1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች እና የአሜሪካ የሰላም ሃሳብ

ዓርብ፣ ኅዳር 19 2018

የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት ውድቅ አድርገዋል።በሚሊዮኖች ላይ አደጋ የደቀነው የሱዳን ጦርነት እንዲቆም እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትን ለመጨመር ዓለም አቀፋዊ ጫና ቀጥሏል።ተንተኞች ጫናው ተፋላሚ ሀይሎችን በሚረዱ እንደ አረብ ኢመሬቶች ያሉ የውጭ ሀይሎች ላይ ጭምር መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ።

የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መሪ ጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ
የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መሪ ጀነራል ሀምዳን ዳጋሎምስል፦ Bandar Algaloud/Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች እና የአሜሪካ የሰላም ሃሳብ

This browser does not support the audio element.

በዚህ ሳምንት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል (RSF) አዛዥ ጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ "ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም" መፈለጋቸውን ገልፀዋል።ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ "የአንድ ወገን የተኩስ አቁም" በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላቀረቡት እና« ኳድ» የሚባሉት ሸምጋይ  ሀገራት ማለትም  ዩናይትድ ስቴትስ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች እና ሳዑዲ አረቢያ ለደገፉት ዓለም አቀፍ ጥረት ምላሽ ነው ብለዋል።

ያም ሆኖ ከአንድ ቀን በኋላ ያለፈው ማክሰኞ በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ሃይሎች በምዕራብ ኮርዶፋን ባባኑሳ በሚገኘው የእግረኛ ጦር ሰፈር ላይ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉን ጥቃት ማክሸፉን ገልጿል። ከዚህ አንፃር ፤መቀመጫውን ለንደን ያደረገችው ሱዳናዊቷ የፖሊሲ ተመራማሪ ሊና በድሪ “አርኤስኤፍ የተኩስ አቁምን መቀበል ታክቲካዊ እርምጃ ነው” ስትል ለDW ተናግራለች። 

«በእኔ አስተያየት በእርግጠኝነት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የተኩስ አቁምን መቀበል ታክቲካዊ እርምጃ ነው።ራሳቸውን የአስተዳደር አካል አድርገው ለማቅረብ የሚደረግ ጥረት ነው። ይህም የራሳቸውን ትይዩ መንግስት ካቋቋሙ ጊዜ ጀምሮ ዋነኛ ግባቸው ነው። ከቅርብ ጊዜ ባህሪያቸው ጋርም የሚመሳሰል ነው,።ታውቃላችሁ  በኤልፋሽር በሲቪሎች ላይ ለተፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሁሉ የግለሰብ ተዋናዮችን ተጠያቂ ያደርጋሉ።»
ሁለቱም ወገኖች በዩናይትድ ስቴትስ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ሳዑዲ አረቢያ በመስከረም ወር በቀረበው የስምምነት ሃሳብ ላይ የተመሰረተውን እና በአሜሪካ የሚደገፈውን አዲሱን የእርቅ ሀሳብ አልተቀበሉም። 

ስምምነቱ ለሶስት ወራት የሚቆይ የሰብአዊ የእርቅ ስምምነት፣ የተኩስ አቁም፣  ማንኛውንም ተዋጊ ሀይል የማያካትት እና በሲቪል የሚመራ ህጋዊ መንግስት ለመመስረት የሚያግዝ የፖለቲካ ሽግግር ሂደትን ያካትታል።ያም ሆኖ ያለፈው እሁድ  የሱዳኑ ጦር መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ ቡርሃን በቪዲዮ በሰጡት መግለጫ ሃሳቡ ተቀባይነት የሌለው እና ከ«እስካሁኑ በጣም የከፋ ነው» ብለዋል። በተጨማሪም የስምምነት ሀሳቡ የሚሬቶችን “የውይይት ነጥቦችን”የሚያያንፀባርቅ ነው ሲሉ ነቅፈዋል።

