁ እንዳይሆኑ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ በኢጋድ አባል ሀገራት እምነት የሚጣልበት አሸማጋይ አካል አለመኖሩ ሌላ ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል። 
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈራረሙ ከስምምነቱ በፊትም ሆነ በኋላ ስኬት የታየበት ያለውን የማግባባት ሥራ ማከናወኑን ኢጋድ አስታውቆ ነበር። ተንታኙ እንደሚሉት ኢጋድ ከነችግሮቹም ቢሆን የሱዳኑን የሰላም ስምምነት ለማሳካት እድል ያለው ይመስላል።
ሱዳን የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት እስካሁን 3 ሚሊዮን የሚጠጋን ሕዝብ ከመኖሪያው አፈናቅሎ ወደ 7 መቶ ሺህ የሚሆኑት ሀገራቸውን ጥለው እንዲሸሹ አድርጓል።
ሰሎሞን ሙጬ 
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ

ምስል Office of the PM Ethiopia

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW