የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 20 2015
ሁለት ሳምንት የዘለቀው የሁለቱ የሱዳን ጀንራሎች ጦርነት፤ አገሪቱን መንግሥት አልባ እንዳያደርጋትና እንዳያፈርሳት አስግቷል። ባለፉት ቀናት ሲፈርስ ሲከበር የነበረው የተኩስ ማቆም ስምምነት፤ በርካታ የአውሮጳና ሌሎች መንግሥታት ዜጎቻቸውን በየብስ፤ በባሕርና በአየር ለማስወጣት ያስቻላቸው ሲሆን፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሱዳኖችም ወደ ጎረቤት አገሮች እንዲሸሹ ረድቷቸዋል። የተቀሩትና 46 ሚሊዮን የሚሆኑት፤ በተለይም የጦር ሜዳ የሆነችው ካርቱም ኑዋሪዎች የሆኑት ሱዳኖችና ስደተኖች ግን፤ ሲበዛ ለሞት፤ ሲያንስ ለረህብና ለበሽታ ተጋልጠው ባሳዛኝ ሁኒታ እንደሚገኙ ነው ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች የሚገልጹት።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ ሱዳን በዚህ ጦርነት ምክኒያት ወደ አስከፊ ሰባዊ ቀውስና የመፍረስ አደጋ እንዳትገባ በማሳሰብ ላይ ነው። ምዕራባውያን መንግስታት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት እንደተጣደፉት ሁሉ፤ በጭንቅና ችግር ውስጥ ያሉ ሱዳናውያንን ሊረሱ እንድማይገባ የሚያሳስቡ ጥሪዎችም ተሰምቷል። ዲፕሎማቶችና የዉጭ ሃገር ዜጎች ሱዳንን እየለቀቁ መሆኑበአሁኑ ወቅት በካርቱም የውኃ፤ የመብራትና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል፤ መደብሮችም ተዘግተዋል ወይም ተመዝብረዋል። በየቦታው ከሚሰማው ተኩስና በየጎዳናዎቹ ከሚደረጉት ጦርነቶች በተጨማሪ፤ ወሮበላዎች ተደራጅተው ከተማዋን እያፈረሱና እየመዘበሩ እንደሚገኙ ነው የሚገለጸው።
በክተማው የሚገኙ የጤና ተቁሞች በመፈራረሳቸውና በመዘረፋቸው አገልግሎት መስጠት እንዳልቻሉ እየተነገረ ሲሆን፤ የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ባለፈው ረቡዕ እንደገለጹት በህክምና እጦት የሚሞተው ሰው ቁጥር በጦርነቱ ከሚሞተው ሊበልጥ ይችላል። «በጦርነቱ ምክንያት ከሚደርሰው የሞትና የመቁሰል አደጋ ይበልጥ በበሽታ፤ በምግብና ውኃ አገልግሎቶች መቋረጥ ምክንያት ለሞት የሚዳረገው ሰው ሊበዛ ይችላል።» በማለት በድርጅታቸው ግምት እሳክሁን ሕይወታቸውን ካጡት ውስጥ አንድ ሦስተኛዎቹ ህክምና ቢያገኙ ሊተርፉ ይችሉ የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ዶክተር ቴዎድሮስ አክለውም፤ በአሁኑ ወቅት ባለው ሁኒታ ምክንያት ሀኪሞችና ነርሶች በሽተኞችን ሊደርሱ፤ በሽተኞችና ቁስለኞችም ሀኪሞችን ሊያገኙ እንዳልቻሉ በማውሳትም፤ በካርቱም ብቻ 61 ከመቶ የሚሆኑት የህክምና ተቋማ እንደወደሙ አስታውቀዋል።
ባለፉት ሦስት ቀናት ከሞላ ጎደል በሥራ ላይ የነበረው የተኩስ ማቆም ስምምነት ከትናንት ሌሊት ጀምሮ ለተጨማሪ ሦስት ቀናት እንዲራዘም ሁለቱ ጀኔራሎች እንደተስማሙ ተሰምቷል። ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ይከበራል ተብሎ ባይጠበቅም፤ እየደረሰ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመቀነስና ተጨማሪ ሰዎች ከጦርነቱ ቀጣና እንዲወጡ ሊያግዝ ይችላል። በተጨማሪም በአፍርቃ በይነ መንግሥታት ኢጋድና በሌሎችም አገሮች በኩል የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች እንዲቀጥሉ ዕድል ሊከፍት ይችላል ተብሎም ተስፋ ተድርጓል። ይሁን እንጂ በሁለቱ ጀነራሎች ማካከል ያለው አለመግባባት ስር የስደደና የግል የሥልጣን ፍላጎት ያለበት በመሆኑ፤ እንዲሁም በሌሎች አካባቢያዊ፤ ፖለቲክዊና ወታደራዊ ምክንያቶች፤ በሱዳን ባጭር ጊዜ ሰላም ወርዶ ሱዳንና ሱዳንውያን ከገቡበት ችግር በቀላሉ ይወጣሉ ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ እንደሚሆን ነው የሚገመተው።
ገበያው ንጉሤ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