በሱዳን  የእርስበእርስ ጦርነት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ  የሱዳን ፈጥኖደራሽ ሀይል ዋና ደጋፊ ተደርጋ የምትታይ ሀገር ነች። አቡ ዳቢ ይህን ውንጀላ ደጋግማ አስተባብላለች።ነገር ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ የምታደርገውን  የወታደራዊ አቅርቦት  ማስረጃዎችን በተደጋጋሚ ማግኘታቸውን ገልፀዋል።  

የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች በሱዳን ጦርነት ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉን ታስታጥቃለች በሚል ትወቀሳለችምስል፦ Zak Irfan/Avalon/picture alliance

ገለልተኛ የጦር መሳሪያ ትንታኞች ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ በሱዳን ይጠቀምባቸው የነበሩ የጦር መሳሪያዎች እና ጥይቶች መነሻው ከኢመሬትስ  ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።የሱዳን ወታደራዊ ተንታኝ ያሲር ዘይዳን እንደሚለው  ይህንን የአረብ ኢመሬቶች ድጋፍ ለማስቆም  ጫና ማሳደር የሚችሉት ትራምፕ ብቻ ናቸው።  «እኔ እንደማስበው የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ጊዜ ብቻ ነው። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ያላቸውን ድጋፍ እንዲገድቡ ጫና ማድረግ የሚችለው። እንደዚህ አይነት አለም አቀፋዊ ክልላዊ ሽፋን እና ወታደራዊ ድጋፍ ከሌለ፣ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል መቋጫ ላይ ለመድረስ እና መሳሪያዎቻቸውን ለማውረድ ግፊት  ያደርጋል ብዬ አስባለሁ።»ብሏል።

ይህንን ሀሳብ  ፊክር የተባለው የሱዳን ጥናትና ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አምጋድ ፋሬድ ኤልታይብ ይጋራል።በሱዳን ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዋና ሚናን ማካተት እንዳለበት ይገልፃል።

«ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት እውን እንዲሆን፣ መደረግ ያለባቸው በርካታ ሁኔታዎች አሉ። በመጀመሪያ የ RSF የመሳሪያ አቅርቦትን ማቋረጥ፣ ሁለተኛ፣ በRSF ላይ የህግ እና የገንዘብ ተፅዕኖ ያለው ተጨባጭ ስጋት ያስፈልጋል። ሦስተኛ፣ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ላይ ስጋት የሚያሳድር  የተጠናከረ፣ እውነተኛ እና ከባድ ጫና ያስፈልጋል። ዘላቂ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማምጣት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ በRSF የጭካኔ ድርጊት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዋና ሚና መነገር አለበት።»በማለት ገልጿል።

ተመራማሪው አያይዞም  "የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በሕዝብ በመጋለጥ፣ በኮንግሬስ ግፊት ማድረግ፣ በማዕቀብ ወይም በፋይናንሺያል ምርመራ ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል። ,ያ ካልሆነ ከንግግር ያለፈ የተግባር ለውጥ አይመጣም ሲል ገልጿል።

በሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መሪ በጀነራል ሀምዳን ዳጋሎ መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ በጎርጎሪያኑ ሚያዚያ 2023ዓ/ም  የተጀመረውን የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም፤እስካሁን የተደረገው እያንዳንዱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ከሽፏል። ሁለቱም ወገኖች የተኩስ አቁም ሙከራዎችን ሁሉ ጥሰዋል።

የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ተዋጊዎች በአቡ ሉሉ ዳርፉር በቁጥጥር ስር ከዋለ ታጣቂ ጋርምስል፦ Rapid Support Forces (RSF)/AFP

ለምንድነው ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን መቀጠል የፈለጉት?

ሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን ወደ ሱዳን ጦር ለማዋሃድ በተደረገ ሙከራ በሁለቱ ጀነራሎች የስልጣን ሽኩቻ የተጀመረው የሱዳን ጦርነት በወርቅ እና በነዳጅ የበለጸገችውን ሀገር ወደ መለያየት አፋፍ አድርሷታል፡ ወታደራዊ ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ በበኩሉ አብዛኛው የሱዳን ምዕራብ ዳርፉርን እና የተወሰኑትን የደቡብ ክፍሎች የሚቆጣጠር ሲሆን፤ በጀመራል አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ደግሞ አብዛኛውን መሃከል፣ ሰሜን እና ምስራቅ የሀሪቱን ክፍል ይቆጣጠራል።

ፈጥኖደራሽ ሀይሉ በመጋቢት እና ሌሎች የታጠቁ ቡድኖች መንግስት የመመስረት ኃላፊነት የተሰጠው የሱዳን መስራች ህብረትን (TASIS) አቋቁመዋል።ሆኖም፣የአልቡርሃኑ የሱዳን ጦር እንደ ህጋዊ አካል አይቀበልውም፣ እና ሁለቱም ወገኖች አገሪቷን በሙሉ ለመቆጣጠር እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።ሱዳናዊቷ የፖሊሲ ተመራማሪ ሊና በድሪ ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ትይዩ መንግስት ካቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ዋና አላማው ራሱን ህጋዊ  የሀገሪቱ አስተዳደር አድርጎ ማቅረብ ነው። በአንፃሩ የሱዳን ጦር በውጪ የሚደገፉ ታጣቂዎችን የሚዋጋ የሉዓላዊ ሀገር ጠበቃ መሆኑን በተደጋጋሚ አፅንዖት መስጠቱን ገልጻለች። በዚህ የተነሳ ሁለቱም በድሪ እንደምትለው ሁለቱም ተፈላሚ ሀይሎች የተኩስ ማቆምም ሆነ የፖለቲካ መፍትሄን እንደ መልካም አጋጣሚ አይመለከቱትም።

የሀገሪቱ ዜጎች ጉዳቱን መሸከማቸውን ቀጥለዋል

ያም ሆኖ የሀገሪቱ ዜጎች ጉዳቱን መሸከማቸውን ቀጥለዋል።«አክሽን አጌንስት ሀንገር» የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ረድኤት ድርጅት የጀርመን ዋና ዳይሬክተር ጃን ሴባስቲያን ፍሪድሪች ረስት ከኤል ፋሸር 100 ኪሎ ሜትር  ርቀት ላይ ከሚገኘው  ቦታ ሆነው እንደገለፁት «አንድ ዶክተር ከሶስት ጤና ረዳቶች ጋር  25,000 ሰዎችን ይንከባከባሉ» ብለዋል ። በዚሁ አካባቢ200 ህጻናት በከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚሰቃዩ ገልፀዋል።

በሱዳን ጦርነት 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናዉያን ተፈናቅለዋል ። ረሃብ ተስፋፍቷል ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።ምስል፦ Rian Cope/AFP

በሀገሪቱ ለህይወት አስጊ የሆነ ረሃብ መኖሩን ያመለከቱት ፍሬዲሪሽ ረስት «30 ሚሊዮን ሱዳናውያን በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ጥገኛ ናቸው። ያምሆኖ  ከጀርመን እና ከሌሎች ለጋሽ አገሮች የሰብዓዊ እርዳታ በበቂ ሁኔታ ባለመገኘቱ ከአሥሩ አንድ ብቻ እርዳታ ያገኛል ።»ብለዋል።
የአለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ እና ሌሎች አለምአቀፍ አካላት እንዳስታወቁት የሱዳን ጦርነት የዓለማች ትልቁን የሰብአዊ እና የመፈናቀል ቀውስን አስከትሏል።

በጦርነቱ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናዉያን ተፈናቅለዋል ። ረሃብ ተስፋፍቷል ፣ እንደ መብት ድርጅቶች በቅርቡ በኤልፋሽር የተፈፀመውን ጥቃት ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW